የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስቀመጠውን ቀነ ገደብ ተጠቅመው ገንዘቡን አልመለሱም ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ከማውጣት በተጨማሪ ፎቷቸውን እና የባንክ ሒሳብ ቁጥራቸውንም በተለያዩ ዙሮች ይፋ በማድረግም ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. በገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ላይ ባጋጠመው ችግር ምክንያት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት እንደነበር ካስታወቀ ሰነባበተ።

ደንበኞች በአካውንታቸው ካለው ገንዘብ በላይ ብር ወጪ በማድረግ ወይም በማዘዋወር ከተወሰደበት ብር ሦስት አራተኛውን ማለትም ከ620 ሚሊዮን ብር በላይ መልሶ በእጁ ማስገባቱንም ባንኩ ገልጾ ነበር።

ባንኩ “ጤናማ ያልሆነ” ባለው መንገድ ደንበኞቹ የወሰዱበትን ገንዘብ እንዲመልሱ በተለያዩ መንገዶች ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆኑም ያላቸው የ565 ሰዎች ስም ዝርዝር፣ የሂሳብ ቁጥር እና ሂሳባቸው የተመዘገበበትን ቅርንጫፍ ይፋ አድርጓል።

ባንኩ ያስቀመጠውን ቀነ ገደብ ተጠቅመው ገንዘቡን አልመለሱም ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ከማውጣት በተጨማሪ ፎቷቸውን እና የባንክ ሒሳብ ቁጥራቸውንም በተለያዩ ዙሮች ይፋ በማድረግም ላይ ይገኛል።

የደንበኞችን ግላዊ መረጃ እና ምስል ይፋ ማድረግ ምን ያህል ሕጋዊ ነው የሚለው ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።

በአገሪቱ ሕግ መሠረት የሰዎችን ፎቶ ማውጣት እና መለጠፍ ክልክል መሆኑን የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ የሆኑት አቶ ታምራት ኪዳነ ማርያም፣ “ሕግ እንደ ተርጓሚው ነው” በማለት ይህ የሚፈቀድበት ልዩ ሁኔታ መኖሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ፖሊስ እና መሰል ተቋማት የሚፈለግን ሰው ምስል መለጠፍ ይችላሉ። ለፍርድ ወይንም ለፍትህ ሲባልም የሰውየው ፈቃድ ሳይጠየቅ ይፋ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ያስረዳሉ።

በክፉ ‘የታወቀ ሰው’ ከሆነ ፎቶውን መለጠፍ የሚቻልበት ዕድል መኖሩም በማንሳት፤ ይህ ‘የታወቀ ሰው’ የሚለው አተረጓጎም ግን ሊሰፋም ሊጠብም ይችላል።

የሕግ አተረጓጎም

የባንክ ሥርዓቱ ስለፈቀደ ብቻ ደንበኞች ከገቡት ውል ውጪ ካስቀመጡት ገንዘብ በላይ በመውሰድ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ፈጽመዋል ሲል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደጋግሞ ይናገራል።

“ማንኛውም በክፉ ሥራው የታወቀን ሰው ፎቶ ማውጣት እነዚህን [ገንዘብ ያወጡትን ሰዎች] ይጨምራል ካልን ባንኩ መለጠፍ ይችላል ወደሚል ድምዳሜ ሊያደርሰን ይችላል” ሲሉ የጉዳዩን አንድ መልክ የሕግ ባለሙያው ያስቀምጣሉ።

ትርጓሜው በመጥፎ ሥራቸው የታወቁ ወይንም በሕዝብ ታዋቂ የሆኑትን የሚመለከት እንጂ በባንኩ ገንዘብ ዝውውር ላይ የተሳተፉትን አይመለከተም ካልን ደግሞ ፎቶ መለጠፍ አይቻልም ወደሚል መደምደሚያ ያደርሳል እንደማለት ነው።

ለዚህ ነው እንግዲህ የሕግ ባለሙያው አቶ ታምራት “ሕግ እንደ ተርጓሚው ነው” የሚሉት። አንደኛው ክፍተትም የሚነሳው እዚህ ላይ ነው።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለ ውል ነው። በባንኩ እና በደንበኛው መካከል ውል አለ። አንድ ሰው የባንክ ደንበኛ ሲሆን የሚገባቸው ውሎች አሉ። ይህ ደግሞ የባንኩንም ሆነ የደንበኛውን መብት እና ግዴታ የያዘ ነው። ሌላኛው አከራካሪ ጉዳይ እዚህ ጋር ይነሳል።

በውሉ መሠረት ባንኩ ተገቢ ያልሆነ ገንዘብ ወደ ደንበኞች ሂሳብ እንዳይገባ ጥበቃ ማድረግ አለበት።

‘ውል በቅን ልቦና ነውና መፈጸም ያለበት’ ደንበኞችም ሂሳባቸው ውስጥ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ሲገባ ማሳወቅ አለባቸው። ሂሳባቸው ውስጥ ካለው በላይ ማውጣትም የለባቸውም።

“ባንኩ ያጋጠመው ችግር ከአቅም በላይ በሆነ የኮምፒውተር ችግር ሊሆን ይችላል” የሚሉት አቶ ታምራት ደንበኞችም ካላቸው ገንዘብ በላይ ካወጡ ግን “ውል መጣስ ነው። ውሉ የሚጣሰው ግን በማወቅ እንደሚሆነው ሁሉ ሂሳባቸው ውስጥ ስንት እንዳለ ባለማወቅ ሊጣስም ይችላል” ብለዋል።

“ዞሮ ዞሮ ግን በሁለቱም ወገኖች በኩል የውል ጥሰት ነው የሚሆነው። በባንኩ በኩል የደንበኞች ያልሆነ ሂሳብ ወደ ደንበኞች ሂሳብ እንዳይገባ ማድረግ አለበት። ደንበኞች ደግሞ ተገቢ ያልሆነ ገንዘብ ሲገባ ማውጣት አይገባቸውም። ይህ ሕገወጥ ብልጽግና ነው የሚሆነው። ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና አውቀህም ሳታውቅም ልታገኝ ትችላለህ። ዞሮ ዞሮ መመለስ ይኖርበታል” ሲሉ ይገልጻሉ።

ሌሎችም መታየት ያለባቸው ዝርዝር ፍሬ ነገሮች መኖራቸውም ይነሳል።

እውነትን እንደ መከላከያ

“የኮምፒውተር ሲስተሙ (ሥርዓቱ) ምንድን ነው ያደረገው? የደንበኞች ሂሳብ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ገንዘብ ከተተ ወይንስ ያንን ሳያደርግ ከሂሳባቸው በላይ ሲጠይቁ የሚያስተላልፍበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው? የሚለው መታየት አለበት” ይላሉ።

ደንበኞች ሂሳብ ውስጥ እላፊ ገንዘብ ገብቶ ከሆነ የሚታይበት መንገድ እና ደንበኞች ሂሳብ ውስጥ ገንዘቡ ሳይገባ ደንበኞቹ ካላቸው በላይ ሲጠይቁ ገንዘብ ከሰጠ ደግሞ በሌላ መልኩ የሚታይ ይሆናል።

ስማቸው እና ፎቷቸው እየተለጠፈ የሚገኙት ደንበኞችን በተመለከተም ‘በትክክል ያወጡ ናቸው ወይንስ ሳያወጡ ስማቸው የተለጠፉ ናቸው የሚለው ነገርም መታየት አለበት።’

“አንድ ሰው እላፊ ገንዘብ ሳያወጣ በስህተት፣ በስም ስህተት ወይንም በአጻጻፍ ስህተት ስሙ ወይንም ፎቶግራፉ ከወጣ በጣም ትልቅ ስህተት ነው፤ ያስጠይቃል” ይላሉ የሕግ ባለሙያው።

ስማቸው እና ፎቷቸው የተለጠፈባቸው ሰዎች በትክክልም ባንኩ እንደሚለው ገንዘቡን ወስደው ከሆነ ግን ባንኩን በስም ማጥፋት የመጠየቁ ዕድል አይኖርም።

“[አንድ ሰው] በትክክል ገንዘብ ካወጣ በሕጉ መሠረት እውነት መከላከያ ነው። ይህ ሰው ከነበረው ገንዘብ እላፊ አውጥቷል ከተባለ እና እውነት ከሆነ ስም ቢጠፋም ያ ነገር እውነት ከሆነ ስም ጠፋ ሊባልም አይችልም። ምክንያቱም እውነት መከላከያ ነው የሚሆነው።”

እውነት ሆኖም ግን ባንኩ ሊጠየቅ የሚችልበት ዕድል አለ።

ሊጠየቅ የሚችለውም እውነቱን የተናገረው ለመጉዳት ካሰበ ብቻ ነው የሚሆነው። በክፋት ተነሳስቶ ከሆነ የግል መረጃውን ያውጣው ሊጠየቅ ይችላል።

ፎቶ እና ሌሎች ግላዊ መረጃዎች በባንኩ ይፋ የተደረጉት በሦስት ጉዳዮች ሊሆን እንደሚችል አቶ ታምራት ያነሳሉ።

“በቀናነት ካየነው ያላወቁ አይተው እንዲመልሱ ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ስማቸውን አይተው ደንግጠው ገንዘቡን እንዲመልሱ ለማድረግም ሊሆን ይችላል። ሰዎችን ለማስጨነቅ እና ሃሳባቸውን ሳይቀይሩ ቶሎ እንዲመልሱ ለማድረግም ሊሆን ይችላል” ሲሉ ያስረዳሉ።

ግላዊ መረጃን ይፋ ማድረግ

ደንበኞች ፎቷቸውን ለባንኩ የሚሰጡት ባላቸው ውል መሠረት ነው። በባንኮች እና በደንበኞች መካከል ጥብቅ ግንኙነት አለ። ባንኩ ምስጢር የመጠበቅ፣ ያላቸውን ገንዘብ፣ የሰጡትንም አድራሻ ለማንም አሳልፎ ያለመስጠት የውልም የሕግም ግዴታ አለበት።

በባንኩ በኩል በዚህ መልኩ ያገኘውን መረጃ ተጠቅሞበታል። ገንዘቡን የወሰዱበትን ማንነት ለማሳወቅ ፎቶውን በመለጠፍ ተጠቅሞበታል።

ደንበኞች ደግሞ በውል ከተሰጣቸው አግባብ ውጪ የማይመለከታቸውን ገንዘብ አውጥተዋል።

“አውቀውም፣ ሳያውቁም ይሁን ከ’አምላክ’ የተሰጠኝ ነው ብለውም ይሁን ገንዘቡን አውጥተዋል። ይህ ከውሉ ውጪ ነው” በውሉ መሠረት አንድ ደንበኛ ካለው ገንዘብ በላይ ካወጣ ለባንኩ ማሳወቅ እና መረጋገጥ አለበት። ትርፍ ከሆነ ለባንኩ መመለስ ይገባል። በዚህ መሠረት ደንበኞች ካላቸው በላይ ገንዘብ ካወጡ በእነሱም በኩል ቢሆን የውል ጥሰት አለ ማለት ነው።

በዚህ ምክንያትም የደንበኞችን ፎቶ ማውጣት የሚለው ጉዳይ ‘አሻሚ’ ይሆናል።

እንደ ሐኪም፣ ጠበቃ እና መሰል ሙያዎች የደንበኞቻቸውን ምስጢር መጠበቅ ግዴታ ቢኖርባቸውም ጉዳዩ በወንጀል ሕግ ሊታይ የሚችልበት ዕድልም አለ።

ሆኖም ስም ከማጥፋት አኳያ ደንበኛው ፈጸመው የተባለው ጉዳይ አውነት ከሆነ “እውነት መከላከያ ነው የሚሆነው” በማለት ደግመው አንስተዋል።

ከስም ማጥፋት ጋር ተያይዞ ባንኩ የሄደበት መንገድም ከግምት የሚገባ ጉዳይ ይሆናል።

“መረጃው የወጣው ሰዎች ተቀባብለውት ያልመሰሱ እንዲመልሱ ነው? ወይስ እምቢተኞችን ማስገደጃ ታክቲክ ነው? የሚለው በማስረጃ መታየት አለበት። ሁለቱንም ይመስላል። በአንድ በኩል ለማሳወቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እምቢተኞች እንዲመልሱ ግፊት ለማድርግ ይመስላል” ይላሉ ጠበቃው አቶ ታምራት።

በሌላ በኩል ደግሞ ባንኩ ሕግን መጠቀም ሲገባው ሕጉን በራሱ መዳፍ በማስገባት ማስገደድ ይችላል ወይ? የሚለውም የሚታይ ነገር ነው።

ለአቶ ታምራት ባንኩ “ፎቶ እና ስም ዝርዝር ለጠፈ እንጂ የሕግን ኃይል በእጁ አስገብቶ ፖሊስ ልኮ ወይንም በራሱ ሥልጣን ከራሳቸው ሂሳብ ውስጥ ገብቶ የመውሰድ እንደዚህ ዓይነት ነገር አልማሁም። እንደዚህ ከሆነ ደግሞ [የግል መረጃዎችን] መለጠፍ ይቻላል” ይላሉ።

መረጃዎቹን መለጠፉ በፍትሀብሔር እና በወንጀል ሕጎች የሚታይ ይሆናል። የሙያ ምስጢርን ማውጣትም በዚሁ የሚታይ ይሆናል።

ባንኩ ያቀርበው ምክንያት እውነት ከሆነ ግን እውነትነቱ ነጻ ያወጣዋል ሲሉ ይገልጻሉ።

ሌላው የሚታየው የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ነው ወይ የሚለው ጉዳይ ነው።

አንድ ሰው ጥቃት ሲደርስበት ሕገ ወጥም ቢሆን የደረሰበትን ጥቃት ለማስወገድ ተመጣጣኝ ወይም ተመሳሳይ ጥቃት በመፈጸም መብቱን መከላከል ይችላል።

አቶ ታምራት ይህንን “ሕገ ወጥነትነትን በሕገ ወጥነት መከላከል የሚቻልበት ሁኔታ አለ” ሲሉ ያስረዳሉ።

በዚህ በኩል ደግሞ ባንኩ የወሰደው እርምጃ ራስን መከላከል ነው ወይ የሚለው ይታያል። ሕጋዊ መከላከል የሚፈጸመው ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ወይንም ሲቃረብ ነው። ወይንም እንደተፈጸመ ወዲያው መሆን አለበት።

“ጥቃቱ ከተፈጸመብህ በኋላ ቆይተህ የምትወስደው የአጸፋ እርምጃ ሕጋዊ መከላከል ውስጥ አይወድቅም። በአንድ በኩል ሰዎቹ ገንዘቡን ከመውሰዳቸው በፊት ቢሆን ይህንን ማደረግ ይቻላል። ከወሰዱ በኋላ ግን ሕጋዊ መከላከል ነው የሚለው ሊያከራክር ይችላል” ብለዋል።

ዞሮ ዞሮ የባንኩ እና ደንበኞቹ ጉዳይ ከተለያዩ ሕጎች አንጻር መታየት አለበት የሚሉት አቶ ታምራት “ጠቅለል አድርጎ ይህ ነው ሊባል አይችልም። በብዙ መንገድ ሊታይ ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል። ለዚህም ነው ሕግ እንደ ተርጓሚው ነው የሚሉት።

ምንጭ: BBC NEWS አማሪኛ

Advertisement