ታሪክን ትጥቅ ማስፈታት

 

ትውስታና ተስፋ ያለው ምድራ ፍጡር ሰው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክና ዕቅድ አለው፡፡ የሰው ልጅ ጥንታዊ ጥያቄ የሚባለው ‹ከየት መጣሁ› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ስለ ትናንት ለማወቅ ጉጉታቸው የጨመረውና ትናንታቸውን መፈልፈል የፈለጉት ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ ነበር፡፡ ታሪክ ያለው የሰው ልጅ ብቻ ስለሆነ፡፡ 
የታሪክ አንዱ ጠባዩ ድርጊቱ የተጠናቀቀ፣ ጣጣው ያላለቀ መሆኑ ነው፡፡ የታሪክ ሂደት ከጊዜ ጋር የተሠናሰለ በመሆኑ ድጊቱ ተከናውኖ ይጠናቀቃል፡፡ የድርጊቱ ተጽዕኖ ግን ሺ ዓመታትን እስከመሻገር ይደርሳል፡፡ ተጽዕኖው እንዳይቋረጥ የሚያደርጉት ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው አዳዲስ መረጃዎችና ማስረጃዎች ስለሚገኙ የነበረውን ትረካ ይቀይሩታል፤ ሁለተኛ ደግሞ ቀድሞ ለተደረገ ድርጊት አዳዲስ ምልከታዎችና ትርጉሞች ይሰጡታል፡፡ ‹ለምን እንዲህ ሆነ? እንዲህ መሆን አልነበረበትም፤ እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነበር› የሚሉ አእላፍ ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡
ከትናንቱ ከመማርና ወደፊት ከመስፈንጠር ይልቅ ‹እህህ› እያሉ በትናንቱ የሚቆዝሙት ‹የታሪክ እሥረኞች - prisnores of history› ይባላሉ፡፡ የማንኛውም ነገር መበየኛቸው ትናንት ነው፡፡ ያ አካል ዛሬ ቢሻሻል፣ ቢቀየር፣ ግድ የላቸውም፡፡ ትናንት ያንን የፈጸሙት ሰዎች ቢኖሩ፣ ባይኖሩ ቁብ አይሰጣቸውም፡፡ በጥፋት ውኃ በጠፉ ሰብአ ትካት ላይ ቂም ይይዛሉ፡፡ 
ብዙ ጊዜ ታሪክ ጠቀስ ጠብ የሚፈጠረው በድርጊቱ ምክንያት ሳይሆን ለድርጊቱ በሚሰጠው አሁናዊ ትርጓሜ ነው፡፡ ከዘመናት በፊት የተፈጠሩ ድርጊቶችን አንሥተው ሀገሮች ጦርነት ገጥመዋል፡፡ ጎሳዎች ተጋጭተዋል፤ ማኅበረሰቦች ተለያይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ብዙዎቹ በድርጊቱ የተሳተፉት አንድም የሉም፣ አለያም ጨርሰው ማንነታቸው አይታወቅም፡፡ ወንጀል ግለሰባዊ ነው፡፡ ሰዎች ተመካክረውና ወስነው ቢፈጽሙት እንኳን በየራሳቸው የነበራቸው ድርሻ ወሳኝ ነው፡፡ ታሪክን ለአሁን የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም የሚፈልጉ አካላት ግን የወንጀልን ግለሰባዊ ባሕሪይ በመካድ ማኅበራዊ ባሕሪይ ያላብሱታል፡፡ እንደ ተቋምም ካየን መንግሥታት በሕግ ሀገራትንና ሕዝቦችን ይወክላሉ እንጂ ተተኪ ትውልድ የቀደመውን አይወክልም፡፡ ሀገሮችና ሕዝቦች የፈጸሟቸው ነገሮች አሉ ከተባሉም መንግሥታት ወይም የሕዝቡ መሪ የነበረው አካል ታሪካዊ ወይም መዋቅራዊ ወራሽ ነው የሚቀበላቸው፡፡ 
ታሪክን እንዲህ ካለው መከራ የሚያድነው እርሱን ራሱን ትጥቅ ማስፈታት ነው (disarmament of history)፡፡ ታሪክ የመማማሪያ፣ ከትናንት የተሻለ ዓለም ለመገንባት የመነሻ መሠረት፣ መልካሙን የማስቀጠያ፣ ክፉውን የማረሚያ መንገድ ስናደርገው ትጥቅ እናስፈታዋለን፡፡ ታሪክን መሣሪያ አስነግቶ ለመታኮሻ፣ ሆድ ለማባባሻ፣ ለማተራመሻ፣ ለጠብ መቆስቆሻ፣ ለእሳት መለኮሻ፣ ለቁስል መቀስቀሻ መጠቀም የጠላነውን ታሪካዊ ክሥተት እንደገና መድገም ነው፡፡ ይህ ከሆነ ታሪክ ቦንብና ፈንጅ፣ መትረጊስና ላውንቸር፣ ታንክና ኒውክሌር ታጥቋል ማለት ነው፡፡ 
በተረቶቻችን ውስጥ አያሌ አስደንጋጭ፣ አሳዛኝ፣ አስፈሪና አሰቃቂ ድርጊቶች አሉ፡፡ እነዚያን ተረቶች እንድንሰማቸው የሚያደርገን በሚተረቱበት ዓላማ ምክንያት ነው፡፡ የተረቱ ሞራላዊ ፋይዳ በጎ በመሆኑ፡፡ ታሪክንም ለተሻለ ሞራላዊ ፋይዳ ካልተጠቀምንበት ያታኩሰናል፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰን ለመቀየር አንዳች ዐቅም ሆነ ዕድል በሌለን ድርጊት መነሻነት ዛሬያችንንና ነጋችንን እንድናበላሽ ያደርገናል፡፡ ታሪካችን ትጥቅ ይፍታ፡፡ ሌጣውን ታሪክ እንማርበት፣ እንገረምበት፣ እንናደድበት፣ እንደሰትበት፣ እንቆጭበት፣ እንወያይበት፣ እንከራከርበት፡፡ ታሪክ ባለ ትጥቅ ከሆነ ውይይትና ክርክር፣ መተራረምና መማማር ፈጽሞ አይኖርም፡፡ እየተታኮሱ ትምህርትም፣ ውይይትም፣ ክርክርም የለምና፡፡ 
ታሪካችን ትጥቅ ይፍታ፡፡

ምንጭ: የዳንኤል ክብረት እይታዎች ፌስቡክ ድህ-ረገፅ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.