የእግር እብጠት አለብዎ?

                                         

የእግር እብጠት ማንኛውንም ሰው ሊያጋጥም የሚችል የተለመደ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር በራሱ በሽታ አይደለም ነገር ግን ሌሎች ውስጣዊ ችግሮች እንዳሉ የሚያሳይ ምልክት እንጂ፡፡ ይህ ችግር የሚጀምረው ፈሳሽ በሰውነታችን የተለያዩ ክፍሎች በሚከማችበት ጊዜ ሲሆን እብጠት እንዲፈጠር ያደርጋል ይህ እብጠት በህክምና ቋንቋ ኢዴማ(Edema) ይባላል፡፡

ይህ ችግር የሚያጋጥመን በተለያዩ ምክንያቶች ነው ከነዚህም መካከል፦ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት፣ ለረጂም ጊዜ መቆም ወይም መቀመጥ፣ እድሜ፣ እርግዝና፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ደካማ የደም ዝውውር ናቸው፡፡
የስኳር በሽታ፣ የልብ ችግር፣ የኩላሊት ወይም ጉበት በሽታ ያለባቸው ሰዎች እና ነፍሰ ጡር/እርጉዝ ሴቶች ለዚህ ችግር በይበልጥ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የእግር እብጠትን ለመቀነስ ይረዳሉና ይተቀሙባቸው፦
1. የውሃ ፈውስ/Hydrotherapy
ይህ አይነቱ የውሃ ህክምና ቀዝቃዛና ሙቅ ውሃን የሚያካትት ሲሆን በእግርዎ ላይ ያለውን እብጠት በመቀነስ ስኬታማ ነው፡፡ ሙቅ ውሃው የደም ዝውውር እንዲጨምር ሲረዳ ቀዝቃዛ ውሃ ደግሞ እብጠትና መቅላት እንዲቀንስ ይረዳል፡፡
• በሁለት እቃዎች፦ በአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ በሌላኛው ደግሞ ሙቅ ውሃ ይሙሉት፡፡
• እግርዎን ከ3-4 ደቂቃ በሙቅ ውሃ ውስጥ ይንከሩት
• በፍጥነት እግርዎን ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ለ1 ደቂቃ ይንከሩት፡፡
• ይህን ሂደት በማቀያየር ከ15-20 ደቂቃ ይደጋግሙት
• እስኪሻልዎት በቀን ለጥቂት ጊዜ ይደጋግሙት
2. መታሸት/Massage
እግርን መታሸት(ማሳጅ) ለእግር እብጠት በጣም ፍቱን ከሆኑት ዘዴዎች አንዱ ነው፡፡ በተጎዳው አካባቢ ግፊት በመፍጠር የተጎዱ ጡንቻዎች ዘና እንዲሉ በማድረግ እና የደም ዝውውር እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ትርፍ ፈሳሾች እንዲወገዱ የሚደረገውን ሂደት ያበረታታል፡፡
• እግርዎን ትንሽ ሞቅ ያለ የኦሊቭ ዘይት ይቀቡት
• ለ 5 ደቂቃ በቀስታ ወደ ላይ አቅጣጫ ይሹት(ወደ ታች አቅጣጫ መታሸት የለበትም)፡፡ በጣም ተጭነው እንዳያሹት ይጠንቀቁ፡፡
• በቀን ለብዙ ጊዜ ይህን ያድርጉት
ሻወር እየወሰዱ ወይም ከሻወር በኋላ ቢያሹት በጣም ውጤታማ ይሆናል፡፡ እብጠቱ በእርግዝና ምክንያት የተከሰተ ከሆነ ሃኪምዎን ያማክሩ፡፡
3. ጨው
ጨው በፍጥነት እብጠትን የመቀነስ እና ህመምን የማስታገስ ባህሪ አለው፡፡ በጨው ውስጥ የሚገኝው ማግኒዚየም ሰልፌት በቀላሉ በቆዳ ውስጥ ሰርጎ በመግባት የደም ዝውውርን በመጨመር እና እብጠትን በመቀነስ ይረዳል፡፡ በተጨማሪ የተጎዳ እና የደከመን ጡንቻ ዘና ያደርጋል፤ የእግርን ሽታ በመቀነስ ይረፋል፡፡
• ግማሽ ኩባያ ጨው ለብ ባለ ውሃ ጋር ይቀላቅሉት
• ያበጠውን እግር ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ይንከሩት/ይዘፍዝፉት
• ይህን ሂደት በሳምንት 3 ጊዜ ይደጋግሙት
4. ዝንጅብል/Ginger
ዝንጅብል ተፈጥሮአዊ የእግር እብጠት ፍቱን ህክምና ነው፡፡ ከእግር እብጠት ጀርባ ያለውን ሶዲየም(Sodium) በማቅጠን(Dilute) ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በተጨማሪም የዝንጅብል ፀረ-ኢንፍላሜሽን ባህሪ እብጠቱ እንዲቀንስ ይረዳል፡፡
• ያበጠውን እግር በዝንጅብል ዘይት ማሸት ወይም
• ከ2-3 ብርጭቆ የዝንጅብል ሻይ ይጠጡ ወይም ጥሬ ዝንጅብል ያኝኩ
5. የሎሚ ውሃ
የሎሚ ውሃ መጠጣት ትርፍ ፈሳሽ እና መርዛማ ነገሮች ከሰውነታችን እንዲወገዱ በማድረግ የእግር እብጠትን እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ያሉ እብጠቶችን ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪ ሰውነታችን የፈሳሽ እጥረት እንዳያጋጥመው ይከላከላል፡፡
• በአንድ ኩባያ ሙቅ ውሃ ውስጥ ሁለት ማንኪያ የሎሚ ጭማቂ ይቀላቅሉበት
• ትንሽ የተፈጥሮ ማር በመጨመር ያጣፍጡት
• ያዘጋጁትን የሎሚ ውሃ በቀን ለጥቂት ጊዜ ይጠጡት፡፡

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement