የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለመስራት ትክክለኛው ሰዓት የቱ ነው? – What’s the Best Time to Exercise?

                                                             

አብዛኞቻችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ጠዋት ከእንቅልፍ ስንነቃ የምንሰራ ሲሆን፥ በርካቶች ደግሞ ማታ ከስራ መልስ ወደ ስፖርት ቤት ጎራ በማለት መስራትን ያዘወትራሉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለሙያዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለመስራት ትክክለኛ ሰዓት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በአግባቡ ለመስራት ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ ምክር ለግሰዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለመስራት ትክክለኛው ሰዓት የቱ ነው…?

የአካል ብቃት እቅስቃሴ ባለሙያ የሆነው ባን ሃስ፥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የግድ ጠዋት ወይም ማታ መስራት የለብንም፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለመስራት ትክክለኛው ሰዓት ውስጣችን በጣም ተነሳሽነት በሚኖረው ጊዜ ነው ይላል።

ወደ ስፖርት ቤት ለመሄድ የማመንታት ስሜት በማይሰማን ሰዓት፣ እዛም ሄደን ያለ ድካም ለመስራት ውስጣችን ተነሳሽነት ሲሰማው እና የድካም ስሜት እየተሰማን ካልሆነ ይህ ትክክለኛው ሰዓት ነው ብለዋል።

ጠዋት ወይም ማታ ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት የማይመቸን ከሆነ ደግሞ ምሳ ሰዓታችንን ተጠቅመን እንደ ዮጋ ያሉ ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ብንሰራም መልካም ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ።

የአካል ብቃት አሰልጣኝ የሆነው ጆናታን ቴይለር በበኩሉ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለመስራት ትክክለኛው ሰዓት ይህ ነው ተብሎ የተቀመጠ ነገር የለም፤ ሰዓቱ እንደ ግለሰቡ ምርጫ የሚወሰን ይሆናል ብሏል።

በጠዋትም ይሁን በማታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስራት በምናገኘው የጤና ጠቀሜታ ላይ ላይ የሚያመጣው ተጨባጭ ልዩነት እንደሌለም ነው ጆናታን የሚናገረው።

ዋናው ውስጣችን የአካል ብቃት ለመስራት ተነሳሽነት መኖሩ ነው እንጂ በማንኛውም ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብንሰራ የጤና ጠቀሜታ እንደሚያስገኝልን ነው አሰልጣኑ ያስታወቀው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement