የዲቪ ነገር – DV Lottery

                                                               

ኤፍሬም እንዳለ

ያለፈው ቅዳሜ ነው፡፡ ጠዋት ላይ በከተማችን አንዱ ክፍል በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች ያሉ ሀያ አምስት፣ ሠላሳ የሚሆኑ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ይቁነጠነጣሉ፣ ይንጎራደዳሉ፡፡ ምን ተፈጠረ? የተፈጠረውማ ገና በጠዋቱ መብራቱ እንደለመደው ድርግም ብሎ ጠፍቷል፡፡

እና ደግሞ ለአዲስ አበባ መብራት መጥፋት ምን አዲስ ነገር አለው! አዲአለው!ማ እነኚሀ ሰዎች በሌሊት የመጡት ለአንድ አስቸኳይ ጉዳይ ነበር … የዲቪ ፎርም ለመሙላት፡፡

አዎ የሌሊት ህልማቸውን አቋርጥው የእውን ህልማቸውን ሊያሳድዱ የመጡ ናቸው … ዲቪ ሞልተው፣ እጣ ደርሷቸው እዛቹ አሜሪካ የሚሏት ሁሉም የሚሮጥባት አገር ለመሄድ፡፡

እናማ፣ እንደተለመደው ገና በማለዳው መብራቱ ድርግም ሲል፣ ለጥቂት ሰዓታትም ቢሆን ተስፋቸውን አጨልሞባቸዋል፡፡ ወይም ልክ በዓል ሲደርስ በበዓሉ ወቅት “ምንም አይነት የሀይል መቆራራጥ እንዳይደርስ ዝግጅት ተደርጓል እንደሚባለው ሁሉ “የዲቪ ሎተሪ ፎርም መሙያ ጊዜ እስኪጠናቀቅ ምንም አይነት የሀይል መቆራረጥ እንዳይኖር ዝግጅት ተደርጓል” ይባልልን፡፡

በነገራችን ላይ፣ አሁን ኢንተርኔት ካፌውም በዝቶ፣ ሰዉ በየመሥሪያ ቤቱም፣ በየመኖሪያ ቤቱ ኮምፒዩተሩ በዝቶ አንድ ሰሞን እናይ የነበረውን ግርግር ባናይም ህዝባችን እንደ ጉድ የዲቪ ፎረም እየሞላ ነው፡፡ የቀይ ባህርንና የሜዲቴራኒያንን አሰቃቂ አደጋዎች እንኳን ሳይፈራ የሚፈልስ ህዝባችን እንደ ዲቪ አይነት አድል ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ከጠቅላላችን በየዓመቱ ስንታችን እንሆን ፎርም የምንሞላው!

ለምሳሌ በላይቤሪያና በሌሎች የምእራብ አፍሪካ አገሮች ከመላው ህብረተሰብ ወደ 10% የሚጠጋው ዲቪ ፎርም ይሞላል ነው የሚባለው፡፡ በጣም ብዙ ቁጥር ነው ይላሉ፡፡ እኛ ዘንድ አሥር በመቶ ቢባል ወደ አስር ሚሊዮን ህዝብ ማለት ነው፡፡ አሥር ሚሊዮናችንም ሞላን አርባ ሚሊዮናችን፣ አንዱ ሀቅ ዘንድሮ ብዙ ነገሮች የሰዉን ልብ እያሸፈቱት ነው፣ ውጪ፣ ወጪ እያስባሉት ነው፣ የማያውቀውን አገር እያስናፈቁት ነው፡፡

እንደ በፊቱ “ሠርቶ መኖር አገር ውስጥ!” ብሎ ነገር ከመልካም ምክርነት ይልቅ ወደ ፌዝ የተጠጋ ይሆናል፡፡ ስንት ዓመት ሙሉ ራሳቸውን ለሥራ ብቁ ለማድረግ ናላቸውን ሲያዞሩ የኖሩ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ተመራቂዎች ሥራ እያጡ አራትና አምስት ዓመት በሚንከራተቱበት ዘመን አንዳንድ የለመድናቸው አባባሎች ፌዝ ይሆናሉ፡፡ በሌለ ሥራ፣ ባልተፈጠረ የሥራ መስክ…

“አገር ውስጥ ሠርቶ አይኖርም!” 
“ሰው አገር ከመሄድ አንዱ መሥሪያ ቤት ብትቀጠር አይሻላትም!”

