ኪንታሮት – Hemorrhoid

                                                                        

(በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም ቱፈር)

ሄምሮይድ ወይንም በተለምዶ ኪንታሮት ብለን የምንጠራው የሕመም ዓይነት ሲሆን ሕመም የሚከሰተው በፊንጢጣ ላይ የደም ስሮች (veins) ቬይንስ በሚያብጡ ጊዜ ነው፡፡

ሄሞሮይድ/ኪንታሮት ሠገራን በምናስወገድ ጊዜ ከማማጥ ወይንም በእርግዝና ጊዜ በሚከሰት የደም ስሮች ላይ የሚገኝ ግፊት ምክንያት የሚመጣ ሲሆን በሁለት መልኩ ይከፈላል፡፡

1) ውስጣዊ ሄሞሮይድ (internal hemorrhoid) በፊንጢጣ ውስጥ የሚገኝ
2) ውጫዊ ሄሞሮይድ (external hemorrhoid) በላይኛው ቆዳ ላይ የሚገኝ

ሄሞሮይድ በአብዛኛው የሚከሰት ሲሆን ዕድሜ 50 ዓመት የሞላቸው ሰዎች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት የሄሞሮይድ ምልክቶችን እንደሚያዩ ጥናቶች ያሳያሉ ነገር ግን አብዛኞቹ በቤት ውስጥ ሕክምና እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ በማድረግ ይድናሉ፡፡

ሄሞሮይድን የሚያስከትሉ ምክንያቶች

• ሠገራን ሲያስወግዱ ለረጅም ጊዜ ማማጥ
• ለረጅም ሰዓታት በመፀዳጃ ቤት መቀመጥ
• የሆድ ድርቀት (ለረጅም ጊዜ የቆየ)
• ከመጠን ያለፈ ውፍረት
• ዕርግዝና
• የፋይበር መጠኑ የቀነሰ ምግብ መመገብ ናቸው

• በዕድሜ መጨመር ቬይኖችን የሚደግፉ የሰውንት ክፍሎች እንዲደክሙ ስለሚያደርግ ለሄሞሮይድ ያጋልጣል፡፡

የሄሞሮይድ/ኪንታሮት ምልክቶች

• ሕመም የሌለው ከፊንጢጣ የሚፈስ ደም
• በሰገራ መውጫ አካባቢ ማሳከክ
• ሕመም ወይንም አለመመቸት
• በፊንጢጣ አካባቢ እብጠት ናቸዉ፡፡

ሃኪምዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነው?

– በፊንጢጣ የሚወጣ ደም የሄሞሮይድ/ኪንታሮት የተለመደ ምልክት ነው፡፡ ነገር ግን ከሌሎች የሕመም ዓይነቶች እንደ ኮሎሬክታል ካንሰር እና ሌሎች የህመም አይነቶች ጋር ተመሳሳይ ምልክት ሊኖረው ስለሚችል ሄሞሮይድ ነው በሚል ግምት ችላ ሊባል አይገባም፡፡ ስለዚህም ወደ ሐኪም በመሄድ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

– ከፍተኛ ሕመም የሚሰማዎ ከሆነ እና በቤት ውስጥ የሕክምናዎች ለውጥ የማያገኙ ከሆነ ወደ ሕክምና ቦታ መሄድ ይገባዎታል፡፡

– ከፍተኛ መጠን ያለው ደም መፍሰስ ካጋጠምዎ እና እንዲሁም ራስ የማዞር የመሳሰሉት ስሜት ከተሰማዎ ወደ ሐኪም እንዲሄዱ ይመከራል፡፡

ሄሞሮይድ የሚያስከትለው ተያያዥ ጉዳቶች ምንድን ናቸዉ?

– አኒሚያ (የደም ማነስ) ከፍተኛ የሆነ ደም በሚፈስ ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ ኦክስጂን ተሸካሚ ቀይ የደም ሴሎች መጠን ስለሚቀንስ የድካምና ራስ የመሳት ሁኔታዎችን ያስከትላል፡፡

– ለውስጣዊ ሄሞሮይድ የሚደርሰው የደም ፍሰት መጠን ሲቀንስ ከፍተኛ የሆነ ሕመምን ያስከትላል፡፡ ይህም ለሴሎች መሞት እና ለጋንግሪን ይዳርጋል፡፡

በቤት ውስጥ የሚደረጉ ሕክምናዎችና የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች

• ለብ ባለ ውሃ ከ10 – 15 ደቂቃ በቀን በቀን ሁለትና ሶስት ጊዜ መዘፍዘፍ
• ሁሌም ከተፀዳዱ በኋላ በሚገባ በንፁህ ለብ ባለ ውሃ መታጠብ
• ደረቅ የሆነ የመፀዳጃ ወረቀትን አለመጠቀም
• እብጠት እንዲቀንስ በረዶን መጠቀም
• ሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን መጠቀም

ከላይ የተጠቀሙትን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሄሞሮይድን ማጥፋት የሚቻል ሲሆን ሕመም የሚያብስ ከሆነ እና ምንም ዓይነት ለውጥ በሳምንት ውስጥ ካላገኙ ወደ ሕክምና ቦታ እንዲሄዱ ይመከራል፡፡

ሄሞሮይድን ለመከላከል ምን ማድረግ ይገባል?

• በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን ማዘውተር
አትክልት፣ፍራፍሬዎችን መመገብ ሠገራን በማለስለስ ማስማጥ እንዳይኖር ያድርጋል፡፡
• ፈሳሽ በብዛት ይውሰዱ
በቀን ከስድስት እስከ ስምንት ብርጭቆ ውሃን ወይም ጭማቂን መውሰድ
• ማስማጥን ማስወገድ
ሠገራን ለማስወጣት በምናምጥ ጊዜ በደም ስሮቻችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ግፊትን ስለምንፈጥር ለሄሞሮይድ/ለኪንታሮት/ ተጋላጭንት ይጨምራል፡፡
• ሠገራ በሚመጣ ጊዜ ጊዜውን ሳያልፉ ወደ መፀዳጃ ቤት በመሄድ ያስወግዱ፡፡ አለዚያ ሠገራዎ ስለሚደርቅ ለማስወገድ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
• የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያዘውትሩ
የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ጤናማ እንድንሆን ያደርጋል፣
• ለረጅም ሰዓታት መቀመጥን ያስወግዱ፡፡ በተለይም በመፀዳጃ ቤት ለረጅም ሰዓት መቀመጥ ለሄሞሮይድ መከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

ምንጭ፦Mahdere Tena

Advertisement