ከከሰል የሚወጣው ጭስ ለሰው ልጅ ጤና አደገኛ በመሆኑ ለመሞቅ ያቀጣጠልነው ከሰል ሌላ መዘዝ ያመጣብናል እና ጥንቃቄ ብናደርግ መልካም ነው።
በከሰል ጭስ ምክንያትም በየጊዜው የተለያዩ ሰዎች ለሞት ሲዳረጉም በብዛት ይስተዋላል።
ከሰል በምናቀጣጥልበት ጊዜ ከውስጡ ካርቦን ሞኖክሳይድ /Carbon mono Oxide/ የሚባል ንጥረ ነገር የሚወጣ ሲሆን፦ ይህም ለጤናችን አደገኛ ነው ።
ታዲያ በታፈነ ቤት ውስጥ ከሰል አቀጣጥለን የንምጠቀም ከሆነ በቤቱ ውስጥ ያለው ሰው ላይ በካርቦን ሞኖክሳይድ አማካኝነት እስከ ሞት የሚደርስ ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል።
በከሰል ጭስ የመመረዝ ምልክቶች…
በከሰል ጭስ የመመረዝ ምልክቶች ውስጥ፥ ከፍተኛ የራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ እና የድካም ስሜት መሰማት ወይም የሰውነት መዛል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ የማዞር ስሜት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ የሰውነት መልፈስፈስ፣ የደረት አካባቢ ጨምድዶ የመያዝ ስሜት፣ ከፍተኛ የሆነ የድብርት ስሜት እና ራስን መሳት ሊከሰቱ ይችላሉ።
በከሰል ጭስ የመመረዝ ምልክቶችን የሚያሳይ ሰው ካጋጠምዎት በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ማዕከል በመውሰድ እርዳታን መስጠት ተገቢ ነው፡፡
ከሰልን አዘውትረን የምንጠቀም ከሆነ ማድረግ የሚገባን ጥንቃቄ…
ከሰልን አዘውትረን የምንጠቀም ከሆነ ከሰሉን በተቻለን አቅም ከቤት ውጭ በማቀጣጣል እና መጠቀም መልካም ነው።
በቤት ውስጥ የምንጠቀምም ከሆነ መጀመሪያ ከሰሉን ውጭ ላይ በማቀጣጣል ጭሱን መጨረሱን ካረጋገጥን በኋላ ቤት ውስጥ ማስገባት የምንችል ሲሆን፥ የቤቱ መስኮቶች እና በሮችን በመክፈት በቂ አየር ወደ ውስጥ እንዲገዳ እና እንዲወጣ ማድረግ።
እንዲሁም የተቀጣጠለ ከሰልን ከተጠቀምን በኋላ ማጥፋት፣ ከሰል በመኝታ ክፍል ውስጥ አለማኖርም ይመከራል።
ምንጭ:- ዶክተር አለ (Doctor Alle)