ረጅም ዕድሜን ለመጎናፀፍ ማድረግ ያለብን እና የሌለብን የትኞቹን ይሆን?

በአኗኗር ዘይቤያችን ላይ መጠነኛ ለውጥ በማድረግ ረጅም ዕድሜን መኖር እንችላለን ይላል የሄልዝ ዶት ኮም መረጃ።

የቅርብ ጊዜ ጥናት እንዳመለከተው ማጨስ፣ አብዝቶ አልኮል መጠጣት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና በቂ የአትክልት እና የፍራፍሬ ውጤቶችን አለመመገብ ረጅም ዕድሜ እንዳይኖረን ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ይገኙበታል።

ይሁንና እነዚህን እና ሌሎች ጤናማ የህይወት ዘይቤ መንገዶችን በመከተል ቢያንስ ከዕድሜያችን ላይ 12 ዓመትን መጨመር እንችላለን ይላል መረጃው።
በመሆኑም ከተወሰኑ ልምዶች እንራቅ፣ አንዳንዶቹን ደግሞ እንተግብራቸው ሲል ይመክራል።

  1. ከልክ በላይ አይመገቡ

በዓለም ዙሪያ ረጅም ዕድሜ መኖርን በተመለከተ ብዙ ፅሁፎችን የፃፉት ደራሲ ዳን በትነር እንደሚሉት፥ ከ100 ዓመት በላይ መኖርን ካቀድን የምንመገበውን ምግብ መመጠን ግድ ይለናል።

ቀደምት የጃፓን ሰዎች እንደሚያደርጉት 80 በመቶ ያህል መጥገባችን ሲሰማን መመገባችንን ማቆም ይኖርብናል ሲሉም ምክራቸውን ያክላሉ።

የቅዱስ ልዊስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡትም አመጋገብን መመጠን በቶሎ እንዳናረጅ ያደርጋል።

በየቀኑ የምንወስደውን የካሎሪ መጠን መመጠኑ በሰውነታችን የቲ 3 (የምግብ መዋሃድ ስርዓትን ዝግ እንዲል በማድረግ እርጅናን የሚያፋጥነው የታይሮይድ ሆርሞን) ምርትን እንዲቀንስ ያደርጋል።

2. ቴሌቭዥንዎ ላይ ጊዜዎን አያጥፉ

ለረዥም ጊዜ ቴሌቭዥን መመለከት በጤናዎ ላይ ችግር እንደሚያመጣ ይገንዘቡ።
እ.ኤ.አ በ2010 የተደረገ ጥናተ እንደጠቆመው፥ በቀን ለአራት ሰዓት እና ከዚያ በላይ ቴሌቭዥን በመመልከት የሚያሳልፉ ሰዎች ፤ በቀን ከሁለት ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ የቴሌቭዥን መስኮትን ከሚቃኙት የሞሞት ዕድላቸው 46 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
ቴሌቭዥን ሳልመለከት መዋል አልችልም የሚሉም ከሆነ የተወሰነ ጊዜ ፋታ መውሰድ ሌላ አማራጭ እንደሆነም ነው የተጠቆመው።

ቴሌቭዥን አዘውትሮ መመልከት በአጠቃላይ የመሞት ዕድልን በ11 በመቶ፣ በልብ ችግር የመሞት ዕድልንም በ18 በመቶ ከፍ ያደርጋልም ተብሏል።

3. ከልክ ካለፈ የፀሃይ ብርሃን ይጠበቁ

ከልክ ያለፈ የፀሃይ ብርሃን ቆዳን በመጉዳት ካንሰርን ያስከትላል።
በተጨማሪም በቆዳ ላይ የሚወጡ ምልክቶች እንዲበራከቱ እና ለተለያዩ የቆዳ በሽታዎች በማጋለጥ ዕድሜያችንን ሊያሳጥር ይችላል።

4. ከብቸኝነት ይራቁ

ጥናቶች ብቸኝነት ለልብ ህመም የመጋለጥ ዕድላችንን እንደሚያሰፋው ነው የሚናገሩት።
ብቸኝነት ለጭንቀት ዋነኛም መንስኤ እንደሆነ ይነገራል።
በመሆኑም ከምንቀርባቸው ሰዎች ጋር መጫወት እና ጊዜ ማሳለፍ ይመከራል።

5. አልኮል በልክ ይውሰዱ

የተመጠነ የአልኮል መጠጥ አወሳሰድ ለጤንነት ጠቃሚ ነው።
ሴቶች በቀን ከሁለት ብርጭቆ ወንዶች ደግሞ ከሶስት ብርጭቆ ያልበለጠ ወይን ቢጎነጩ ለጤናቸው ይበጃልም ነው የተባለው። የአሜሪካ የልብ ህክምና ማዕከል በ2010 ያወጣው መፅሄት ላይ እንደተጠቆመው፥ ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ የአልኮል አወሳሰድን መመጠኑ ለልብ ጤንነት ፍቱን ነው ።

6. ከአትክልት እና ፍራፍሬ ጋር ይወዳጁ

የአትክልት እና ፍራፍሬ ውጤቶችን አዘውትሮ መመገብ ረጅም ዕድሜን ያጎናፅፋል።
በተለይም በፋይበር እና ቫይታሚን የተሞሉ ምግቦችን ተመራጭ ማድረጉ ለልብ ህመም የመጋለጥ እድልን 76 በመቶ ሲቀንስ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልንም በእጅጉ ይቀንሳል።
በተጨማሪም አትክልት እና ፍራፍሬ በዋናነት የደም ዝውውርን ያቀላጥፋሉ፤ የምግብ መፈጨት ሂደትን ጤናማ ያደርጋሉ፣ የቆዳ ህዋሳትን በየጊዜው በመተካት የቆዳ መጨማደድንም ያስቀራሉ።

7. የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ያዘውትሩ

በየቀኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ በዕድሜያችን ላይ አራት አመትን እንድንጨምር ያስችላል ተብሏል። በተለይም እንደ ሶምሶማ፣ ሩጫ፣ ርምጃ ያሉትን ዘወትር መተግበርም በልብ ህመም የመጠቃት ዕድልን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ያስችላል። በተጨማሪም እነዚህ እንቅስቃሴዎች ለአካል እና አዕምሮ ዕድገትና ብሩህነት፣ ለምግብ መፈጨት ሂደት መጎልበትም ወሳኝ ናቸው።

8. ሲጋራ አያጭሱ

ሲጋራ ማጨስን ማቆምዎ ዕድሜዎን ለማርዘም ከሚወስዷቸው እርምጃዎች አንዱ እና ዋነኛው ነው። እንደ አሜሪካ የጤና ማዕከል የጥናት ውጤት ከሆነ ዕድሜያቸው 35 ሳይደርስ ማጨስ የሚያቆሙ ሴቶች በዕድሜያቸው ላይ ከስድስት እስከ ስምንት ዓመትን ለመጨመር እንደሚያስችላቸው ተረጋግጧል።

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.