የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን – Vaginal Candidiasis

የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን እጅግ በጣም የተለመደ እና ከ4 ሴቶች በ3ቱ ላይ በዕድሜ ዘመናቸው ቢያንስ አንዴ የሚከሰት የሕመም ዓይነት ነው፡፡

የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን ከአባለዘር በሽታዎች ውስጥ የማይመደብ ሲሆን ቀላል በሚባል ሕክምና ሊድን የሚችል ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ከ4 እና ከዛ በላይ የሚከሰት ከሆነ ግን ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ሕክምና ያስፈልገዋል፡፡

የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ካንዲዲያ (Candidia) በሚባል ፈንገስ ምክንያት ነው፡፡

በሴቶች ማህፀን በተፈጥሮ የሚገኙ የፈንገስ እና የባክቴሪያ ሕዋሳት አሉ፡፡ ሁለቱም በተመጣጠነ ሁኔታ የሚገኙ ሲሆን ባክቴሪያው አሲድን በማመንጨት የፈንገስ መብዛትን ይከላከላል፡፡ ማንኛውም ዓይነት ይህን ተፈጥሮአዊ መመጣጠን

የሚያዛባ ሁኔታ ለፈንገስ መባዛት (yeast overgrowth) ስለሚዳርግ የማህፀን ማሳከክ፣ማቃጠል እና ሌሎች ምልክቶችን ያስከትላል፡፡

✔ የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን በምን ምክንያት ይከሰታል?

– ፀረ ባክቴሪያ(Antibiotic)መውሰድ በማህፀን ውስጥ የሚገኘውን የባክቴሪያ መጠን ስለሚቀንስ ለማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን ምክንያት ይሆናል
– እርግዝና
– በሕክምና ያልተስተካከለ የስኳር ሕመም ካለብን
– በሽታ የመከላከል አቅማችን የተዳከመ ከሆነ
– በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ የማህፀን ውስጥ ባክቴሪያ መጠን ሲቀንስ ለማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን ሊያጋልጥ ይችላል፡፡

✔ ለማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን ተጋላጭነት የሚጨምሩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

– ፀረባክቴሪያ በመውሰድ ላይ ያለች ሴት
– የኤስትሮጂን ሆርሞን መጠን መጨመር፣ እርጉዝ (ነፍሰጡር) ሴቶች እና የኤስትሮጂን መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚወስዱ ሴቶች
– በሕክምና ክትትል ያልተስተካከለ የስኳር ሕመም ያላቸው ሴቶች
– በሽታን የመከላከል አቅማቸው የተዳከሙ ሴቶች
– ግብረስጋ ግንኙነት፡- የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን ከአባለዘር በሽታ ባይመደብም በተለያዩ የግብረስጋ ግንኙነት አይነቶች ምክንያት ግን ሊተላልፍ ይችላል፡፡

✔ የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን ምልክቶች ምንድን ናቸው?

– በማህፀን አካባቢ ማሳከክ
– የውሃሽንት በማስወጣትና በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ የማቃጠል ስሜት
– የማህፀን አካባቢ መቅላትና ማበጥ
– የማህፀን ሕመም
– ነጭ፣ወፍራም እና ሽታ አልባ የማህፀን ፈሳሽ መኖር ናቸው፡፡

✔ ከባድ የሆነ የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን መኖሩን የሚያመለክቱ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

– ከፍተኛ የሆነ የማህፀን ማሳከክ፣ማበጥ እና መቅላት መኖር
– በዓመት ውስጥ 4 ጊዜ እና ከዛ በላይ የሚከሰት የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን
– ነፍሰጡር ሴት ላይ የሚከሰት የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን
– በሕክምና ያልተስተካከለ የስኳር ሕመም መኖር
– ከተለመደው የፈንገስ ዓይነት በተለዬ የፈንገስ ዓይነቶች የሚከሰት ኢንፌክሽን
– በሕክምና ወይንም በሕመም ምክንያት የተዳከመ በሽታን የመከላከል አቅም መኖር ናቸው፡፡

✔ የማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽንን እንዴት መከላከል ይቻላል?

– የማያጠብቁ (ዘና የሚያደርጉ) ሱሪዎችን መልበስ
– ከጥጥ የተሠሩ የውስጥ ሱሪዎችን መልበስ
– ዕርጥበት ያላቸውን የውስጥ ሱሪዎች ለብሰው አለመቆየት ለምሳሌ የዋና ልብስ
– በጣም በሚሞቅ ውሃ አለመታጠብ ወይንም አለመዘፍዘፍ
– የግል ንጽህናን በሚገባ መጠበቅ

✔ ሐኪምዎን ማማከር ያለብዎት መቼ ነው?

– በሕመሙ ሲጠቁ የመጀመሪያዎ ከሆነ
– በማህፀን ፈንገስ ኢንፌክሽን መያዝዎን እርግጠኛ መሆን ካልቻሉ
– የሕመሙ ምልክቶች ሐኪምዎ በሚሰጥዎት መድኃኒት ማይጠፋ ከሆነ
– ሌሎች ተጨማሪ ምልክቶችን ካስተዋሉ ናቸው፡፡

የሕመሙን ምልክቶች እንዳስተዋሉ ወደሕክምና ቦታ በመሄድ ለሕክምና የሚሆን መድኃኒት በመውሰድና በሚገባ በመጠቀም ከሕመሙ ነፃ መሆን ይችላሉ፡፡

በዶr/ርሆነሊያት ኤፍሬም)

Advertisement