የራስ ምታት ስሜቶችና መከላከያ መንገዶች

                                                       

ራስ ምታት በአብዛኛው የተለመደና በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአብዛኛው ራሱን የቻለ ህመም ሳይሆን ምልክት መሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያዎች፥ በጤና እክል ምክንያት ከሚፈጠር የህመም ስሜት ጋር ተያይዞ ራስ ምታት ሊከሰት እንደሚችልም ነው የሚናገሩት።

በሰውነት ህዋሳት ውስጥ፣ በደም ቧምቧዎች፣ ነርቭና በሰውነት ውስጥ ያሉ ኬሚካሎችም በዚህ ጊዜ የሚከሰት የራስ ምታት ስሜት እንዲሰማን ሊያደርጉ ይችላሉም ነው የሚሉት።

ከዚህ አንጻርም ራስ ምታትን እንደሚከሰትበት ሁኔታ በአግባቡ ማከምና ማስታገስ እንደሚቻልም ያነሳሉ።

ባለሙያዎቹ ስድስት አይነት ራስ ምታቶችን መንስኤና ማከሚያ መንገዶችን ይጠቁማሉ፤

መድሃኒት አብዝቶ በመጠቀም ሳቢያ የሚከሰት፦ ይህ አይነቱ ራስ ምታት መነሻው ለፈውስ በሚውል የሚወሰዱ መድሃኒቶች በሚበዙበት ጊዜ ነው።

ይህ ስሜት በጣም ከባድና ምናልባትም ከሳምንት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሊቆይ የሚችል ከበድ ያለ ራስ ምታት ነው።

ስሜቱ የሚቆመውም ለህመሙ ምክንያት የሆነውን በርካታ መጠን ያለው መድሃኒት መውሰድ ሲያቆሙ ብቻ ነው።

ከዚህ ባለፈ ግን ሃኪም ማማከርና መፍትሄ ይሆናል ያሉትን አማራጭ በራስዎ እንዲወስዱ አይመከርም።

ከአፍንጫ ጋር በሚከሰት ችግር ሳቢያ የሚከሰት ራስ ምታት፦ ይህ ደግሞ የመተንፈሻ በተለይም አፍንጫ አካባቢ በሚከሰት እክል ሳቢያ የሚፈጠር ራስ ምታት ነው።

የፊት አካባቢ መክበድ ስሜት፣ ከባድ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ህመምና የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት በዚህ ጊዜ የሚከሰቱ ምልቶች ናቸው።

ይህ አይነቱ ራስ ምታት በተለይም ቀዝቃዛ አየር በሚኖርበት ወቅት ሊከሰት የሚችል ሲሆን፥ ወዲያውኑ ማከምና ስሜቱን ማጥፋት አይቻልም።

ከዚያ ይልቅ በአለርጅና ተያያዥ ምክንያቶች የሚከሰተውን ሳይነስና የአፍንጫ መደፈን፥ የጉንፋን ስሜቱን ማከምና ማስወገድን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ከመጨናነቅ የሚመጣ ራስ ምታት፦ ጭንቅላትን ወጥሮ የመያዝና የማስጨነቅ ስሜት በተለይም በኋለኛው የጭንቅላት ክፍልና አንገት አካባቢ የዚህ ራስ ምታት ምልክቶች ናቸው።

ከጭንቀት፣ ፍርሃት፣ ጫና፣ በጭንቅላት ውስጥ በሚፈጠር የኬሚካል ለውጥ ሳቢያ አንገት አካባቢ የሚፈጠር ጫና፣ የጡንቻ መኮማተርና አንገት አካባቢ ያዝ የማድረግ ስሜት ይከሰታል።

ይህ ስሜት ምናልባት ቶሎ መፍትሄ ካልተሰጠው በእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እክል ሊፈጥር ይችላል።

ራስን ከጫና ማላቀቅና ማረጋጋት ከዚህ ባለፈም ጉዳዩን ለሃኪም በማማከር የሚታዘዝልዎትን መድሃኒት በአግባቡ መጠቀም ይመከራል።

በአንድ ጎን የሚከሰት ራስ ምታት፦ ይህ ራስ ምታት ምናልባትም በተደጋጋሚ በየቀኑ አልያም በየሳምንቱ ጊዜ እየጠበቀ ሊከሰት የሚችል መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ይህ አይነቱ ራስ ምታተ ሲከሰት የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛትና ከበድ ያለ ስሜት ይከሰታል፤ ከዚህ ባለፈም ስሜቱ ባለበት የአይን ክፍል ላይ ጫን የማለት ስሜትም የዚህ ራስ ምታት ሌላው ምልክት ነው።

በዚህ ጊዜ አብዝቶ ማስጨነቅና አይንዎ አካባቢ ጫና መፍጠርም ከራስ ምታት ስሜቱ ጋር ተያይዞ የሚሰት ስሜት ነው።

አጫሽ ከሆኑ አለማጨስና መጠጥ ማቆም፥ ከዚህ ባለፈም የኦክስጅን ቴራፒን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በጥርስ ህመም ሳቢያ የሚከሰት ራስ ምታት፦ ይህ ደግሞ በጥርስና አገጭ አካባቢ ከሚያጋጥም ችግር ጋር ተያይዞ የሚከሰት የራስ ምታት ነው።

የጥርስ ማፋጨትና አገጭ አካባቢ የሚከሰት ህመም ራስ ምታቱ እንዲባባስ ያደርገዋል።

ከዚህ ባለፈም ከበድ ያለ የፊት አካባቢ ህመምም ይከሰታል።

የአገጭና መንጋጋ አካባቢ መናጋት፣ ያልተስተካከለ አቀማመጥ፣ የመገጣጠሚያ አካባቢ ህመምና ጭንቀት ለራስ ምታቱ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ።

አለመጨናነቅና ባለሙያ ማማከር ደግሞ የመፍትሄ ሃሳቦች ናቸው።

ማይግሬይን (ከፍተኛ ራስ ምታት)፦ ይህ ደግሞ ከፍተኛና የባሰው ራስ ምታት ሲሆን ህመሙን ተከትሎ ማስመለስና ሌሎች ስሜቶች ሊከሰቱም ይችላሉ።

ባለሙያዎች ምናልባትም በዘር ሊተላለፍ ይችላል የሚሉት ይህ ህመም ረዘም ያለ ጊዜ ሊቆይ የሚችልና ስሜቱም ከበድ ያለ ነው።

የህክምና ባለሙያዎችም ለዚህ ህመም ትክክለኛ መንስኤ ያሉትን መለየት ባይችሉም ሃኪም ማማከር ግን ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement