የክትባት መርፌ ለሚፈሩ አዲስ የመከተቢያ ዘዴ አግኝተናል ይላሉ ባለሙያዎች::

                                                           

ክትባቶችን ለመውሰድ መርፌ መወጋት የግድ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል፤ ሆኖም ግን አንዳንዶች መርፌውን በመፍራት እስካለመከተብ ሲደርሱ ይስተዋላል።

አስፈላጊ የሆኑ ክትባቶችን አለመከተብ ደግሞ በጤናችን ላይ የሚያመጣው ጉዳት ይታወቃል።

ተመራማሪዎች ከዚህ በኋላ በመርፌ ፍራቻ ክትባት አለመከተብ ሊያከትምለት ነው ያሉ ሲሆን፥ ከህመም የፀዳ እና አዲስ የመከተቢያ መንገድ ማግኘታቸውንም አስታውቀዋል።

አዲሱ የመከተቢያ መንገድ በቆዳ ላይ የሚለጠፍ ፕላስተር መሳይ ነገር ሲሆን፥ ይህም ፀጉር መሳይ ጥቃቅን መርፌዎችን የያዘ ነው።

በፕላስተሩ ላይ ያሉት ጥቃቅን መርፌዎችን ቀስ እያሉ ቆዳችንን ከፍተው ወደ ውስጥ የሚገቡ መሆናቸውን ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

በፕላስተሩ አማካኝነት ክትባት መውሰድ የሚፈልጉ ሰዎችም ፕላስተሩን ቆዳቸው ላይ መለጠፍ ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው ሲሉም ተመራማሪዎቹ አብራርተዋል።

ይህም በርካቶችን ይረዳል ያሉት ተመራማሪዎቹ፥ በተለይም መርፌ የመወጋት ፍራቻ ያለባቸው ሰዎች በዚህ መንገድ የሰውነታቸውን በሽታ የመከላከል ስርዓት ማስጠበቅ ይችላሉ ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፕላስተሩን አሁን በጥቅም ላይ ያሉት እንደ ኢንፉሌንዛ ያሉ የክትባት አይነቶች የግድ ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ አይጠበቅብምን ተብሏል።

የመድሃኒት መደብሮች (ፋርማሲዎች) ልክ እንደ ሌሎች መድሃኒቶች መደርደሪያዎቻቸው ላይ አስቀምጠው መሸጥ ይችላሉ።

አዲሱን የመከተቢያ ዘዴ በፈቃደኝነት የሞከሩ ሰዎችን ለክትባት መርፌ ከመወጋት ይልቅ ይህንን አዲስ የመከተቢያ መንገድ እንመርጣለን ሲሉ ተሰምተዋል።

አዲሱ መከተቢያ በአሜሪካ ብሄራዊ የጤና ኢኒስቲቲዩት የገንዘብ ድጋፍ በጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የተሰራ መሆኑም ተነግሯል።

በዩኒቨርሲቲው የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማርክ ፕራውኒትዝ “ፕላስተሩን በሚያጎላ ነገር ብንመለከት በርካታ ጥቃቅን መርፌዎችን ይታዩናል፤ ሆኖም ግን ፕላስተሩ ላይ ያሉት መርፌዎች ምንም አይነት ህመም ሳይፈጥሩ ወደ ቆዳችን መግባት የሚችሉ ናቸው ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ሌሎች ተመራማሪዎችም በቆዳ በኩል የሚሰጠው ህክምና ከህመም ነጻ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።

በአውስትራሊያ የሚገኙ ተመራማሪዎችም “ናኖፓች” የተባለ እና በጣም አነስተኛ መርፌዎች የተገጠሙለት አዲስ ቴክኖሎጂ ዲዛይን ማድረጋቸውም ተሰምቷል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement