የጣልያኗ “የአለማችን ጤናማ መንደር” ነዋሪዎች የረጅም እድሜ ሚስጢሮች::

                                          

በደቡባዊ ጣሊያን የምትገኘው የፒዮፒ መንደር “የአለማችን ጤናማ መንደር” የሚል ስያሜን ካገኘች ሰነባብታለች።

አብዛኞቹ የፒዮፒ ነዋሪዎች ከ100 አመት በላይ የሚኖሩ ሲሆን፥ ጤናቸውም የተስተካከለ ነው ተብሏል።

በመንደሯ ነዋሪዎች ላይ ጥናት ያደረጉት የልብ ሀኪም ዶክተር አሲም ማልሆትራ፥ አብዛኞቹ የፒዮፒ ነዋሪዎች የስኳር ፍጆታቸው በጣም አነስተኛ መሆኑን ያሳያል።

በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ስኳር የሚጠቀሙት የመንደሯ ነዋሪዎች ለስኳር በሽታ እና የልብ ህመም የሚጋለጡት አልፎ አልፎ ነው ብሏል ጥናቱ።

ጭንቀት ማስወገዳቸው እና ከሰባት ስአት በላይ የሌሊት እንቅልፍ ማግኘታቸው ከአመጋገባቸው በተጨማሪ ጤናቸውን ለመጠበቅ ረድቷቸዋል ነው ያሉት ዶክተር ማልሆትራ።

ፒዮፒ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሜዲትራኒያን ምግብ መገኛ ተደርጋ ተመዝግባለች።

በብሪታንያ የልብ ህመም እና ከልክ ያለፈ ውፍረት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን በተመለከተ ሰፊ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ማልሆትራ፥ የበዛ የስኳር እና የተጣራ ካርቦሃይድሬት ፍጆታ ለታይፕ 2 የስኳር ህመም፣ ከልክ ላለፈ ውፍረት እና ለልብ ህመም እያጋለጠ ይገኛል ብለዋል።

አትክልቶችን መመገብ፣ ማጨስ ማቆም እና ጭንቀት የሚያስከትሉ ነገሮችን ማስወገድ ስር የሰደዱ በሽታዎችን ጭምር ለመከላከል ከየትኛውም የህመም ማስታገሻ መድሃኒት የበለጠ ውጤታማ መሆኑን በፒዮፒ መንደር ነዋሪዎች አረጋግጠናል ነው ያሉት ዶክተር ማልሆትራ።

በአካባቢያቸው ምንም አይነት ሱፐርማርኬት የሌላቸው የፒዮፒ ነዋሪዎች አትክልቶችን፣ አሳ፣ የወይራ ዘይት፣ ስጋ፣ ወተት እና የወተት ተዋፅኦዎችን ነው የሚመገቡት። በኦሜጋ 3 የበለፀጉ ምግቦችን ያዘወትራሉ። ፓስታና እና ዳቦም አልፎ አልፎ ይመገባሉ።

ስጋም ውድ በመሆኑ አብዝተው አይመገቡም ያሉት ተመራማሪው፥ በእያንዳንዱ ምግባቸው ውስጥ የወይራ ዘይት ይገባበታል፤ ይህም ለጤናማ እና ረጅም እድሜያቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።

የፒዮፒ ነዋሪዎች እንደ ምዕራባዊያኑ ክብደት ለመቀነስ የሚያስችል መደበኛ ስፖርት ባይሰሩም፥ ብዙ ጊዜ በእግራቸው ይንቀሳቀሳሉ።

በመንደሯ ከስአት በኋላ ለተወሰነ ደቂቃ መተኛት (ናፕ መውሰድ) የተለመደ ተግባር ነው።

አመጋገብን አለማስተካከል የአካል እንቅስቃሴ ካለማድረግ፣ ሲጋራ ከማጨስ እና አልኮል ከመጠጣት በበለጠ ለበሽታ እና ህልፈት እንደሚዳርግ አጥኝው ጠቁመዋል።

“የስብ ይዘታቸው አነስተኛ”፣ “ከግሉቶን ነፃ” እና “ለልብ ተስማሚ” የሚል ፅሁፍ ተለጥፎባቸው የሚሸጡ ምግቦች በጤናችን ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ቀላል አይደለም ብለዋል ዶክተር ማልሆትራ።

ዶክተር ማልሆትራ እንደሚሉት የፒዮፒ ነዋሪዎችን አመጋገብ መከተል ከልብ ህመም ጋር በተገናኘ በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ለህልፈት የሚዳረጉ 20 ሚሊየን ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ያስችላል።

ከልክ ያለፈ ውፍረት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ለመከላከል የሚመደብ በቢሊየን የሚቆጠር በጀትንም ለመቀነስ ያግዛል ተብሏል።

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk/

 

Advertisement