አሁን የማድረግ አንገብጋቢነት

“The fierce urgency of now” በ1963 በአሜሪካ የሰብአዊ መብቶችን መከበር በተመለከተ ማርቲን ሉተር ኪንግ ያነሣው ሐሳብ ነበር፡፡ ነገሮችን ይዋሉ ይደሩ ሳይሉ አሁን የማድረግ አንገብጋቢነት፡፡ ይቆይ ይሰንብት አንበል፤ የመሥሪያ ቀን ዛሬ ነው፡፡ እኛ የዛሬ እንጂ የነገ አይደለንም፡፡ እኛ ‹ነገ› ስንል የምናስረዝመው የብዙዎችን ስቃይና መከራ ነው፡፡ ዛሬ መሥራት ያለብንን ባለመሥራታችን የሚጎዱት አያሌ ናቸው፡፡ ስለዚህም ‹አሁኑኑ እንሥራ›፡፡ ነገሮችን አሁን የማድረግ አንገብጋቢነት፡፡ 
‹ምነው ተንቀዠቀዥክ›፣ ‹አትቸኩል ይደርሳል›፣ ‹ምን ያጣድፍሃል›፣ ‹ተረጋጋ ጎበዝ›፣ የሚሉ ምላሾች በየቢሮ እንሰማለን፡፡ ‹እየተመላለስክ ጠይቅ›፣ ‹ከጥቂት ቀናት በኋላ ብቅ በል› እንባላለን፡፡ ዛሬን ለመቅጠሪያ እንጂ ለመሥሪያ የማይጠቀሙ ሰዎች አሉ፡፡ ሥራን ወደ ነገ ማሸሽ ማለት ወርቅን ጥልቀቱን በማታውቀው ጉድጓድ ውስጥ እንደ ማስቀመጥ ነው፡፡ 
ነገን የተሳካና የተቃና ማድረግ የሚቻለው የአሁንን አንገብጋቢነት በሚገባ ለመረዳት ከተቻለ ነው፡፡ ትናንት የተበላ ዕቁብ ነው፡፡ ነገ የሚጠበቅ ገቢ፡፡ ‹አሁን› ማለት ግን በእጅ ላይ ያለ፣ ግብር የተቆረጠለት፣ ኪራይ የተከፈለለት፣ ዕቁብ የተጣለለት፣ ዕዳ የተቀነሰለት፣ ንጹሕ ገንዘብ ነው፡፡ የተጣራ ገቢ፡፡ መሥራት እጅህ ላይ ባለውና ባረጋገጥከው ገንዘብ ነው፡፡ አሁን የመሥራት አንገብጋቢነት የሚመጣው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በሀገራችን ‹የመብል የነገ ያገለግላል፣ የሥራ የነገ ያጀለጅላል› የሚል አባባል አለ፡፡ ገበሬው ስለ ሥራና ስለመብል ያለውን አመለካከት የገለጠበት ነው፡፡ ክፉ አጋጣሚ ማለት አሁናችንን የሚያበላሽብን አጋጣሚ ነው፡፡ ገበሬው ይሄንን ያውቃል፡፡ እያንዳንዱ ጊዜ ለእርሱ ወሳኝ ነው፡፡ በእርሻው ወቅት አያጭድም፣ በአጨዳ ወቅት አይከምርም በመከመሪያው ወቅት አይወቃም፣ በመውቂያው ወቅት ጎተራ አያስገባም፡፡ ድንገቴ ዝናብ፣ እንደ መዓት የወረደ ኩብኩባ፣ ሀገር የሚነቅል ተምች፣ ሕይወቱን ሊያበላሽበት እንደሚችል ያውቃል፡፡ ለዚህ ሁሉ መፍትሔው ተገቢውን ሥራ በተገቢው ጊዜ መሥራት ብቻ ነው፡፡ የአሁንን አንገብጋቢነት መረዳት፡፡ 
ያ ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ የተገኘ ጤናና ጉልበት ነገ ላይገኝ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ ብራ፣ እንዲህ ያለ ነፋስ፣ እንዲህ ያለ ዝናብ፣ እንዲህ ያለ የበሬ ጉልበት ነገ ስለመገኘቱ ርግጠኛ አይደለም፡፡ የተሻለው አሁን ግጥም አድርጎ መሥራት ነው፡፡ ‹ገሥግሦ የመጣን ደኅና አድርገህ ጫነው› የሚባለውኮ ለዚህ ነው፡፡ አንተ ከቀኑ ፀሐይ ጋር እየተፎካከርክ ደፋ ቀና ስትል ያገኘኸውን አጋዥ በወሬ አትጥመደው፣ በይሉኝታ አትሸኘው፡፡ ይልቅ አግዘኝ በለውና የዛሬውን ዛሬ ሥራው፡፡
መዝገብ ከምረን፣ ደብዳቤ በትነን፣ ነገ እንሠራዋለን ብለን ከቢሮ እንወጣለን፡፡ ልቅሶ፣ ሕመም፣ አደጋ፣ መርዶ፣ ስብሰባ፣ ዝውውር፣ ስንብት፣ ይገጥመንና ወይ እንደወጣን እንቀራለን፤ አለያም ከርመን ሰንብተን እንመለሳለን፡፡ ነገ ሄዶ፣ ብዙ ነገዎች ነጉደው እንደርሳለን፡፡ ‹ሞሰብ ሰፍቼ፣ ለአጤ አበርክቼ. ብለን መኖር ከለመድን ብዙ ዛሬዎችን እንዲህ አድርገን እናባክናቸዋለን፡፡ አሁን የመሥራትን አንገብጋቢነት መረዳት ከዚህ ሁሉ ነው የሚያድነን፡፡ አንዳንዴ የቀኑ ፍጻሜ የኛም ፍጻሜ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ 
በትግርኛ አንድ አባባል አለ ‹መነ ይሥረሐያ? አነ፤ መዓስ? ኸዚ – ማን ይሥራው? እኔ፤ መቼ? አሁን› የሚል፡፡ ነገርን ወደ እገሌና ወደ ነገ ማሻገርን የሚኮንን አባባል ነው፡፡ ሥራን ከራስ የማራቂያ አንዱ መንገድ ‹እገሌ ይሥራው› ብሎ ማስተላለፍ ነው፡፡ ሌላው መንገድ ደግሞ ‹ነገ› ብሎ መገላገል፡፡ የሥራ ትክክለኛው መፍትሔ ግን ‹እኔና አሁን› ናቸው፡፡ ‹የእነ እገሌ ኃላፊነት ነው፣ የእነርሱ ግዴታ ነው፣ የእነርሱ ሥራ ነው› እያሉ ኃላፊነት የሚሸከም ፍለጋ የሚዞሩ ሰዎች ጥሩ ጠቋሚዎች እንጂ ጥሩ ሠሪዎች አይሆኑም፡፡ በየስብሰባችን እንዲህ ያሉ ሰዎች ሞልተዋል፡፡ ተሽቀዳድመው ሰዎችን ጠቁመው በማስገባት ራሳቸውን ከኃላፊነት የሚያርቁ፡፡ በተለይ ሥራው አድካሚ ከሆነ፡፡
የማርቲን ሉተር ኪንግን the fierce urgency of now የተረዱት ታላላቆቻችን ናቸው ‹መዓስ? ኸዚ፤ ያሉት፡፡ መቼ? አሁን፡፡ ለማታውቀው ሰው ገንዘብህን እንደማትሰጠው ሁሉ ለማታውቀው ነገ ዕጣ ፈንታህን አትስጠው፡፡ የምታውቀውና የምታምነው ወዳጅህ ‹አሁን› ነው፡፡ እንደ ወጡ የቀሩትን፣ መጣሁ ብለው ወጥተው በመኪና አደጋ የተቀጩትን፣ ያላሰቡበት ጠብ ውስጥ ገብተው ፖሊስ ጣቢያ ያደሩትን፣ ድንገት ወድቀው ሆስፒታል ተኝተው የከረሙትን፤ ስታይ ‹አሁን የማድረግ አንገብጋቢነትን› ካልተረዳኸው፣ አንተ የነገ ተስፈኛ ሳትሆን የነገ ምርኮኛ ነህ፡፡ ከማታውቀው ሰው ፍቅር ይዞህ መከራህን የምታይ፡፡
ምን ያህል ገንዘብና ዕውቀት፣ ሥልጣንና ተሰሚነት ቢኖርህ ከአሁን ውጭ ልታደርጋቸው የማትችላቸው ነገሮችም አሉ፡፡ ልጅ ሆነህ የተጫወትካቸውን፣ ከማግባትህ በፊት ያደረግካቸውን፣ ከመውለድህ በፊት የኖርክባቸውን፣ ወላጆችህ በሕይወት እያሉ ያሳለፍካቸውን፣ ሮጠህ በማይደክምህ ጊዜ የፈጸምካቸውን፣ ሙሉ ጤና እያለህ የከወንካቸውን እስኪ አስታውሳቸው፡፡ እንዴት አድርገህ ትደግማቸዋለህ? አንዳንዶቹ አልፈዋል፤ ሌሎቹ ተፈልገው አይገኙም፤ ሌሎቹም ቢያምሩህም አያምሩብህም፡፡ ያኔ ‹አሁን የማድረግን አንገብጋቢነት› ብትረዳው ኖሮ ….፡፡ ፀፀት የሚመነጨው አሁን የማድረግ አንገብጋቢነትን ካልተረዳ ልብ ነው፡፡

ለመሆኑ አሁን ምን እያደረግክ ነው?

ምንጭ: የዳንኤል ክብረት እይታዎች ፌስቡክ ድህ-ረገፅ

Advertisement

95 Comments

  1. [url=https://trentalgen.com/]trental 400 mg tablets in india[/url] [url=https://ciprofloxacinrx.com/]ciprofloxacin sale online[/url] [url=https://viagrarem.com/]viagra 50 mg tablet online purchase[/url] [url=https://albenzarx.com/]albendazole medicine price[/url] [url=https://propranololtab.com/]propranolol purchase online[/url] [url=https://tadalafil.us.org/]tadalafil 5mg daily use[/url] [url=https://tadalafilxr.com/]tadalafil canada online pharmacy[/url]

Comments are closed.