ግሽ ዓባይ የኪነት ቡድን የት ነው?!

 የነፃነት አቀንቃኙ ማርቲን ሉተር ኪንግ “ዓለም ሁለት ታላቅ ስጦታዎች አሏት፡፡እነሱም የአምላክ ቃል እና ሙዚቃ ናቸው” ይላል፡፡

 በአማራ ክልል ቀደም ባለው ጊዚያት ፣ሶስት ግዙፍ የባህል ቡድኖች ነበሩ፡፡የፋሲለደስ፣የወሎ ላሊበላ እና የግሽ ዓባይ ቡድኖች፡፡እነዚህ የኪነት ቡድኖች እስከ 1984 ድረስ ባህልን በኪነጥበብ በማሳየት የላቀ አበርክቶት ነበራቸው፡፡ነገር ግን የጠናከረ ተቋማዊ አደረጃጀት ስላልነበራቸው ከ 1985 ዓ/ም ጀምሮ ጠፍተው ቆይተው ከ 2006 ዓ/ም ጀምረው ደግሞ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡

 የሰባት አውራጃዎች ወይም የጎጃም ክፍለሀገር ወኪል የነበረው ግሽ ዓባይ የባህል ቡድን የተመሰረተው ሀምሌ 5 ቀን 1972 ዓ/ም ነው፡፡በ 60 ያህል አባላት የተመሰረተው ግሽ ዓባይ የባህል ቡድን፣በሙዚቃ ብቻ ሳይሆን በስነፁሁፍ ዘርፉም ይሰራ ነበር፡፡

 

እነ ይሁኔ በላይ፣ሰማኸኝ በለው፣ አንሙቴ ወዘተ የግሽ ዓባይ የባህል ቡድን ፍሬዎች ናቸው፡፡በ 13 ኛው የዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ሀገር ብሎም አፍሪካን በመወከል በፒዮንግያግ ሰሜንኮርያ የኪነጥበብ ድግሱን አቅርቧል፡፡አቅርቦም ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ተችሮታል፡፡

 

ከ 1977 ዓ/ም በሀገሪቱ በተከሰተው ድርቅ የኪነት ቡድኑ ከመንግስት በጀት አጣ፡፡በእርግጥ ግሽ ዓባይ የኪነት ቡድን ቀድሞውንም ብዙ ድጋፍ የሚያገኘው ከህዝብ ነበር፡፡ግን ህዝቡ ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት ግሽ ዓባይ ተዘነጋ፡፡በ 1978 ዓ/ም ግሽ ዓባይ ተደራጅቶ እስከ 1984 ዓ/ም ዘልቆ ነበር፡፡

 

ከሽግግር መንግስቱ በኋላ ግሽ ዓባይ የባህል ቡድን በባህርዳር መሪ መዘጋጃቤት እንዲመራ በሚል የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ደብዳቤ ፅፈው ነበር፡፡ነገር ግን መሪ ማዘጋጃ ቤቱ የኪነት ቡድኑን ለመደገፍ አቅም አነሰው፡፡ግሽ ዓባይም ፈረሰ ይላል ጋዜጠኛ ደረጀ ጥበቡ በኪነት ቡድኑ ዙሪያ ባቀረበው አጭር ጥናት፡፡

 

የግሽ ዓባይን የኪነት ቡድን ወደ ነበረበት ግርማ ሞገሱ ለመመለስ ከ 4 ዓመት በፊት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እርምጃ ጀምሯል፡፡የግሽ ዓባይ የባህል ቡድን ተመስርቷል፡፡የቱን ያህል እየተጓዘ ነው? በሌላ ጊዜ የምመለስበት ሆኖ የባህል ቡድኑ ከሰምኑ የፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ የሙዚቃ ቀንን ያከብራል፡፡ከባህል ና ቱሪዝም ተቋማት፣ከኢትዮጲያ የሙዚቃ ማህበራት እና ከሌሎች አካላት ጋር ሆኖ ባለውለታዎቹን ይሸልማል፡፡የኪነት እንቅስቃሴውን ይቃኛል፡፡

 

 

 

Advertisement