የዲስክ መንሸራተት

የጀርባ አጥንት ቨርተብሬ የሚባሉ የ26 አጥንቶች ስብስብ ነው። ዲስክ በቨርተብሬዎች መሃከል የሚገኙ ርብራብ መሰል ክፍሎች ናቸው ። እነዚህ ዲስኮች የጀርባ አጥንትን ባለበት ደግፈው ይይዛሉ። ሰውነት ከባድ ሃይል ሲያስተናግድ ሃይሉን የሚያምቁ ክፍሎች ናቸው።
ዲስክ ጠንካራ ሽፋን ያለው ሲሆን በውስጡ ግን ለስላሳ የሆነ ፈሳሽ ነው። የዲስክ መንሸራተት የሚባለው በዲስክ ግድግዳ ላይ የሚፈጠር ቀዳዳ ምክንያት የሚፈጠር የውስጥ ፈሳሽ መውጣት እንዲሁም ዲስክ ወደፊት ወይም ወደኃላ አሊያም ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ በኩል ቦታዉን ለቆ በሚንሸራተትበት ወቅት የሚመጣ ነዉ፡፡ይህ ችግር ከአንገት ጀምሮ በየትኛውም የህብለሰረሰር ክፍል ላይ የሚከሰት ነው፡፡
 የዲስክ መንሸራተት መንስኤ
– የዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ በዲስኮች ላይ መኖር የሚገባው ፈሳሽ መቀነስ
– የሰውነት ክብደት ከመጠን በላይ መሆን
– በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን አለማድረግ
– ከበድ ያሉ ስራዎችን መስራት
– በተደጋጋሚ መጠምዘዝ
– ለረጅም ሰአታት መቀመጥ
– በተደጋጋሚ ከባድ ነገር ማንሳት፣ መጎተት፣ መግፋት
 የህመሙ ምልክቶች

ስለመከሰቱ ምንም አይነት የህመም ምልክቶች ሳይኖር የዲስክ መንሸራተት ሊኖር ይችላል፡፡ ዲስኩ የነካው ነርቭ ከሌለ የህመም ስሜት አይሰማንም።
– የጀርባ አካባቢ ህመም ለረጅም ጊዜያት የሚቀጥል ከሆነ
– የእጅ/የእግር ላይ ህመም፡-
የዲስክ መንሸራተት የተከሰተው በታችኛዉ የጀርባ አጥንቶች አካባቢ ከሆነ ከፍተኛ ህመም በመቀመጫ፣ በጭንና በባት አካባቢ እንዲሁም መርገጫ/የእግር መዳፉ ላይ ሊሰማ ይችላል፡፡
የዲስክ መንሸራተት የተከሰተው አንገት ላይ ከሆነ ህመሙ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰማው በትከሻና በእጅ ላይ ነዉ፡፡ ሕመሙ በሚያስሉበት፣ በሚያስነጥሱበት ወቅት ወይም ወደ ተወሰነ አቅጣጫ የጀርባ አጥንቶች በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት ሊባባስ ይችላል፡፡
– የመደንዘዝ ወይም የመጠቅጠቅ ስሜት
-የእጅ/ እግር መስነፍ፡- በዲስክ መንሸራተት ምክንያት የተጎዳ ነርቭ ካለ ያ የተጎዳዉ ነርቭ እንዲሰራ የሚያደርገዉ ጡንቻ ሊደክም ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳ መራመድ መቸገር፣እቃ ማንሳት ወይም መያዝ ያለመቻል ሊከሰት ይችላል፡፡
– በጣም ያልተለመደ ቢሆንም በዲስክ መንሸራተት ምክንያት ከዳሌ በታች ያለው የነርቭ ክምችት ሊጨማደድ ይችላል። ይህ ሲሆን በዘላቂነት የሚቆይ የድካም ስሜት፣ የሽንት እና ሰገራ መቆጣጠር ብቃት መዳከም እና ስንፈተ-ወሲብ ይፈጠራል።

 ህክምና
-ቀላል የሚባል የዲስክ መንሸራተት የሚያጋጥማቸው አብዛኞች ሰዎች በተወሰኑ ቀናት እስከ 4 ሳምንት ውስጥ ያገግማሉ።
-እረፍት በማድረግ ፣ የህመም ስሜት ከሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች በመቆጠብ እና የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ እንዲሁም የህመም መድሃኒቶችን በመውሰድ ህመሙን ማስታገስ እንችላለን።
-ከባድ የጀርባ ህመም አይነት እንደ ህመሙ አይነት የተለያዩ ህክምናዎች የሚሰጡ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ፡-
 መድሃኒቶች
– የህመም ማስታገሻ ክኒኖች፣የነርቭ መድሃኒቶች፣ ናርኮቲክስ
– በኮርቲዞን መወጋት፡ ህመሙ የተፈጠረበት ቦታ ላይ ኮርቲዞን በቀጥታ መወጋት የህመም ስሜቱን ሊቀንስ ይችላል። ነገር ግን ይህንን መድሃኒት አዘውትሮ መወጋት ሌላ የጤና መዘዝ ሊያመጣ ይችላል፡፡
– Acupunctur /የደረቅ መርፌ ህክምና/
– የኢፒዱራል መርፌ(Epidural injections): ኢፒዱራል የተባለው የሰውነት አካል ላይ የሚደረግ መርፌ መወጋት ነው። መርፌው በውስጡ የተለያዩ ህመም ስሜትን የሚያስታግሱ መድሃኒቶች በውስጡ የያዘ ነው።
– ጡንቻ የሚያላሉ መድሃኒቶች፡ እነዚህ መድሃኒቶች የጡንቻ መሳሳብን ይቀንሳሉ። ነገር ግን የማዞር ስሜት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
 የሰውነት ቴራፒ ማድረግ ህመሙን ለመቀነስ ይረዳናል ።
 ቀዶ ጥገና ፡- ከላይ የተጠቀሱት ህክምናዎች ህመሙን ማስታገስ ካልቻሉ ቀዶ ጥገና ማድረግ ይመከራል።

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

2 Comments

Comments are closed.