ብሎ ነገር ከመልካም ምኞትነት የማያልፍበት ዘመን ላይ እየደረስን ነው፡፡ እናማ… ሰዋችን የዲቪ ፎርም ለመሙላት ይህን ያህል የሚጨነቀው ልበ ደረቅ ስለሆነ፣ አገሩን ስለጠላ ምናምን አይደለም፡፡

በተለየ ወጣቱ እንደ መስቀል አደባባይ ሰልፍ በኢንተርኔት ካፌዎች ቢኮለኮል አይገርምም፡፡ ስንት ዓመት ለፍተው ከተመረቁ በኋላ አራትና አምስት ዓመታት ሥራ በማይገኝበት ጊዜ ሰዉ ‘ዲቪ መዳኛዬ’ ቢል አይገርምም፡፡

አሁን ግን ዲቪ ከባድ ጠላት ተነስቶበታል፣ ክንዳቸው ሀያል የሆኑ ጠላት፣ ዶናልድ ትረምፕ የሚባሉ ጠላት፡፡ ኮንግረስን “ይሄንን ዲቪ የሚሉትን ነገር ሰርዙልኝ፣” እያሉ ነው፡፡ በርካታ ደጋፊዎች አሏቸው – ከሪፐብሊካን ፓርቲው ብቻ ሳይሆን ከዴሞክራቲክ ፓርቲውም፡፡ በዚህም የተነሳ ‘የዲቪ ሎተሪ ዘመን ሊያጥር ይሆን እንዴ!” እየተባለ ነው፡፡

የዲቪ ሎተሪ ተቃዋሚዎች አንዱ ትልቅ ምክንያት ሽብርተኞች ሰተት ብለው አገራችን እንዲገቡ ማድረግ ይሆናል የሚል ነው፡፡ “ሽብርተኛ ድርጅት ከሆንክ ከበርካታ ሀገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቶችህ ፎርም እንዲሞሉ ታደርጋለህ … ከእነዚህም አንዱ ወይም ሁለቱ እጣው ሊደርሳቸው ይችላል” ብለዋለ አንድ የዲቪ ተቃዋሚ የኮንግረስ አባል፡፡

“ዲቪ ሎተሪ ሸፍጥ የበዛበት፣ ምንም አይነት ኤኮኖሚያዊ ወይንም ሰብአዊ ጠቀሜታ የሌለው ነው” ብለዋል ሌላኛው የምክር ቤት አባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሪፐብሊካኖቹ ቁጥጥር ስር ባለው በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ዲቪ ሎተሪን ለማስቆም ያለሙ ቢያንስ ሁለት የውሳኔ ረቂቆች አሉ፡፡

ሄሻም መሀመድ ሃዳዬት የተባለ ግብጻዊ በሎስ አንጀለስ አውሮፕላን ጣቢያ ተኩስ ከፍቶ ሰዎች ይገድላል፡፡ ግብጻዊው ከጥቂት ዓመታት በፊት በዲቪ ሎተሪ ነበር አሜሪካ የገባው፡፡ ድርጊቱ አቧራ አስነስቶ ነበር፡፡ “ይኸው ሎተሪ፣ እጣ እያላችሁ አሸባሪዎችን እያስገባችሁ ልታስጨርሱን ነው!” አይነት ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡

በቀደም እለት ደግሞ ኒው ዮርክ ውስጥ በመኪና ብዙ ሰዎች ገጭቶ የገደለው ሳይፉሎ ሳይፖቭ እንዲሁ በዲቪ ሎተሪ የገባ ነው፡፡ በ2009 ከኡዝቤክስታን እድል ካገኙት 3‚284 ሰዎ አንዱ ነው፡፡ እንደውም እሱ ከገባ በኋላ መአት ሰዎች ጎትቷል ነው የሚባለው፡፡

በነገራችን ላይ ብዙዎች ዲቪን ዘመናዊ ባርነት ይሉታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አብዛኞቹ በዲቪ ከየደሀ ሀገራት የሚሄዱ ሰዎች ዝቅተኛ በሚባሉ ሥራዎች ላይ መውደቃቸው ነው፡፡ “አሜሪካውያን ዝቅተኛዎቹን ሥራዎች እነሱ መሥራት ስለማይፈልጉ የዘየዱት ዘዴ ነው፣” ይላሉ፡፡

በተለይም ከአፍሪካ ሀገራት ወደላይ የሚፈናጠሩ ብዙ አይደሉም ነው የሚባለው፡፡ ብዙ የእኛ ልጆች ማጣፊያው አጥሯቸው ባክነው ቀርተዋል ይባላል፡፡ በሌላ በኩል ቢከፋም ቢለፋም የአቅማቸውን ያህል እየሠሩ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳደሩ ብዙ ናቸው፡፡

“ህይወቴን ለውጦታል፣” ብሏል ቪክተር ኦቴ የተባለ የቬኑኒዙዌላ ተወላጅ፡፡ “እኔ ከአገር ከወጣሁ በኋላ ቬኑዙዌላ ምን እንደሆነች ተመልከቱ!” ግን ከመጭበርር አላመለጠም፡፡ ለአንድ ኩባንያ 150 ዶላር ከፍሏል፡፡ እጣ ሲደርስው ኩባንያው ተጨማሪ 3‚000 ዶላር ክፈል አለው፡፡ አንድ አሜሪካዊ ጓደኛው ነው “ምንም መክፈል የለብህም!” ብሎ ያተረፈው፡፡

