ቁጠባ ወደ ስኬትዎ የሚያስገባ አይነተኛ መንገድ – Saving Money For a Successful Life

በታደሰ ብዙዓለም

ብዙዎቻችን ከትንሽ ደመወዝ ላይ በመቆጠብ ህይወታችን ሊቀየር እንደሚችል አናስብም።

ስለገንዘብ በቂ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ግን ይህን ቢያደርጉ በቀላሉ ወደ ስኬትና በልፅግና ጎዳና ሊያመሩ ይችላሉ ያሏቸውን ምክሮች ይጠቁማሉ።

ቢዝነስ ስታንዳርድ ይዞት በወጣው ዘገባ ላይ እንደተመለከተው ሀብት ለማከማቸት ዝግጁ መሆን ከሁሉ በፊት መምጣት ያለበት ጉዳይ ነው ይለናል፤ ዝግጁነት ደግሞ ከአስተሳሰብ ይጀምራል በማለት።

ሀብትን በማከማቸት ህይወትዎን ለመቀየር ከፈለጉ ፥ ቀደም ብለው እያራመዱት ያለውን የአይቻልም ካባ ማውለቅና አዲስ የአዕምሮ ዝግጁነትን መጎናፀፍም ግድ ይልዎታል።

ይሁንና አንዳንዶች ዝግጁነቱ ቢኖራቸውም እንኳን አካሄዱን ካለማወቅ ብዙ ጊዜ ውድቀትን ሲያስከትልባቸው እናስተውላለን።

ለመለወጥ ቁጠባ አይነተኛ መሳሪያ እንደሆነ ቢያምኑም ቁጠባቸውን በምን መልኩ ማከናወን እንዳለባቸው ግን ባለማወቃቸው ሲቸገሩ እናያለን።

                                          

ለዚህም በርካቶች በዘልማድ ያገኙትን ገንዘብ ካገኙና የሚፈልጉት ነገር ላይ ካዋሉ በኋላ ፤ የምትተርፋቸውን ጥቂት ገንዘብ በመቆጠባቸው ነው ውጤታማ ሊሆኑ የማይችሉት።

ባለሙያዎቹ ግን ይህ አይነቱ አካሄድ ኋላቀር እና ከዚህ ይልቅ ከወርሃዊ ወጪዎ አስቀድመው መደበኛ ቁጠባን ባህል ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ።

ልክ እንደ ሯጭ አትሌት ሁሉ ከመነሻ መድረሻ ግብን አስቀድሞ መወሰን ተገቢ ነው ሲሉም ያክላሉ።

የሚቆጥቡትን ገንዘብ ምን ላይ ሊያውሉት እንዳሰቡና ሊሰሩት ያሰቡት ስራ ምን ያህል ካፒታል እንደሚጠይቅ ማወቅም አስቀድመው ሊሰሩት የሚገባ የቤት ስራዎ ነው።

በገንዘብ አወጣጥዎ ላይ ህግና መመሪያ ማስቀመጥም ወሳኝ ነው፤ ከማገኛት አንስተኛ ገንዘብ ላይ ከዚህ በላይ ወጪ ማውጣት አይኖርብኝም በማለት ለፍላጎትዎ ልጓም ሊያበጁም ይገባል።

ገንዘብዎን ባገኙት ነገር ላይ ከመበተን መቆጠብና በጡረታ ጊዜ ሊያጋጥምዎ የሚችለውን የገንዘብ እጥረት ከግንዛቤ በማስገባት የቁጠባ ባህልዎ በተቻለ መጠን የማያቋርጥ እንዲሆን መወሰንም ይጠበቅብዋታል ።

ገቢዎትንና ወጪዎትን መለየትዎ ቁጠባ ከመጀመርዎ በፊት ሊያውቁት የሚገባ ጉዳይ ሲሆን፥ የቁጠባ ባህልዎ ማደጉ በተጨማሪም ብድርዎን ያለመጨናነቅ እንዲመልሱ የሚያስችልዎ አይነተኛ ስልት መሆኑንም መዘንጋት የለብዎትም።

እነዚህን ምክሮች በሚገባ ከተገበሩም ህልም የመሰለዎትንና በትንሽ ገቢ ቀስ በቀስ መለወጥ ይቻላል የሚለውን መርህ ገንዘብዎ በማድረግ፤ ሀብት መፍጠር ይችላሉ የሚለውም የባለሙያዎቹ መልዕክት ነው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement