በስራ ሰዓት ከመቀመጥ ይልቅ ቁሞ መስራት ውፍረት ለመቀነስ ይረዳል ተባለ | Working While Standing In Office Helps to Reduce Over Weight

                                          

ቀኑን በሙሉ ተቀምጦ እየሰሩ መዋል በጤናችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ጥናቶች ያረጋገጡ ሲሆን፥ በቅርቡ የተሰራ ጥናት ደግሞ ለሰውነት ውፍረት እንደሚዳርገን አረጋግጧል።

ቀኑን ሙሉ ተቀምጦ ከማሳለፍ ይልቅ ቢያንስ በቀን ለ6 ሰዓት መቆም በዓመት እስከ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የሰውነት ክብደትና ውፍረትን ለመቀነስ እንደሚረዳም ጥናቱ አረጋግጧል።

በዚህ መልኩ በተከታታይ ስራቸውን ቆመው የሚሰሩ ሰዎች በ4 ዓመት ውስጥ እስከ 10 ኪሎ ግራም የሰውነት ክብደት መቀነስ ይቻላሉ ተብሏል።

በአሜሪካ ሚኔሶታ የሚገኘው የማዮ ክሊኒክ ተመራማሪዎች በሰሩት የጥናት ውጤት መሰረት በአውሮፓ ያሉ ሰዎች በቀን በአማካኝ ከ3 ነጥብ 2 እስከ 6 ነጥብ 8 ሰዓት ተቀምጠው ሲያሳልፉ፤ በአሜሪካ ደግሞ አንድ ሰው በቀን ከ7 ሰዓት በላይ ተቀምጦ ያሳልፋል።

ተመራማሪዎቹ ለረጅም ሰዓት ቁጭ ብሎ መዋል ከመጠን በላይ የሰውነት ክብደት፣ የብህ ህመም እና የስኳር በሽታ እንዲከሰትብን ምክንያቶች ናቸው ያሉ ሲሆን፥ ስራን ቁሞ መስራት ግን ለጤናችን የሚያስገኘው ጠቀሜታ በዚህ በተቃራኒው ይገለጻል ይላሉ።

ለረጅም ሰዓት መቆም ብዙ ካሎሪ ለማቃጠል ይረዳል የሚሉት ተመራማሪዎቹ፥ አንድ ሰው ቆሞ የሚሰራ ከሆነ በአንድ ደቂቃ ውስጥ 0 ነጥብ 15 ካሎሪ እንደሚያቃጥል ለይተወዋል።

በማዮ ክሊኒክ ተመራማሪ የሆኑት ፍራንሲስኮ ሎፔዝ ጄሚኔዝ፥ ረጅም ሰዓት መቆም በተለይም ስራቸው ከጠረጴዛ ጋር ተያይዞ ለሚውል ሰው አስቸጋሪ ሊመስል ይችላል ይላሉ።

ነገር ግን በቀን ውስጥ ለ12 ሰዓት ተቀምጦ የሚሰራ አንድ ሰው ግማሽ ያክሉን ቆሞ ቢሰራ ከፍተኛ የጤና ጠቀሜታ ያገኛል ብለዋል።

በማዮ ክሊኒክ ክሊኒካል ዳይሬክተር ሞሀመድ ጣሃ፥ በስራ ቦታችን ላይ ቆመን ለመስራት የሚያመች ጠረጴዛ እና የሚያመች ሁኔታ ከሌለ ሌሎች ማድረግ ያለብንን ነገሮች እንዲ ይመክራሉ፦

• ስልክ በምናናግርበት ጊዜ መቆም

• የስልካችንን የማንቂያ ደውል በየ30 ደቂቃ ልዩነት በሞሙላት ስልካችን ምልክት ሲሰጠን ለ1 ወይም 2 ደቂቃ ተነስተን መንቀሳቀስ

• ስብሰባዎችን አንዳንዴ በቁም አሊያም የእግር ጉዞ እያደረግን ማካሄድ 

• አቀማመመጣችንን የተስተካከለ ለማድረግ መሞከር።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement