ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት ራሳችን ልናደርግ የምንችለዉና የህክምና እገዛ የሚያስፈልግበት

አንድ ሰዉ 60 ዓመት ይኖራል ቢባል በአማካይ 20ዓመታትን የሚያሳልፈዉ በእንቅልፍ ነዉ፡፡ ጥሩ እንቅልፍ ፦ በቀላሉ መተኛት መቻል፣ ያልተቆራረጠ እንቅልፍ እና ቀኑን ንቁ ሆኖ መዋልን ያጠቃልላል፡፡ ለሊት ላይ ጥሩ እንቅልፍ አለመተኛት ቀን መነጫነጭ፣ ትኩረት አለማድረግ፣የማስታወስ ችግር፣ ድብርትና ጭንቀት ያስከትላል፡፡ በሌላ መልኩ ሀሳቦቻችን፣ ስሜቶቻችንና በአጠቃላይ የአእምሮ ጤንነታችን የእንቅልፍ ስርአታችንን ሊያዛባዉ ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ የእንቅልፍ ችግሮች ተፈጥሮአዊና ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ ለምሳሌ ፈተና ፣ ከፍቅር ጓደኛ ጋር አለመግባባት፣ የምንወደዉ ሰዉ በሞት ሲለየን የሚከሰቱ ሲሆኑ፤ሌሎች የእንቅልፍ ችግሮች ለረጅም ጊዜ የሚቆዩና የህክምና እገዛ የሚያስፈልጋቸዉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት በራሳችን ልናደርግ የምንችላቸዉ፡፡

ማድረግ የሚገባን

– ቋሚ የመተኛ ሰዓት መመደብ
– ቋሚ የመነሻ ሰዓት መመደብ (አእምሮአችን መደበኛ የሆነ የእንቅልፍ ፕሮግራም እንዲይዝ ያደርጋሉ ፡፡)
– የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ (ጠዋት ጠዋት ቢሆን ይመረጣል )
– እራት በጊዜ መመገብ ( ከመተኛት ሶስት-አራት ሰዓት ቀደም ብሎ )
– መኝታ ክፍልን ብርሀን ያልበዛበት፣ ጸጥተኛና ቀዝቀዝ ያለ ማድረግ

ማድረግ የሌለብን

– አልጋ ላይ ሆኖ ስልክ ማወራት፤ ቻት ማደረግ
– አልጋ ላይ ሆኖ ቲቪ ማየት፣ ሬዲዮ ማዳመጥ
– አነቃቂ ነገሮች አመሻሽ ላይ መጠቀም
– አልኮል መዉሰድ (ለአጭር ጊዜ የሚረዳ ቢመስልም ከጊዜ በኃላ የተቆራረጠ እንቅልፍ ያስከትላል ፡፡)

ከላይ የተዘረዘሩት ቀላል ዘዴዎች ስለሆኑ የማይሰሩ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ የእንቅልፍ ችግር ያለባቸዉን ሰዎች ያለ መድኃኒት ጥሩ እንቅልፍ እንድተኙ ረድተዋል፡፡

ከእንቅልፍ ጋር ተያይዞ ህክምና የሚያስፈልጋቸዉ

-ከላይ የተጠቀሱትን አድርገን አሁንም በቂ እንቅልፍ የማናገኝ ከሆነ
– ተያያዞ የድብርት ስሜት የሚሰማ ከሆነ
-ተያይዞ ጭንቀት ካለ
-በአጠቃላይ የእንቅልፍ ችግሩ በሥራችን ወይም በማህበራዊ ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ የሚያመጣ ከሆነ ፡፡

ጥሩ እንቅልፋ ሲኖረን ጥሩ የአዕምሮ ጤና ይኖረናል፡፡
የህይወታችንን አንድ ሶስተኛ ስንንከባከብ ሁለት ሶስተኛው ላይ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንችላለን፡፡

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

4 Comments

Comments are closed.