ስልክን ቻርጅ በሚያደርጉ ጊዜ ማስተዋል ያለብዎት ጉዳይ

                                                                        

ዘመናዊ ስልኮች ከስሪታቸው አንጻር ባትሪያቸው ቶሎ የሚያልቅና አጭር ጊዜን የሚያስጠቅሙ ናቸው።

ከዚህ አንጻርም ተጠቃሚዎች ባትሪውን ቶሎ ቶሎ ሃይል ለመሙላት (ቻርጅ ለማድረግ) ሲሞክሩ ይስተዋላል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ምናልባትም የባትሪን እድሜ ሊያሳጥር እና ሙሉ በሙሉ ሊያበላሸውም ይችላል።

ስልክን ከመጠቀም ባለፈ ግን የባትሪ እድሜን ማራዘምና በአግባቡ ቻርጅ በማድረግ መጠቀም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

ስልክዎን ቻርጅ በሚያደርጉበት ጊዜ ምናልባት ያላስተዋሏቸው ነገሮች ይኖራሉና እነዚህን የባለሙያ ምክረ ሃሳቦች እናካፍልዎ።

ቻርጅ እያደረጉ ስልክን በጭራሽ አለመጠቀም፦ አንዳንድ ጊዜ አስቸኳይ ጉዳይ ቢያጋጥም እንኳን ስልክን ቻርጅ እያደረጉ ባይጠቀሙ ይመረጣል።

ምናልባት የግድ ከሆነ ደግሞ ስልኩ ከተሰራበት ኩባንያ አብሮ የተዘጋጀን ቻርጀር እየተጠቀሙ ቢሆን ይመረጣል ይላሉ ባለሙያዎች።

ጥራት ያላቸውን ባለማራዘሚያ ቻርጀሮች መጠቀም፦ ባለማራዘሚያና በአብዛኛው በነጭ መደብ የተሰሩ እውነተኛ ቻርጀሮችን መጠቀም የባትሪን እድሜ ለማራዘም ይረዳልና ይጠቀሙበት።

ሌሊቱን ሙሉ ቻርጅ ከማድረግ መቆጠብ፦ ወደ መኝታ ሲያመሩ ስልክዎን ቻርጀር ላይ ሰክተው ማሳደርዎ አደጋ አለው።

ይህም ባትሪው ከመጠን በላይ ቻርጅ በማድረግ ማዳከም ይጀምራል፥ በአብዛኛው ስልክን በ40 እና በ80 ፐርሰንት መካከል ቻርጅ ማድረግ መልካም መሆኑንም ይመክራሉ።

ምክንያታቸው ደግሞ 40 ፐርሰንት ከደረሰ ቻርጅ ማድረጉ ግዴታ ሲሆን 80 ከሆነ በኋላ ነቅለው ቢገለገሉበት ችግር የለውም የሚል ነው።

ስልክን ለተወሰነ ጊዜ ማጥፋት፦ ሰው ሰርቶ ማረፍ እንደሚፈልገው ሁሉ ስልክን ማጥፋትም ለባትሪው መልካም እንደሆነ ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት።

ለዚህ ደግሞ ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን በተለይም ወደ መኝታ ሲያመሩ በማጥፋት እረፍት መስጠት።

ይህ ሲሆን ደግሞ የስልኩ ባትሪ እድሜ እንዳያጥርና ረዘም ላለ ጊዜ እንዲያገለግልዎ ይረዳል።

ባትሪው እስከሚያልቅ ጠብቆ ቻርጅ አለማድረግ፦ ሌላውና በብዙ ሰዎች የተለመደው ጉዳይ ደግሞ የስልክ ባትሪ እስከሚያልቅ ጠብቆ ቻርጅ ማድረግ ነው።

ይህ ደግሞ ለባትሪ እድሜ የመጀመሪያውና ዋናው ጠር ነውና፥ ባትሪው 40 ፐርሰንት ላይ ሲደርስ ቻርጅ ማድረጉን ይመክራሉ።

ይህ ባይሆን እና በጣም ከወረደ በኋላ ቻርጅ ለማድረግ መሞከሩ ግን ባትሪን በመግደል ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላልና ይህን ልማድ ያስወግዱም ይላሉ።

ከዚህ ባለፈም ቻርጀሩን ከቀጥተኛው ሶኬት ላይ አለመሰካት እና ከፍተኛ ሙቀት ባላቸው ቻርጀሮች አለመጠቀም መልካም ነው።

ለስልኩ መከላከያ የገጠሟቸውን ነገሮች ማስወገድ፦ ስልክ ቻርጅ ሲደረግ ቀስ እያለ መሞቁ የተለመደ ጉዳይ ነው።

ይሁን እንጅ ስልኩን ከአደጋ ለመከላከል በሚል የለጠፏቸው መከላከያዎችን ቻርጅ በሚያደርጉ ጊዜ አለመንቀል ባትሪው ከመጠን በላይ እንዲግልና በጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲያቆም ሊያደርገው ይችላል።

ፈጣን ቻርጀሮችን አይጠቀሙ፦ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ከመቸኮል የተነሳ ቶሎ ሃይል የሚሞሉ ፈጣን ቻርጀሮችን መጠቀምና እነሱኑ አማራጭ ማድረጉ አይመከርም።

ምክንያቱም እነዚህ ቻርጀሮች በፍጥነት ሃይል ስለሚለቁ ባትሪው ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ከልክ በላይ እንዲግል ያደርጉታል።

ይህም በባትሪው እድሜ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ ከልክ በላይ መጋሉ ባትሪውን የማቃጠል እድሉ ከፍተኛ ነው።

የባትሪ መተግበሪያዎችን ማጥፋት፦ ከኢንተርኔት አውርደው የሚጠቀሙባቸውን አንዳንድ “የባትሪ እድሜ ማራዘሚያ” መተግበሪያዎችን በዚህ ጊዜ መዝጋት ይመከራል፤ ከዚህ ባለፈም በየጊዜው ቻርጅ አለማድረግ።

ቻርጅ ሲያደርጉ 80 በመቶ ከደረሰ በኋላም መንቀልና መጠቀም ይቻላል፥ ይህን ሲያደርጉ ባትሪው ቶሎ ቶሎ እንዳይጨርስ ይረዳዋል።

ቻርጅ እያደረጉ ስልኩን አለመጠቀም ሌላው ጠቃሚ ምክረ ሃሳብ ነው።

ከዚህ ባለፈም የባትሪውን እድሜ ለማራዘም የማይጠቀሙባቸውን መተግበሪያዎችን መዝጋት፦ ይህን ማድረግዎ ባትሪው ስልክዎን በሚጠቀሙበት መጠን እንዲሰራ በማድረግ የተሻለ መቆጠብ እና መጠቀም ያስችልወታል። 

የስልኩን ንዝረት መቀነስ፦ ስልኩ በሚጠራ ጊዜ ያለው ንዝረት ከፍተኛ መጠን ያለው ሃይል ይጠቀማል፤ ይህ ደግሞ የስልኩን ባትሪ ቶሎ እንዲያልቅ ያደርገዋል።

የስክሪኑን የብርሃን መጠን መቀነስ፦ የስልኩ የብርሃን መጠን ከፍተኛ ሲሆን ባትሪው ቶሎ እንዲያልቅ ያደርገዋልና በተቻለ መጠን የስልኩን ስክሪን ብርሃን መጠን (screen brightness) መቀነስዎን አይዘንጉ።

ብሉቱዝ እና ዋይፋይ መዝጋት፦ የስልኩን ብሉቱዝ መዝጋት ስልኩ በአቅራቢያው ካሉና ብሉቱዛቸወን ከከፈቱ ስልኮች ጋር ሲገናኝ ባትሪውን በብዛት ስለሚጠቀም ቶሎ የመጨረስ እድሉ ከፍተኛ ነው።

ከዚህ ባለፈም ገመድ አልባ ኢንተርኔት (ዋይ ፋይ) በሌለበት ቦታ ኔትዎርኩን መዝጋት ስልኩ ኔት ዎርክ ፍለጋ የሚያጠፋውን ባትሪ እንዲቀንስ ያስችለዋል። 

ኢንተርኔቱን ማጥፋት፦ የስልኩ ኢንተርኔት (ሞባይል ዳታ) ክፍት ከሆነ ኢንተርኔት በሚጠቀም ጊዜ ብዙ ባትሪ ስለሚወስድ ኢንተርኔቱን ቢያጠፉ ይመከራል። 

ስልኩን ለመነጋገሪያ ብቻ ቢጠቀሙበት፦ በስልክዎ ፊልሞችን መመልከትና የተለያዩ ጨዋታዎችን (ጌም) መጫዎት ለባትሪ እድሜ ጠር ነውና ያነን ያስወግዱ።

ብዙ መተግበሪያዎችን በአንድ ጊዜ ከመዝጋትና መክፈት መቆጠብ

ብዙ ጊዜ እንደነ ኦፔራ ሚኒ፣ ፌስቡክ የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን ተጠቅመን ስንጨርስ ዘግተን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መልሰን እንከፍታለን፡፡

ስለሆነም ከተጠቀምን በኋላ የ“ሆም” ቁልፉን ተጠቅመን መውጣት ሌላ ጊዜ መጠቀም ስንፈልግ ሞባይላችን ካቆመበት እንዲቀጥል ያደርገዋል፡፡
ይህም የሞባይላችንን ባትሪ እድሜን ያስቀጥላል።

እርስዎም ከላይ የተጠቀሱትን የባለሙያ ምክረ ሃሳቦች በመተግበር የስልክዎን ባትሪ እድሜ ያራዝሙ።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement