ክረምት ወለድ በሽታዎች-የጉንፋን በሽታ ጨምሮ፣ ፍሉ፣ የአፍንጫ አስም፣ሳንባ ምችና የዲያፍራሞች መዳከም የክረምቱን መግባት ተገን አድርገው የሚዘምቱብን የጤና ችግሮች ናቸው፡፡

 የክረምቱን መግባት ተከትለው የሚከሰቱ እንደ ጉንፋን ያሉ የጤና ችግሮች ለበርካቶቻችን ጤና መጓደል ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነኚህ የጤና ችግሮች የአተነፋፈስ ስርዓትን የሚያውኩና ለከፋ የጤና ችግር የሚዳርጉን ሲሆኑ በክረምቱ ወራት መግቢያና መውጫ ላይ በስፋት የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በቫይረስ ሳቢያ ከሚከሰተው የጉንፋን በሽታ ጨምሮ፣ ፍሉ፣ የአፍንጫ አስም፣ ሳይነሣይተስ፣ የሳንባ አስም፣ የመተንፈሻ ቱቦዎች መታወክ፣ ሳንባ ምችና የዲያፍራሞች መዳከም የክረምቱን መግባት ተገን አድርገው የሚዘምቱብን የጤና ችግሮች ናቸው፡፡ ክረምት ወለድ በሽታዎች በአብዛኛው በቫይረሶች፣ በኢንፌክሽኖች፣ በባክቴሪያና ፈረሶች የሚከሰቱ
ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ በአለርጂ ሳቢያ ሊመጡ የሚችሉም ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ የክረምቱን ወራት መምጣት ተከትለው ከሚነሱና ብዙዎቻችንን ለጤና መጓደል ከሚዳርጉን ክረምት ወለድ በሽታዎች መካከል ጥቂቶቹን በማንሳት፣ ስለበሽታዎቹ ምንነት፣ ምልክቶቻቸው፣ ስለሚያስከትሉት የጤና ችግርና መፍትሄዎቻቸው ባለሙያ የሚለውን እናጋራችሁ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሀኪም የሆኑት ዶክተር አብርሃም ተስፋዬ፤ ክረምት ወለድ በሽታዎችን እንዲህ ይገልጿቸዋል፡፡ ከክረምት ወለድ በሽታዎች መካከል ጉንፋን፣ የአፍንጫ አስም፣ ሳይነሳይትስ አስም፣ ሃይፐርሊን፣ ሲቲቪቲ፣ ኒምናይትስ እና በአለርጂ ሳቢያ የሚከሰቱ የመተንፈሻ አካላት ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጉንፋን ከክረምት ወለድ በሽታዎች መካከል በስፋት የሚታወቀውና ለበርካቶች ጤና መጓደል ምክንያት የሚሆነው ዋንኛው ችግር የጉንፋን በሽታ ሲሆን ይህም በቫይረስ አማካይነት የሚከሰትና ከ280 በላይ ዓይነቶች ያሉት ነው፡፡ ጉንፋን ከአፍንጫ ጀምሮ ወደ ውስጥ ያሉትን የመተንፈሻ  አካላት የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ ለአብዛኛዎቹ የጉንፋን በሽታ ዓይነቶች መነሻ የሚሆነው
ራይኖቫይረስ የተባለው ቫይረስ ሲሆን ይህ ቫይረስ ከመተንፈሻ አካላት በተጨማሪ የጆሮና የብሮንካይ አካባቢዎችንም ያጠቃል። በጉንፋን በሽታ በምንያዝበት ወቅት ዐይናችን፣ ጆሮአችን፣ ጥርሳችንና ጉንጫችን ላይ የህመም ስሜት የሚኖረንም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ጉንፋን ከቀላል የኢንፍሊዌንዛ ህመም ጋር የሚመሳሰልበት ሁኔታ አለ፡፡ ከፍተኛ ራስ ምታት፣ ሳል፣ ማስነጠስና የምግብ ፍላጎት መቀነስ በሁለቱም በሽታዎች ላይ በስፋት የሚታዩ ምልክቶች ሲሆኑ ማስነጠስ፣ ንፍጥና ቀጭን የአፍንጫ ፈሳሽ፣ ዓይን እንባ ማቆር፣ አፍንጫን ውስጠኛ ክፍል ማሳከክ፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ መንቀጥቀጥ፣ በላብ መጠመቅና ትኩሳት በጉንፋን በሸታ ወቅት የሚታዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ ከጉንፋን አምጪ  ቫይረሶች መካከል የአብዛኛዎቹ መተላለፊያ መንገድ ከትንፋሽ ይልቅ ንኪኪ ነው። እጅግ የተለመደው አስተላላፊ ንኪኪ ደግሞ በቫይረሱ የተበከለ እጅን በመጨበጥ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጉንፋን የተያዘው ሰው የነካቸውን ዕቃዎች መነካካትም ለበሽታው መተላለፊያ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ በጉንፋን የተያዘን ሰው ከመሳም ይልቅ መጨበጡ በሽታው በቀላሉ ወደጤናማው ሰው እንዲተላለፍ ያደርገዋል፡፡ ጉንፋን የያዘውን ሰው በሚጨብጡበት ወቅት የሚጨብጡት በአፍንጫ ፈሳሽ የራስ ናፕኪን  /መሃረብ/ ይዞበት የነበረውን እጁን ነው፡፡ ህመምተኛው ናፕኪን ወይም መሃረብ ካልያዘ ደግሞ አፍንጫውን ለማበስ በተደጋጋሚ እጆቹን ወደ አፍንጫው መላኩ አይቀሬ ነው፡፡ እርስዎ  ታዲያ ጉንፋን ከያዘው ወዳጅዎ ጉንፋኑ እንዳይጋባብዎ ሰግተው ወዳጅዎን ከመሳም ይልቅ መጨበጡ የተሻለ እንደሆነ አምነው፣ ይህንኑ ሲከውኑ በቫይረስ የተበከለው የወዳጅዎ እጆች ጉንፋን
አምጪ ቫይረሶችን ያቀብልዎታል ይህንኑ በቫይረሱ የተበከለ እጀዎን ከመታጠብዎ በፊት አፍንጫዎንና አይንዎን የሚነካኩበት አጋጣሚ ከተፈጠረ በቀላሉ በቫይረሱ ሊበከሉና ለጉንፋን በሽታ ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም በጉንፋን የተያዘን ሰው ከሚጨብጡት ይልቅ ቢስሙት የተሻለ ነው፡፡ የአፍንጫ አስም (ሪይናይቲስ)
በሳይንሳዊ አጠራሩ አለርጂክ (ሪይናይቲስ) የሚባለውና በተለምዶ የአፍንጫ አስም እያልን የምንጠራው ህመም በስፋት ከክረምት መምጣት ጋር ተያይዞ የሚከሰትና ክረምት ወለድ እየተባሉ ከሚጠሩ በሽታዎች መካከል የሚጠቀስ የጤና ችግር ነው፡፡ ይህ በሽታ የሚከሰተው ለአፍንጫ አካባቢ አለርጂክ በሚሆኑ ሽታዎች፣ ለምሳሌ፡- በዝናብ በራሰ አቧራ (የአፈር ሽታ) የዛፍና የተለያዩ ነገሮች ሽታዎች፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያና የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ሽታ፣ የመኪና ጭስ ለበሽታው መከሰት ዋንኛ መንስኤ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለአንድ ሰው አለርጂ የሚሆኑ ነገሮች በሌላው ሰው ላይ ችግር ላያስከትሉ ስለሚችሉ የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች አለርጂ የሆኑባቸውን ነገሮች ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በአፍንጫ አስም እና በጉንፋን መካከል ካሉት ልዩነቶች ዋንኞቹ የአፍንጫ አስም አለርጂ ቀስቃሽ ነገሩ ወደ አፍንጫችን እንደደረሰ ወዲያውኑ በደቂቃ ውስጥ ህመሙ የሚጀምር ሲሆን ጉንፋን በቫይረሱ ከተበከሉ ከቀናት በኋላ ህመሙ ይጀምራል፡፡ በጉንፋን ህመም ወቅት  የመገጣጠሚያ፣ የጀርባና የጡንቻ ህመሞች የሚከሰቱ ሲሆን በአፍንጫ አስም ላይ ግን እነዚህ ምልክቶች አይታዩም፡፡ ሳይነሳይተስ በፊት አጥንቶች አካባቢ በሚገኙና በአየር በተሞሉ ትናንሽ ቦታዎች ላይ የሚከሰት የህመም አይነት ሲሆን በተለምዶ ሳይነስ እየተባለ ይጠራል። በፊት አጥንቶች አካባቢ፣ በአፍንጫችን፣ በአፍንጫችን በስተጀርባ ያሉና በቆዳና በአጥንት ተሸፍነው በሚገኙ ውስጣቸው ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ ህመሙ ይከሰታል፡፡ ፎሮንታል፣ ማግዚለሪ፣ ኢሞማድ፣ አስፈኖይድ አና በቀኝና ግራ አፍንጫችን ላይ የሚገኙት እነዚህ ክፍት ቦታዎች በአደጋ፣ በአለርጂ፣ በኢንፌክሽንና በቲሞር አማካኝነት ችግር ሲገጥማቸው የሳይነስተስ በሽታ ይከሰታል፡፡ ከእነዚህ መካከል በስፋት የሚከሰተው በአለርጂ ምክንያት
የሚከሰተው ሳይነሳይተስ ነው፡፡ እነዚህ በፊት አጥንቶች አካባቢ የሚገኙትና በአየር የተሞሉት ትናንሽ ቦታዎች አለርጂ ቀስቃሽ በሆኑ ኢንፌክሽኖች በሚጠቁበት ጊዜ የክፍት ቦታዎቹ ሽፋን ያብጥና ወደ አፍንጫ የሚሄደው ቱቦ መሰል ቀዳዳ ይዘጋል፡፡ በዚህ ወቅትም ታማሚው ብርድ ብርድ የማለት ስሜት፣ የትኩሳት መኖር፣ እራስ ምታት፣ የአፍንጫ ማፈንና ማሳከክ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ በሽታው በተለይ ከአይን፣ ከጆሮ፣ ከጉሮሮ፣ ከሳምባና ከአንጎላችን ጋር ቁርኝት አለው፡፡ አንድ ሰው በዚህ በሽታ ቢያዝ እነዚህ የሰውነት ክፍሎችም ጥቃቱ ይደርስባቸዋል፡፡ የሳይነሳይትስ (ሳይነስ) በሽታ በተለይ በስኳር በኩላሊት፣ በቲቢና በኤድስ ህሙማን ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ በአገራችን በስፋት የሚታየውን የአለርጂ ሳይነሳይተን ለመከላከል አለርጂ
የሚሆኑባቸውን ነገሮች በጥልቀት በማጥናት ማስወገዱ፣ ዋንኛ መፍትሄ መሆኑን ባለሙያው
ይናገራሉ፡፡ የታችኛው የመተንፈሻ አካላት ህመሞች እነዚህ ህመሞች የታችኛውን የመተንፈሻ አካላት የሚያጠቁ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ኒሞኒያ፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ የሳንባ ውሃ መቋጠር የሳንባ ካንሰር፣ አጣዳፊ ብሮንካይትስና ኢንፍሎዌንዛ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በታችኛው የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች ከላይኛው የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች በበለጠ አደገኛ ናቸው፡፡ በኢንፌክሽን ከሚመጡ ህመሞች ውስጥ ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋውን የሟቾች ቁጥር የያዙት በዚሁ በታችኛው የመተንፈሻ አካላት ላይ በሚፈጠር ህመም ሳቢያ የሚሞቱ ናቸው፡፡ በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና እጅግ አደገኛ የሆነ በሽታ መሆኑንም ዶክተር አብርሃም ገልፀዋል፡፡ የክረምትን መምጣት ተከትለው የሚከሰቱና በርካቶችን ለከፋ የጤና ችግር ከሚዳርጉ በሽታዎች ለመጠበቅ የራስንና የአካባቢን ንፅህና መጠበቅና አለርጂ ከሚሆኑ ነገሮች መጠንቀቅ ጠቃሚ እንደሆነም ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡   

 

Advertisement