በእንቅልፍ ሰዓት ለምን ያልበናል…?

በእንቅልፍ ሰዓትም ይሁን በቀን በሙቀት የተነሳ ወይም በሌላ ምክንያቶች ሊያልበን ይችላል።
ሆኖም ግን ሌሊት በእንቅልፍ ሰዓት የሚከሰት ላብ ለበርካቶች ችግር ሲሆን ይስተዋላል።
አንዳንዶች የሚሞቅ የአየር ፀባይ በሌለበት ስፍራ ሁላ ከፍተኛ የሆነ ላብ እንደሚወጣቸው የሚናገሩ ሲሆን፥ በዚህም የተነሳ ልብስ እና አንሶላ ጭምር እንቀይራለን ይላሉ።
ይህም በቂ እንቅልፍ እንዳያገኙ ችግር እንደሆነባቸው የ
ሚናገሩ ሲሆን፥ ወደ ህክምና ተቋም በሚሄዱበት ጊዜም ህክምና የለውም በመባል የምንመለስበት ጊዜ ይበዛል ነው የሚሉት።

ላብ በአካባቢ ላይ በሚከሰት ሙቀት አማካኝነት ሊከሰት የሚችል ሲሆን፥ ሲጀምር በብዛት ፊት፣ አንገት እና ደረት አካባቢ እርጥበት ሊሰማን ይችላል።
በቅርብ የተሰራ ጥናት ግን በእንቅልፍ ሰዓት የሚከሰት ከፍተኛ የሆነ ማላብ የሌሎች ህመሞች ምልክት ሊሆን ይችላል እና ችላ ሊባል አይገባም ይላል።
የህክምና ባለሙያዎችም ቢሆኑ የታካሚዎቻቸው ማህደር ላይ ላቡ እንዴት እንደጀመራቸው በመመዝገብ እና ክትትል በማድረግ ችግሩን ከስር ሊያገኙት ይገባል ሲሉም ጥናቱ አመልክቷል።
በተለይም እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ትኩሳታቸውን መለካት፣ ያልተጠበቀ የሰውንት ክብደት መቀነስ እና ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት ከተስተዋላባቸው በህክምና መከታተል ይገባል የሚለውም በጥናቱ 
ተምልክቷል።

በእንቅልፍ ሰዓት ከሚከሰት ከፍተኛ ላብ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል የተባሉ ህመሞች 
# ቲቢ (Tuberculosis)፦ በእንቅልፍ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ላብ እንዲከሰትብን ሊያደርጉ ይችላሉ ከተባሉ ህመሞች ውስጥ ቲቢ (የሳንባ ነቀርሳ) አንዱ ነው።
በዚህ ሀመም ከተጠቁ ሰዎች ውስጥ 50 በመቶ ያክሉ በእንቅልፍ ሰዓት የሚከሰት ከፍተኛ የማላብ ችግር እንደሚታይባቸውም ይነገራል።
ሆኖም ግን ሳል፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ የድካም ስሜትም የህመሙ መለያዎች መሆናቸው ተነግሯል።
# “ብሩሴሎሲስ” (Brucellosis)፦ ብሩሴሎሲስ “ብሩሴላ” በተባለ ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት ኢንፌክሽን ሲሆን፥ በብዛት ከእንስሳት ወደ ሰዎች የሚተላላፍ ነው።
በተለይም ጥሬ ወተት የሚጠቀሙ ሰዎች “ለብሩሴሎሲስ” ኢንፌክሽን የመጋለጣቸው እድል የሰፋ ነው ተብሏል።
በዚህ ኢንፌክሽን የተጠቁ ሰዎችም በእቅልፍ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ላብ እንደሚታይባቸው ነው የተነገረው።
እንዲሁም የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት እና የሰውነት መዛልም ከምልክቶቹ ይጠቀሳሉ።

# ካንሰር፦ ከበርካታ የካንሰር ምልክቶች ውስጥ በእንቅልፍ ሰዓት የሚከሰት ከመጠን በላይ ያለፈ ላብ አንዱ ሊሆን ይችላል ይላሉ ተመራማሪዎች።
በተለይም “ለይምፎማ” በመባል የሚታወቀው እና የደም ማስተላለፊያ ትቦን የሚያጠቃው የካንሰር አይነት በእንቅልፍ ሰዓት ከፍተኛ ላብ እንዲከሰት ያደርጋል ተብሏል።
# የምግብ አለመፈጨት ችግር እና ቃር (heartburn) በእንቅልፍ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ላብ እንዲከሰት ያደርጋል የሚለውም በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም በህክምና ባለሙያ ታዘውልን የምንውጣቸው መድሃኒቶችም በቀንም ይሁን በማታ ከፍተኛ የሆነ ላብ እንዲከሰትብን ያደርጋሉ።
ስለዚህ በእንቅልፍ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ ላብ የሚያልበን ከሆነ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ህክምና ማድረግ እና የህክምና ባለሙያዎችን ማማከር መልካም ነው ተብሏል።

ምንጭ:- ዶክተር አለ (Doctor Alle)

Advertisement