የህንዶቹን አስራ አንድ አንበሶች ምን ገደላቸው?

በህንድ የሚገኙ የእንስሳት ጥበቃ ባለሙያዎች እንደገለጹት ባልተለመደ መልኩ በጉጅራት ግዛት ሞተው የተገኙትን 11 የእስያ አንበሶች የሞት ምክንያት እያጣሩ ነው።

የእስያ አንበሶች እ.አ.አ ከ2008 ጀምሮ በመጥፋት ስጋት ላይ ያሉ እንሰሳት ተብለው ነበር። በጉጅራት እንስሳት መጠበቂያ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስያ አንበሶች ይገኛሉ።

ነገር ግን ይህን ያክል ቁጥር ያላቸው አንበሶች በተመሳሳይ ሰአት መሞታቸው በእንስሳት መጠበቂያው ውስጥ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

እስካሁን ድረስ ለአንበሶቹ ሞት ምክንያት የሆነው ነገር ባይታወቅም፤ አንበሶቹ በመጠበቂያ ውስጥ የአደንና የማረፊያ ቦታ ለማግኘት በሚደርጉት ፍልሚያ ሳይሆን እንዳልቀረ ባለሙያዎቹ ገምተዋል።

የእንስሳት ጥበቃ ባለሙያው ጂኬ ሲንሃ እንደተናገረው ከሌላ አካባቢ የመጡ ሶስት አንበሶች መጠለያ ውስጥ የነበሩ ሶስት ደቦሎችን የገደሉ ሲሆን፤ የዚህ አይነት ባህሪ በአንበሶች ዘንድ የተለመደ ነው ብሏል።

የተቀሩት ስምንት አንበሶች ግን በምን ምክንያት እንደሞቱ የታወቀ ነገር የለም።

በህንዷ ጉጅራት ግዛት በሚገኘው የእንስሳት መጠበቂያ ውስጥ የሚኖሩት አንበሶች ከቦታው ጠባብነት የተነሳ የሚበሉትን ምግብም ሆነ መጠለያ ለማግኘት ከፍተኛ ትግል ማድረግ አለባቸው።

በእንስሳት መጠበቂያው ከሚኖሩ አንበሶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት የሚሞቱት በተፈጥሯዊ ምክንያት ሲሆን የተቀሩት 30 በመቶዎች ግን ተፈጥሯዊ ባልሆኑና ምክንያታቸው ባልታወቁ አጋጣሚዎች ይሞታሉ።

የአንበሶች አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ ከ15 እስከ 16 ዓመት ሲሆን፤ ከ10 ዓመት በኋላ ግን አድኖ የመብላትና የመንቀሳቀስ አቅም ስለማይኖራቸው በአንድ አካባቢ ተወስነው የእርጅና ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።

የእንስሳት ጥበቃ ባለሙያው ጂኬ ሲንሃ ሌላ መላ ምት አስቀምጧል። ለቢቢሲ እንደተናገረው ”ሲዲቪ” የተባለ በውሾች የተላለፍ ቫይረስ ሊሆን ይችላል አንበሶቹን የገደላቸው።

የእንስሳት መጠበቂያው በቂ ጥበቃ ስለማይደረግለት አንበሶች ወደ ሰዎች መኖሪያ የሚወጡ ሲሆን፤ ውሻዎችም ቢሆን ወደ ጥብቅ ክልሉ ይገባሉ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.