ሞትን አምልጦ የብዙዎችን ተስፋ ያንሰራራው ወጣት – The Young Man Who Escaped Death Gives Hope To Others

                                                      

በብዙዎች ዘንድ አሰቃቂ ትውስታን ጥሎ ያለፈው የ 1977 ዓ.ም ረሃብ በተለይም በትግራይና በወሎ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ጠባሳን ጥሎ አልፏል። ሰው የሚላስ የሚቀመስ ባጣበት ወቅት ደርግ መፍትሄ ያለውን እርምጃ ወስዷል።

ህዝቡ ቢቀበለውም ባይቀበለውም ከያሉበት በማሰባሰብ ውሃና ልምላሜ ይገኝባቸዋል ወደ ተባሉ የሃገሪቱ ክፍሎች ሄዳችሁ መስፈር ኣለባችሁ በማለት ኣወጀ። ይህ ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ ሰፈራ በመባል የሚታወቀው ነው።

በዚህም አጋጣሚ በኣላማጣ ዙርያ ሎላ በተባለች ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት ባልና ሚስት ከበኩር ልጃችው ጋር ለገበያ ወደከተማ እንደወጡ ቤት የቀሩትን ልጆቻቸው ለጎረቤት አደራ ሳይሰጡ ነበር ታፍሰው በሄሊኮፕተር ወደ ወለጋ የተወሰዱት።

እንደስሟ አልሆነላትም እንጂ ሎላ ማለትስ ኣረንጓዴ/ልምላሜ ማለት ነበር። መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ወላጆቹ የተወሰዱበት የ6 ዓመቱ ህፃን አበበ ፋንታሁን ከሴት አያቱ ጋር በሎላ መኖር ጀመረ። ወላጆቹን በቅጡ ሳያውቃቸው እነሱም አንደልጅ አይተው ሳይጠግቡት መለያየታቸው ግድ ሆነ።

መለያት

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ህፃኑ በረሃብ ምክንያት መታመም በመጀመሩ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የማያውቁት አያቱ እንደጨርቅ ጠቅልለው ኣላማጣ ወደ ሚገኝ የካቶሊክ ተራድኦ ወሰዱት። የድርጅቱ ሰራተኞችም ”ይህማ በቃ ሞቷል።

ከሚቀበሩት ተርታ ይቆይ” በማለት አስቀመጡት። ልጁን ያዩ የአካባቢው ሰዎችም በጨለማ ከተቀመጠበት ሰርቀው ወስደው ለአያቱ መልሰው ሰጧቸው።

በሁኔታው ደስተኛ ያልነበሩት አያቱ ግን “ለምን ይዛችሁት መጣችሁ? ልጁ አይኔ እያየ መሞት የለበትም!” በማለት እንደገና መልሰው ወደ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ወሰዱት።በዚህ ሁኔታ የተደናገጡት የድርጅቱ ሰራተኞችም “ይህን ህፃን ሞቶ ቀብረነው ነበር፤ እንዴት ተመልሶ መጣ?” በማለት ዳግም ተቀበሏቸው።

ድርጅቱም ህፃኑን በማከምና በመንከባከብ ጤንነቱን ከመለሱ በኋላ ለሴት አያቱም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኣስረከቧቸው።

ጥያቄ

እያደገና ነገሮችን መለየት ሲጀምር ህፃኑ “አባትና እናቴ የት ናቸው?” በማለት ጥያቄ ማንሳት ጀመረ። የአያቱም መልስም “ገበያ ወርደዋል፤ ይመለሳሉ።” የሚል ጊዚያዊ መልስ ነበር።

በዚህ መልስ ተስፋ አድርጎ መቆት ያልቻለው አበበ ከአያቱ ጋር መቆየት አልፈለገም። በተቃራኒው እግሩ ወደሚመራው ለመጓዝ መንገድ ጀመረ።

ኣላማጣ ከተማ ደርሶ በልመና የጎዳና ላይ እየኖረ ሳለ፤ ደርግ ወላጆቻቸውን ያጡና በየመንገዱ የሚኖሩትን ህፃናት እያሰባሰበ ወደ ሰፈራ መውሰድ ጀመረ። ከተወሰዱትም መካከል አበበ አንዱ ቢሆንም ወደ ታሰበው ቦታ አልደረሰም።

ምክንያቱም ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚወሰዱበት ጊዜ አዲስ አበባ መቅረትን መረጠ። እዚያም ቀድሞ የማያውቃቸውን ጫት መቃምና ሲጋራ ማጨስን ለመደ። ቀኑን ሙሉ ለልመና ሲዞር ይውልና ሲመሽ ካገኘበት ይተኛል።

በዚህ ጊዜ ነበር ከየት እንደመጣና ማንነቱን ለማወቅ ጥረት የጀመረው። ትግርኛ መናገር መቻሉ ከትግራይ መምጣቱን እንዲያውቅ ረዳው።

ፍለጋ

ደርግ ከስልጣን ተወግዶ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በከተማዋ የነበሩ ህፃናት በመቐለ ከተማ በተዘጋጀ ማሳደጊያ እንዲገቡ ተደረገ። ኤልሻዳይ ወይም በቀድሞ ስሙ ለስ ፕራንስ (ተስፋ) የተባለ በጎ ኣድራጎትም እሱን ለማሳደግ ተረከበዉ።

ማሳደጊያ ቢገባም አሁንም ከማሳደጊያው ተደብቆ በመውጣት ሲዞር ነበር የሚውለው። ትምህርት ቤት የገባው እድሜው ከገፋ በኋላ 13 ዓመት ሲሞላው ነበር። በውቕሮ ክልተ ኣውላዕሎ እስከ 3ኛ፣ በመቐለ ከተማ እስከ 9ኛ ክፍል፣ ከ10ኛ እስከ 12ኛ ደሞ አዲስ አበባ ተምሯል።

በዛን ወቅት ስለቤተሰቦቹ ምንም አይነት መረጃ አልነበረውም። ወላጆቹም ስለእሱ በህይወት መኖር አያውቁም ነበር። በዩኒቨርስቲ ቆይታው ስለወላጆቹ መኖር አንድ ፍንጭ አገኘ።

ይህም በመገናኛ ብዙሃን የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ሲነገር በእሱ እድሜ ያለ አበበ የሚባል ሰው ከትግራይ አካባቢ መጥፋቱን ሰማ። ከዚህ ማስታወቂያ በኋላ ወላጆቹን መፈለግ ጀመሮ ከወንድሙ ጋር በደብዳቤ ለመገናኘት ቻለ።

ለትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ ስላልነበረው ከሰዎች ወስዶ ወደ ወለጋ ነቀምት በማምራት ከወላጆቹና ከወንድሙ ጋር ለመጀመርያ ጊዜ በአካል ለመተያየት በቃ።

ለዓመታት ተለያይው የቆዩት ቤተሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ሲገናኙ መተዋወቅ እነዳልቻሉ የሚናገረው አበበ “ሁላችንም ፈዘን ቆመናል፤ ወላጅ እናቴ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ነገሮቸን በውስጧ ስታብላላ ከቆየች በኋላ መቆም ተስኗት ወደቀች። ” በማለት ይናገራል።

                                                                     

ሌሎችን መርዳት

ለጥቂት ጊዜ ከቤተሰቦቹ ጋር ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ተመልሶ መጣ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ከትምህርቱ ጎን ሰዎችን መርዳት ያዘወትር የነበረው አበበ ከተመረቀ በሁዋላም በደማቸው ኤች አይ ቪ ቫይረስ ያለባቸውን ህፃናት በሚረዳ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረ።

በወቅቱ በደማቸው ቫይረሱ ያለባቸው ህፃናት እርዳታ ለማግኘት ከትግራይ ወደ አዲስ ኣበባ ሲመጡ በማየቱ በራሱ ተነሳሽነት ሎላ ብሎ የሰየመውን የህፃናት መንከባከቢያ በ2001 ዓ.ም ኣቋቋመ። ሥራውን የጀመረው ቫይረሱ በደሟ ያለባትን የስድስት ወር ህፃን በመቀበል ነበር።

ድርጅቱን ለማቋቋም አሜሪካዊና አንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው ባልና ሚስትም የገንዘብ ድጋፍ አድርገውለታል። ከሞት አፋፍ የተረፈው የትናንትናው አበበ ዛሬ ከሞት ጋር ትግል ላይ ያሉትን ህፃናት እየተንከባከበ ይገኛል። ይህም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ህፃናትን በመንከባከብ በትግራይ ቀዳሚ የበጎ ኣድራጎት ድርጅት ሆኗል።

ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ችግር ያጋጠማቸው ህፃናት በማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት እየተመረጡ ይሰጡታል። በዚህ መሰረትም ሎላ የህፃናት መንከባከቢያ ድርጅት 20 ወላጅ አልባ ህፃናትን እያሳደገ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ በየቤታቸው ሆነው እርዳታ የሚያገኙትም ቀን በድርጅቱ ሲረዱ ይውሉና ማታ ወደየቤታችው ይላካሉ። በድምሩ 56 ህፃናት ከድርጅቱ እርዳታ ያገኛሉ።

አበበ ህፃናቶቹን ለመርዳት በመቐለ ከተማ ቀበሌ 17 ለተከራየው ቤት በየወሩ 10 ሺ ብር ይከፍል ነበረ። አሁን ግን የመቐለ ከተማ አስተዳደር 5000 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቶት በከተማዋ ደብረ ገነት ተብሎ በሚጠራ ኣካባቢ ማዕከሉን ገንብቷል።

አበበ በማዕከሉ ያሉ ልጆቹ ከምንም ነገር በላይ ትምህርት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይጥራል። “የህዝብና የሃገር ሸክም ሳይሆኑ፤ ችግር ፈቺ ዜጎች ለማፍራት እጥራለሁ። በጥሩ ሥነ-ምግባር ታንፀው ሌሎችን እንዲያስተምሩም እፈልጋለሁ።” በማለት አበበ ይናገራል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ያቋቋመው ድርጅት በእሱ ብቻ ተገድቦ እንዳይቀርና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ህዝቡ ተገቢውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪውን ያቀርባል። አበበ ፋንታሁን ባለ ትዳር ሲሆን ወላጆቹ ዛሬም ድረስ የሚኖሩተረ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወለጋ ውስጥ ነው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement