ናይጄሪያዊቷ የ15 ዓመት ታዳጊ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ቀልብ እየገዛች ነው

ተማሪዋ ቶሚሲን የኮምፒዩተር ሶፍትዌሮችን እና የስልክ መተግበሪያዎችን የመሥራት ጽኑ ፍላጎት አላት።

የዛሬ ሶስት ዓመት የጠፉ ልጆችን የሚጠቁም ”ማይ ሎኬተር” የተሰኘ የስልክ መተግበሪያ ፈጠረች።

በጉግል ፕለይ ስቶር የሚገኘው ይህ መተግበሪያ መጀመሪያ ከተጫነበት እ.ኤ.አ ከ2016 ጀምሮ ከአንድ ሺህ በላይ ጊዜ ሰዎች አውርደው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

“መተግበሪያው ከጉግል ካርታ ጋርም የሚያገናኝ ከመሆኑ በተጨማሪ አሁን ካላችሁበት ቦታ ጀምሮ ቀደም ሲል እስከመዘገባችሁት ቦታ ያለውን አቅጣጫ ያመላክታችኋል” በማለት አሁን 15 ዓመት የሞላት እና በናይጀሪያ ኢኬጃ ትምህርቷን የምትከታተለው ቶሚሲን መተግበሪያው እንዴት እንደሚሰራ ታብራራለች።

ፈጣን ምላሽ

“የማንቂያ ቁልፍ ወይም በተኑን ስትጫኑም ሌላ ተግባር አለው፡፡ የጽሁፍ መልዕክት ይልካል፤ የስልክ ጥሪም ያደርጋል። ይህ የሚሆነው እናንተ ላስቀመጣችሁለት የስልክ ቁጥር ቅንብር/ሴቲንግ ውስጥ ገብታችሁ እንዲሰራ ካስተካከላችሁት ነው።”

“የድንገተኛ ጊዜ መደወያ ወይም የቤተሰብ አባል ቁጥር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በዋናነት የእናንተ ምርጫ ነው። በመሆኑም በድንገተኛ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ስትፈልጉ አሁን ያላችሁበትን አድራሻ ላስተካከላችሁት ቁጥር ስለሚልክ ያ ሰው በቀላሉ ያላችሁበትን ማወቅ ይችላል።”

“የተለያዩ አደገኛ ሰዎች እንዳሉ ስለማስብ ስለደህንነት በጣም ንቁ ነበርኩ። እናም በሰላም መንቀሳቀስ ለመቻል ማሰቤ መተግበሪያውን እውን እንዳደርግ ያነሳሳኝ ይመስለኛል” በማለት ታብራራለች።

“ነገር ግን የእኔ የያኔዋ የ12 ዓመት ታዳጊ የራስ ሀሳብ ነበር። የሚገርም ነው፤ መተግበሪያ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ተማርኩ። እኔ የተማርኩትን ፈጠራ ለራሴም ሆነ ለሌሎች የሚጠቅም ነገር ለመስራት ብጠቀምበትስ? የሚል ሃሳብ መጣልኝ።”

በጉግል የፕሮግራም ሀላፊ የሆነው አኔዲ ኡዶ-ኦቦንግ እንደሚናገረው በዘርፉ የናይጀሪያውያን አርአያዎች ባለመኖራቸው የሀገሪቱ ሰዎች ኤለን መስክ እና ማርክ ዙከርበርግን ነው ምሳሌ የሚያደርጉት።

ነገር ግን ብዙ ተመራቂዎች ዘርፉን ኑሮን ለመምራት እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ለመመስረት ሁነኛ መድረክ አድርገው እየቆጠሩት ነው።

አኔዲ ጉግል ውስጥ ባለው ሀላፊነት ዘወትር በበርካታ ሀሳቦች የተሞሉ የስራ ፈጣሪዎችን ያገኛል። ስራው ዘርፉ በአፍሪካ እንዲያድግ ከፈጠራ ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት ማጠናከርን ይጨምራል። እንደ እርሱ ማብራሪያ ‘ማይ ሎኬተርን’ የማስፋፋት ፍላጎት አለ። ነግር ግን ቶሚሲን እጅግ ጠቃሚውን አርምጃ ወስዳለች ይላል።

“በቶሚሲን መተግበሪያ በሁለት ምክንያቶች በጣም ተመስጫለሁ። እጅግ የሚገርም ሀሳብ ከመስማት ይልቅ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ይሁኑ በተግባር ላይ የዋሉትን ማየት እመርጣለሁ። አንድ ሰው በጭንቅላቱ የሚመላለሰውን ሀሳብ ወደ መሬት አውርዶ እውን ማድረጉን እወደዋለሁ” ይላል።

ታዳጊ እምቅ አቅሞች

የቶሚሲን የኮምፒውተር ሳይንስ መምህር ኮፎዎሮላ ኮሌ እንደሚለው የታዳጊዋ ስኬት ትምህርት ቤቱ በትምህርት አይነቱ በሚከተለው የአቀራረብ ዘዴ ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል፤ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ላይም እንዲሁ።

“ከታዳጊ ተማሪዎች እንድንጀመር ተጨማሪ ብርታት ሰጥቶናል። ለወትሮው የምናተኩረው ትልልቆቹ ላይ ነበር፤ ቶሚሲን ማሳካት ስትችል ግን በታዳጊ ትምህርት ቤቶች ውስጥም እምቅ አቅም እንዳለ አወቅን” በማለት ይናገራል።

አኔዲ እንደሚለው በሀብታም እና ድሃ ቤተሰብ ባላቸው ተማሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ትምህርት ላይ የበለጠ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ ያስፈልጋል።

“ኢስቶኒያ፤ ብሪታንያ፤ ቻይናና ኮሪያን በመሳሰሉ ሌሎች ሀገሮች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ያተኮሩ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ አይተናል። ልጆቻችን በተመሳሳይ ደረጃ እና አንድ አይነት መሳሪያዎች እንዲሁም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቅመው ካልተማሩ ወደኋላ እንዳንቀር እፈራለሁ” ይላል።

ቶሚሲ ግን “ልዩነት የሚያመጣ ነገር መስራት በጣም የምወደው ነገር ስለሆነ ለቴክኖሎጂ በጣም ፍቅር አለኝ” ትላለች።

ይህ የቢቢሲ ተከታታይ ክፍል የተዘጋጀው ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.