የፍቅር ግንኙነትዎን በዚህ መልኩ ቢያጠነክሩስ?

መተማመን፣ ግልጽነት፣ መነጋገር እና መተሳሰብ በፍቅር ህይዎት ውስጥ ወሳኝ እና ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

እነዚህ ነገሮች ጥንዶች በፍቅር ህይዎታቸው ረዘም ያለ ጊዜን በአብሮነት እንዲያሳልፉ ያግዟቸዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን ፍቅርን ለማጠንከርና በጠንካራ ፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ለማድረግ ከምስጋና ጀምሮ ጥንዶች የሚሄዱባቸው መንገዶች ወሳኝነት አላቸው።

ፍቅርን ለማጠንከርና ቆይታን ለማዝለቅ ደግሞ ጥንዶች እነዚህን መንገዶች ቢጠቀሙ መልካም መሆኑን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ፤

ማመስገን፦ ዘወትር የፍቅር አጋርዎ ላደረገው ነገር ማመስገንና በሰራው ስራ እርሰዎ ደስተኛ እንደሆኑ መንገር መልካም መሆኑን ይመክራሉ።
ያንን ማድረጉ የእነርሱ ሃላፊነትና ግዴታ ነው ብለው ቢያስቡም እንኳን ለሰሩት ስራና ላደረጉት ነገር ማመስገኑ ጠንካራ የፍቅር ግንኙነትን ለመመስረትና ቆይታን ለማጠንከር ይረዳል።

ይህን ማድረጉ የፍቅር አጋርዎ ጥሩና መልካም ስሜት እንዲሰማው በማድረግ ቆይታችሁን ያራዝማል።

በአትኩሮት ማዳመጥ፦ ዘወትር የፍቅር አጋርዎ ስለሚያነሳው ነገር መስማትና ማዳመጥ ለፍቅራችሁ ዘለቄታ ወሳኝነት ያለው ጉዳይ ነው።

ምናልባት ንግግሩን ባይረዱትም እንኳን ለማዳመጥ መሞከሩ ተቀባይነት እንዳለው ማሳያ ነውና ለግንኙነት መልካም ነገር ነው።

ማዳመጥ ከአጋርዎ ጋር ያለዎትን ቁርኝትና ጥብቅ ግንኙነት ለማጠንከር ወሳኙ ነገር እንደሆነም ያስቡ።

ቤት ከስራ ውለው እንደገቡ የአጋርዎን ውሎና የስራ ሁኔታ እንዴት እንዳለፈ መጠየቅና በውሎው ስለተሰማው ስሜትና መሰል ጉዳዮች እየጠየቁ ማዋራትም ይልመዱ።

ከዚህ በኋላ ምናልባት እነርሱ መልስ ሳይሰጡዎት ወደ ስራ ከመግባትና ወደ ሌላ ጉዳይ ከመሄድዎ በፊት ሃሳባቸውን ማስጨረስና ማዳመጥም አይዘንጉ።

ዘወትር ከእነርሱ ጋር ሲነጋገሩም ለእነርሱ በሚጠቅምና በሚበጅ ጉዳይ ላይ ቢወያየዩ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል።

ስሜትን መጋራት፦ ምንም ቢሆን የእነርሱን ስሜት መጋራት እና ያነሱትን ሃሳብ በቁም ነገር ወስዶ መወያየትም መልካም ነው።

ምናልባት እየተወያያችሁ መሃል ላይ ንግግሩን መረዳት ካቃተዎት በድጋሚ መስማት እንደሚፈልጉ በመንገር ጉዳዩን ከልብ በሆነ ሁኔታ በመስማት መወያየት ይኖርብዎታል።

ያንን ሲያደርጉ ለአጋርዎ ያለዎትን ስሜትና ምን ያክል እንደሚፈልጉትም ማሳያ ይሆናልና ይተግብሩት።

ስሜትን መግታትና መቆጣጠር፦ አንዳንድ ነገሮችና ውይይቶች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ምናልባትም ወደግጭት ሊመሩ ይችላሉ።

ይሁን እንጅ መሰል አጋጣሚዎችን ተንተርሰው አላስፈላጊ ስሜት ውስጥ ከመግባት ስሜትዎን ገዝተውና ተቆጣጥረው ነገሮችን ማብረድ ይጠበቅብዎታል።

ነገሮችን በሰከነ መንፈስ ማዳመጥና ከስሜት በመውጣት ለመነጋገር መሞከር እና መወያየቱም መልካም ነውና ይጠቀሙበት።

ጊዜ አብሮ ማሳለፍ፦ ይህን ማድረጉ ደግሞ ጠንካራ እና ጥብቅ ቁርኝትን ለመፍጠርና ጠንካራ የሆነ መግባባት ይኖር ዘንድም ያስችላል።

በዚህ መልኩ ጊዜ አብሮ ማሳለፍ ሲደጋገም ደግሞ ለጽኑ እና ጠንካራ ወዳጅነትም ሆነ ለዘላቂ የአብሮነት ቆይታ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አለው።

ከዚህ ባለፈ ግን ከአጋርዎ ጋር ዘና የሚያደርጉ የቃላት ጨዋታዎችን መጫወትና የቀልድ ስሜት ያላቸውን ጨዋታዎች መጫዎትም ይመከራል።

በቁም ነገር ብቻ የምታሳልፉትን ጊዜ በዚህ መልኩ አልፎ አልፎ ማሳለፍዎ ከአጋርዎ ጋር በተለየ መንገድ ለመግባባትና ለመተዋወቅም ይረዳል።

እናም የቻሉትን ያክል ከፍቅር አልያም ከትዳር አጋርዎ ጋር መሰል ልማዶችን በመደጋገም መልካምና ጣፋጭ የፍቅርና የትዳር ጊዜ እንዲኖርዎት ማድረግ ይችላሉ።

ምንጭ፦ psychologytoday.com

Advertisement