በቅርብ ዓመታት አብዛኞቹ የዲቪ አሸናፊዎች ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ናቸው፡፡ ከእነኚህም መሀል እነኢራን፣ ግብጽ፣ ባንግላዴሽ፣ ኡዝቤክስታን፣ ቱርክ የመሳሰሉ ሙስሊም ሀገራት አሉባቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት ከ77% በላይ ዲቪ አሸናፊዎች ከአፍሪካና ከእስያ ናቸው፡፡

ለበርካታ ዓመታት ግብጽና ባንግላዴሽ በጣም ብዙ እድለኞች ልከዋል፡፡ ከ2001 ጀምሮ ባለው ጊዜ ከባንግላዴሽ ብቻ በዲቪ ሎተሪ 180‚000 በላይ እድለኞች አሜሪካ ገበተዋል፡፡ እንዲሁም ከ191‚000 በላይ ኢራናውያን በዚህ ጊዜ አሜሪካ ገብተዋል፡፡ የእኛ ስንት ይሆኑ ይሆን ! በነገራችን ለይ በዲቪ ሎተሪ 2019 ባለፉት ዓመታት 50‚000 ዜጎቻቸው ዲቪ ሎተሪ የደረሳቸው እንደ ካናዳ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ናይጄሪያና ሜክሲኮ በዘንድሮው እጣ አልተካተቱም፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲቪ ፎርም የሚሞላው ሰው መአት ነው፡፡ ለምሳሌ ለዲቪ 2018 ያመለከቱት ሰዎች 14‚600 000 በላይ ናቸው፡፡ ያስመዘገቧቸው ቤተሰቦች ሲጨመሩ ደግሞ ቁጥሩ ከ23 ሚሊየን ያልፋል፡፡

የተመረጡት 115 968 ናቸው፡፡ ከእነኚህ ነው እንግዲህ በኢንተርቪውም በምኑም እየተቀነሱ 50‚000ዎቹ ብቻ የሚቀሩት፡፡ ማንኛውም አገር ከ7% በላይ የዲቪ ሎተሪ ቪዛዎች አይሰጡትም፡፡ ይህም ማለት 3‚500 ቪዛዎች ማለት ነው፡፡

በዚህ ላይ ደግሞ አጭበርባሪው በጸጉር ልክ ነው፡፡ በብዙ ሀገራት በአሜሪካ መንግሥት አካላት የተከፈቱ በሚመስሉ ድረ ገጾች ብዙዎች ይታለላሉ፡፡ ብዙዎቹ በተለያያ ሰበብ ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ ብዙ አመልካቾች ዝርዝሩን ሰለማያውቁትና አሜሪካ ለመግባት ባላቸው ከፍተኛ ጉጉት ገንዘባቸውን ይከስራሉ ነው የሚባለው፡፡

እድሉ ደርሶ ወደዛ ሲኬድ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ብለው ብዙ ችግር ውስጥ የሚገቡ አሉ፡፡ ሁሉም ነገር እንደቤታችው እየመሰላቸው፣ እዚህ በየመዝናኛው፣ በየሞሉ ረብጣ ብር እየመዘዙ እንደሚሸለለው እዛም በየቦታው ረብጣ ብር መምዝዝ የሚያስጨበጭብና የሚያስቀና እየመሰላቸው ችግር ላይ የሚወድቁ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

አሜሪካ ለሀያ ዓመታት በላይ የኖረ አንድ ወዳጃችን የነገረን ታሪከ አለ፡፡ ልጁ እዚህ ቅልጥ ያለ አራዳ የሚባል አይነት ነው፡፡ ምንም እንኳን ዘንድሮ የአራድነት ትርጉም ራሱ የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ቢሆንም፡፡ እየተጣጠፉ፣ እየተገለባባጡ ምን እያሉ ገንዘበ መሥራት ይችልበታል፡፡ አሜሪካ ይሄድና እንዲሁ እዚህ በለመደው መንገድ ይገለባበጥ፣ ይተጠጣፍ ጀመር፡፡ ደግሞ ተሳካለትና ዶላረ ሰበሰበ፡፡

አንድ ቀን መኪና ለመግዛት ይሄዳል፡፡ የሠላሳ ሺህ ዶላር መኪና ሊገዛ ከተስማማ በኋላ “እሺ ክሬዲት ካርድ፣” ሲሉት፣ ልምድ አይለቅም አይደል፣ “አይ በካሽ ነው የምከፍለው” ይላቸዋል፡፡ ከዛም የመኪና መሸጫው ባለቤት “እሺ ጠብቀኝ” ብሎት ቢሮው ይገባል፡፡ ምንም ያሀል ሳይቆይ በመኪና ከች አሉለት … የአገር ውስጥ ገቢ ሰዎች፡፡

“ይሄን ሁሉ ገንዘብ ከየት አመጣህ?” አይነት ማፋጠጥ ጀመሩ፡፡ መንተባተብ ሲጀመር “የምናቀርብልህ ጥያቄዎች አሉ” ተብሎ ተወሰደ፡፡ ታሪኩን በሰማን ጊዜ ገና መከራ ውስጥ ነበር፡፡
እናማ ዜጎቻችን እድል ደርሷቸው ያለ በቂ መረጃ እየሄዱ ችግር እንዳይደርስባቸው እውነተኛ መረጃ የሚያገኙበት ስርአት መዘርጋት ብልህነት ይሆናል፡፡

ባልና ሚስቱ ጥሩ ሥራ፣ ጥሩ ገቢ አላቸው፡፡ የራሳቸው አሪፍ ቤት፣ መኪና ምናምን አላቸው፡፡ በእኛ አገር ደረጃ ከፍተኛ ኑሮ ካላቸው የሚጠጉ ናቸው፡፡ እና በአንድ ወቅት ባልየው ዲቪ ሎተሪ ይደርሰዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ዘመድ አዝማድ “መቼም ይሄን ሁሉ ነገር ጥለው አይሄዱም” ምናምን ይላል፡፡ ሰው አሜሪካ የሚሄደው ለተሻለ ኑሮ፣ ለተሻለ ገቢ አይደል እንዴ ! እነሱ እንዲሀ አይነት ኑሮ እየኖሩ ምን ጎደለባቸወና ይሄዳሉ ! ዘመድ፣ አዝማድ መከረ፣ “እንደው እንዲች ብላችሁ እግራችሁን እንዳታነሱ !” ተባሉ፡፡

አልሰሙም፡፡

ያላቸውን ንብረት ሁሉ ቸበቸቡት፡፡ “ደህና ሁኚ አንቺ ምናምን አገር፣” ብለው ሄዱ፡፡ ዓመታት አለፉ፡፡ ከዛም ድንገት ሳይታሰብ ሁለቱም አዲስ አበባ ከች አሉ፡፡ አሜሪካ አልሆነችላቸውም፡፡ ቢሉ፣ ቢለፉ ምንም ሊሳካ አልቻለም፡፡ እዚህ የተለማመዱት የማሪንጌቻቻ ኑሮ አሜሪካ ፊልም ላይ ብቻ የሚያዩዋት ሆነ፡፡ እዚህም ሲመጡ ምኑም ምናምኑም አልሆነ፡፡ ትዳር ፈረሰ፣ ከዛ በኋላ ሁለቱም የት ይግቡ፣ የት ይውጡ የሚያውቅ የለም፡፡

እነኚህ አይነት ሰዎች አጠቃላይ ስዕሉን ማሳያ አይሆኑም፡፡ በጣም ብዙ ወገኖቻችን ጥርሳቸውን ነክሰው ጥሩ ደረጃ ከመድረስም አልፈው ለቤተሰቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው ሳይቀር ተርፈዋል፡፡ ዶላሩን ወደ አገር ውስጥ የሚያጎርፉት ብዙዎች በዲቪ የሄዱና በዲቪ በሄዱ ዘመዶቻቸው ብርታት አሜሪከ የገቡ ናቸው፡፡

እናም ይሄ ‘ዲቪ ይሰረዝ’ የሚባለው ነገር ተቀባይነትን አግኝቶ ትረምፕና የአላማው ደጋፊዎች የልባቸው ከሞላ በእርግጥም እኛም እንጎዳለን ማለቱ ማጋነን አይሆንም፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ምናልባትም ከዛ በላይ የሚሆን ህዝብ ከውጪ ከዘመድ አዝማድ በሚላክለት ገንዘብ ትንፋሹን የሚያቆይባት አገር እንዲህ አይነት እድሎች ሲታጠፉባት “እሰይ” የሚያሰኝ አይሆንም፡፡

ለአሁኑ ግን መብራቶችም እባካችሁ ተባበሩ፡፡ ግዴለም፣ መብራት ባይኖርም የቀዘቀዘ ሹሯችንን ግጥም አድርገን እንበላለን፡፡ የሰዋችንን የዲቪ ህልም ግን አታቀዝቀዙበት፡፡

እስከዛው ድረስ ዲቪ ፎርም ለሞሉና ለሚሞሉ ሁሉ መልካሙ ይግጠማቸው እንጂ ሌላ ምን ይባላል

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

 

Advertisement