ፆም በሰውነታችን ውስጥ የሚያስከትለው ለውጥ እና የሚሰጠው ጥቅም ምንድን ነው?

ለእስልምና እና ለክርስትና እመነት ተከታዮች ዋነኞቹ የፆም ወቅት የሆኑት ረመዳን እና ዓቢይ ፆሞች ተጀምረዋል። የሁለቱም እምነቶች ምዕመናን የፆሙን ጊዜ በየራሳቸው ሥርዓት እና ደንብ መሠረት የሚከውኑት ሲሆን፣ በየዕለቱ ለረጅም ሰዓታት ከምግብ እና ከውሃ ርቀው ይቆያሉ።

የየእምነቶቹ ተከታዮች በፆም ወቅት ከእህል ውሃ ከመቆጠባቸው በተጨማሪ በልገሳ እና መልካም ነገሮችን እያደረጉ በጸሎት እና በምሥጋና ወደ ፈጣሪያቸው የበለጠ የሚቀርቡበበት ነው።

ምዕመናን በዋናነት በፆም አማካይነት ታላቅ መንፈሳዊ ፀጋን ለማግኘት ይተጋሉ። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ፆም ከፍተኛ የጤና በረከቶች እንዳሉት የሥነ ምግብ እና የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ዝርዝሩን እነሆ.

ሰውነታችን ከፆም ጋር የሚተዋወቀው ለመጨረሻ ጊዜ ምግብ ከቀመስን ከስምንት ሰዓታት በኋላ ነው። ይህም ማለት አንጀታችን ከተመገብነው ምግብ የሚያገኛቸውን ንጥረ ነገሮች በሙሉ አሟጦ ከጨረሰ በኋላ የሚሆን ነው።

ከዚህ በኋላ ሰውነታችን ተስፋ ይቆርጥና ፊቱን በጡንቻዎችን እና በጉበታችን ውስጥ ወደተከማቸ ጉሉኮስ ያዞራል። የተቀረው የሰውነታችን አካል ጉልበት የሚያገኘውም ከእነዚህ የመጠባበቂያ ‘ግምጃ ቤቶች’ ከሚያገኘው ኃይል ይሆናል ማለት ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥም በጡንቻዎቻችን እና በጉበታችን ውስጥ ያለው የጉሉኮስ ክምችት ሲያልቅ ሰውነታችን ሌላ አማራጭ ስለማይኖረው ስብን (Fat) ማቃጠል ይጀምራል። ከዚህ በኋላ ሙቀት እና ጉልበትን የሚያገኘውም ከሌላ ሳይሆን ስብን በማቃጠል ይሆናል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ መልካም ነገሮች ይከሰታሉ። ሰውነታችን ኃይል ለማግኘት የሚያቃጥለው በጤናችን ላይ ችግርን ሊያስከትል የሚችለውን ስብ በመሆኑ ከፆም ለጤናችን ጠቃሚ ውጤቶችን እናገኛለን።

በዚህም ክብደት መቀነስ፣ የኮሌስትሮል መጠን መውረድ በዋናነት የሚታይ ለውጥ ይሆናል። በተጨማሪም የስኳር መጠናችን በዚህ ወቅት ዝቅ ማለቱ አይቀርም።

ሆኖም ግን በደማችን ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ስለሚቀንስ ድካም እና መዛልን ሊስከትልብን ይችላል።

ይህን ተከትሎም መጠነኛ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ እና መልካም ያልሆነ የአፍ ጠረን ሊከተል ይችላል። ይህ የሚሆነው በረሃብ ምክንያት ሆዳችንን ሲሞረሙረን እና ያለ ምግብ መቆየቱ ለሰውነታችን እየከበደው ሲመጣ ነው።

ከ3 እስከ 7ኛ ቀን

ሰውነታችን ፆሙን እየተለማመደ ሲመጣ በውስጣችን የሚገኘው የስብ ክምችት እየተሰባበረ ራሱን ወደ የደም ስኳርነት (Blood sugar) ይለውጣል።

የምንወስደው ፈሳሽ መጠን እየቀነሰ መምጣቱ በሰውነታችን ውስጥ ያለው ፈሳሽ ወደመሟጠጥ (ዲሃይድሬሽን) ስለሚያመራ በማፍጠሪያ ወይም ፆም በሚገደፍበት ሰዓት እና ከዚያም በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ በርከት ያሉ ፈሳሾችን መውሰድ ይመከራል።

በፆም መግደፊያ ሰዓት የምትወስዱት የምግብ መጠን ጉልበት ሰጪ የሆኑ ተመጣጣኝ ምግቦችን ማግኘት ጠቃሚ እንደሆነ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በፕሮቲን ከበለጸጉ ምግቦች ባሻገር ጨው እና በርከት ያለ ውሃ ከሌሎች የተመጣጠኑ ምግቦች ጋር ማግኘት ለሰውነታችን መልካም ሁኔታን ይፈጥራል።

ከ8ኛ እስከ 15ኛ ቀናት

በዚህ ጊዜ ሰውነታችን ፆሙን ተላምዶታል። በዚህም የተነሳ ድካም እና መዛሉ እንደመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

በኬምብሪጅ አዴንብሩክ ሆስፒታል ውስጥ ነው የሚሠሩት፣ የአኔስቴሺያ እና የጽኑ ህሙማን ሕክምና አማካሪው ዶክተር ራዚን ማህሩፍ እንደሚሉት በዚህ ወቅት “ፆሙ ለሰውነታችን ሌላም በጎ ጎን ይዞ ይመጣል።”

ለምሳሌ በሌላው ጊዜ በርከት ያለ ካሎሪ ያላቸው ምግቦችን የምንወስድ ከነበረ ሰውነታችን ሥራዎችን በአግባቡ ለመፈጸም ፈተና ውስጥ ይወድቅ ነበር። ወይም ደግሞ እክል ይገጥመዋል። በፆም ጊዜ ግን ይህ ሁኔታ ይስተካከላል።

“ምክንያቱም የካሎሪ ክምችት ስለማይበዛበት ሰውነታችን ወደ ሌሎች ሥራዎች ትኩረቱን ያደርጋል” ይላሉ ሐኪሙ። ለዚህም ነው “ፆም ኢንፌክሽን በመዋጋት እና ጤናን በመመለስ አስተዋጽኦ የሚኖረው።”

ፆም በጊዜ ሂደት ውስጥ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ እንዲሁም በአጠቃላይ ጤና ላይ ለውጥን ያስከትላል

ከ16ኛ አስከ 30ኛ ቀናት

አንድ ሰው መፆም ከጀመረ ሁለት ሳምንት በኋላ ማለትም ከ15ኛው ቀን ጀምሮ ሰውነት ሙሉ በሙሉ ፆሙን ይላመዳል። በዚህ ጊዜ እነ ደንዳኔ፣ ጉበት፣ ኩላሊት እንዲሁም ቆዳ ሁሉም ራሳቸውን በማጽዳት ሂደት (ዲቶክሲፊኬሽን) ሥራን በማከናወን ለጤና ጠቃሚ የሆነውን ሚና ይወጣሉ።

ዶክተር ማህሩፍ እንደሚሉት በዚህ ወቅት ጤና ተመልሶ፣ ሰውነታችን የቀድሞውን ጉልበቱን የሚያገኝበት እና የማስታወስ አቅም እና ትኩረት የማድረግ ብቃት ወደ ቀድሞው ሁኔታ የሚመለስበት ጊዜ ነው።

በዚህ ጊዜ ሰውነታችን ጉልበት ለማግኘት ወደ ፕሮቲን መሄድ አይኖርበትም። ይህ የሚሆነው ብዙውን ጊዜ ረሃብ ሲሰማንና ሰውነታችን ከጡንቻዎቻችን እየቀሰመ የሚወስደውን ምግብ ማደን ሲጀምር ነው። በዚህ መንገድ የሚቀጥለው ግን ለቀናት እና ለሳምንታት በተከታታይ ሲፆም ነው።

ስለዚህም በየትኛው እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚታዘዘው ፆም በየዕለቱ ለረጅም ሰዓታት ከተካሄደ በኋላ የሚጿሚዎች ሰውነት ለተለመደው እንቅስቃሴው ጉልበት ከምግብ እንዲያገኝ የመግደፊያ ወይም የማፍጠሪያ ሰዓት ዕድል ይሰጠዋል።

በዚህም ምግብ ብቻ ሳይሆን በርከት ያለ ፈሳሽ በመውሰድ የጿሚዎች ሰውነት መልሶ እንዲያንሰራራ ዕድል ይሰጠዋል።

ጡንቻዎቻች ውስጥ የሚገኝ የኃይል ክምችት ለመጠባበቂያነት እንዲቆይ ያደርጋል። በዚህም ሳቢያ የተወሰነ ኪሎ ለመቀነስ ይረዳል። ይህ ደግሞ ለጤና እና የአጠቃላይ ሰውነት ክፍሎች ደኅንነት መልካም አጋጣሚ ነው።

ፆም ጤናን ይጎዳል?

የካምብሪጁ አዲንብሩክ ሆስፒታል ሐኪም ዶክተር ማህሩፍ ፆም በጤና ላይ አሉታዊ ውጤት ይኖረው ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ምላሻቸው “እንደሁኔታው” የሚል ነው። እንደእርሳቸው አመለካከት በርከት ያሉ ሁኔታዎች ፆምን ለሰውነታችን ጎጂም ጠቃሚም ሊያደርጉት ይችላሉ።

ፆም ለሰውነታችን መልካም የሚሆንበት አንዱ ምክንያት መቼ ምን መብላት እንዳለብን ትኩረት እንድናደርግ ስለሚያስችለን ነው። ሁለተኛው ክብደታችንን መቆጣጠር እና የካሎሪ መጠን መወሰንን ያስችላል።

ለወር ያህል መፆም እምብዛምም የሚያመጣው የጤና እክል ባይኖርም፣ ከዚያ በኋላ ግን ለተከታታይ ጊዜ ያለማቋረጥ መፆም ግን አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ሐኪሙ ሳይጠቁሙ አያልፉም።

እንደ ሐኪሙ ማብራሪያ ያለማቋረጥ መፆም በቋሚነት ኪሎ ለመቀነስ አይረዳም። ምክንያቱም ከሆነ ጊዜ በኋላ ሰውነታችን ስብን ወደ ጉልበት መቀየር ያቆማል። ከዚያ ይልቅ ፊቱን ወደ ጡንቻዎቻችን ነው የሚያዞረው።

ይህ ደግሞ ጤናማ አይደለም። ምክንያቱም ሰውነታችን ከሆነ ጊዜ በኋላ “በመራብ ስሜት” ላይ ስለሚቆይ ነው።

ሐኪሙ እንደሚሉት እምነቶች ከመያዙት የፆም ጊዜያት ውጪ መፆም ቢያስፈልግ እንኳ በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ እያፈራረቁ መፆም በመደዳ ለተከታታይ ቀናት ከመፆም እጅግ የተሻለ ጤናማ ነው።

“ፆም በአግባቡ ከተጾመ እና በማፍጠሪያ/መግደፊያ ሰዓት በቂ ፈሳሽ ማግኘት ከተቻለ፣ ጠቃሚ የጡንቻ ክምችቶች ሳይቃጠል ኪሎ መቀነስ ስለሚያስችል የጤና በረከትም ያስገኛል” ይላሉ እኚሁ ሐኪም።

ምንጭ: BBC NEWS አማሪኛ

Advertisement