አትክልት ብቻ ስለሚመገቡ ሰዎች ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮች

በዓለም ላይ ምንም አይነት የእንስሳት ተዋጽኦ የማይመገቡ (ቪጋን) በርካታ ሰዎች አሉ። ምንም እንኳን የእንስሳት ተዋጽኦን አለመመገብ በዓለማችን እየተለመደ የመጣ ቢሆንም፤ የሥጋ ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ ከእጥፍ በላይ ነው።

በእንግሊዝኛው ቪጋን ተብለው የሚጠሩት ሰዎች ምንም አይነት ሥጋ፣ እንቁላል፣ አሳ ወይም ማር በአጠቃላይ የእንስሳት ሥጋና ከእንስሳት የሚገኙ ምግቦችን አይመገቡም።

ምንም አይነት የእንስሳት ተዋጽኦን አለመጠቀም የሚለው እሳቤ ለምግብነት ስለሚጠቀሟቸው ነገሮች ብቻ አይደለም፤ በማንኛውም መልኩ በእንስሳት ላይ የሚፈጸምን ብዝበዛ መቃወምም ያካትታል። ይህ ማለት ደግሞ ከእንስሳት ቆዳ የሚሰሩ አልባሳትን እስካለመጠቀም ድረስ ማለት ነው።

ይህንን የህይወት መንገድ ለመከተል ጠበቅ ያለ ውሳኔ ማሳለፍ ይፈልጋል። በአለማችን ከሌላው ጊዜ እጅግ በጨመረ መልኩ ሰዎች ከእንስሳት ተዋጽኦ ነጻ የሆኑ ምግቦችን ለመጠቀም ብዙ ገንዘብ እየከፈሉ ነው።

ከተክሎች ጋር የተያያዙ ምግቦችም በበይነ መረብ በመላው ዓለም እየተቸበቸቡ ነው።

ማንናውም አይነት የእንስሳት ተዋጽኦ ስለማይመገቡ ሰዎች ሊያውቋቸው የሚገቡ አምስት ነገሮች እነሆ።

1. ታሪካዊ አመጣጥ

ምንም አይነት የእንስሳት ተዋጽኦ የማይመገቡ ሰዎች ማህበር የተቋቋመው እ.አ.አ. በ1944 እንግሊዝ ውስጥ ነው።

ዋትሰን የተባለ ስጋ የማይመገብ ሰው በስጋ ማቀነባበሪያዎች ውስጥ በእንስሳት ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ከተመከለተ በኋላ ነው ይህንን አስተሳሰብ ማራመድ የጀመረው።

ምንም አይነት ስጋ ነክ ምግቦችን ያለመመገብ አስተሳሰብ ከመጀመሩ ከ2500 ዓመታት በፊት ግን በጥንታዊ ህንድና ምስራቅ ሜዲትራኒያኒያን አካባቢዎች የተለመደ እንደነበር የታሪክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

ህንድ ውስጥ ከፍተኛ የተከታዯች ቁጥር ያለው ሂንዱይዝም ሃይማኖት እንስሳት በተለይ ላሞች ስጋቸው መበላት እንደሌለበት የሚገልጽ ሲሆን፤ የዚህ ዘመነኛ አስተሳሰብ መነሻ ተደርጎም ይወሰዳል።

ቡድሂዝም፣ ሂንዱይዝምና ጃኒዝም የተባሉ ሃይማኖት ተከታዮች ሰዎች ማንኛውም አይነት እንስሳ ላይ ህመም ማድረስ የለባቸውም ብለው ያምናሉ።

በ500ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ታዋቂው ግሪካዊ ፈላስፋና የሂሳብ ባለሙያ ፓይታጎረስ በእንስሳት ላይ የሚፈጸሙ ግፎችን በእጅጉ ይቃወም ነበር።

ወደ ስጋችን ሌላ ስጋ ማስገባት ርኩስነት ነው ብሎ ያምን ነበር። የአንድን ሰው ህይወት ለማስቀጠል የሌላውን ፍጥረት ነፍስ ማጥፋት የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል በማለት ሲከራከር ኖሯል።

አትክልት የምትበላ ሴትImage copyrightGETTY IMAGES

2. የጤና ጥቅሞቹ

በቅርቡ እንግሊዝ ውስጥ በተሰራ ጥናት መሰረት ማንኛውም አይነት የእንስሳት ተዋጽኦ ከማይመገቡ ሰዎች 49 በመቶ የሚሆኑት ለጤና ካለው ጥቅም የተነሳ የአመጋገብ ስርአቱን እንደመረጡ ተናግረዋል።

ቀይ ስጋ እና ሌሎች በፋብሪካ የተቀነባበሩ የስጋ ምርቶችን የሚመገቡ ሰዎች ለአንጀት ካንሰር ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ጠቁመዋል።

በአውሮፓውያኑ 2015 የዓለም ጤና ድርጅት በፋብሪካ የተቀነባበሩ የስጋ ውጤቶችን ካንሰር ከሚያመጡ ንጥረ ነገሮች መካከል የመደባቸው ሲሆን፤ በፋይበርና ሌሎች ቫይታሚኖች የበለጸጉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ ደግሞ በካንሰር የመያዝ እድልን በከፍተና ሁኔታ እንደሚቀንሱ ገልጿል።

ምንም አይነት የእንስሳት ተዋጽኦ የማይመገቡ ሰዎች ከሚመገቡ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ጤናማ ህይወት እንዳላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ለአጥንት እድገት፣ ለተስተካከል የደም ስርአት፣ ለነርቭ ስርአትና ለአንጎል እድገት የሚጠቅሙ እንደ ቫይታሚን ዲ፣ ቫይታሚን ቢ12 እና አዮዲን የተባሉ ንጥረ ነገሮችን ማግኘት አይችሉም።

ይህንን ለማካካስ ደግሞ ወደ ሰው ሰራሽ እንክብሎች ፊታቸውን ማዞር አለባቸው። እሱም ቢሆን የራሱ የሆነ አሉታዊ ውጤት ይኖረዋል።

3. አካባቢ ላይ ያለው ተጽ

አሁን አሁን ይህ የአመጋገብ ስርአት ብዙ ተከታዮችን እያፈራ ቢሆንም በአለማችን ያለው የስጋ ተተቃሚ ቁጥር ግን ከግምት በላይ ነው። እንደ ቻይናና ህንድ ባሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ባሉባቸው ሃገራት ዜጎች የምግብ ፍላጎታቸውን ለማርካት ፊታቸውን ወደ ስጋ እያዞሩ ነው።

በቅርቡ የተሰሩ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት እየጨመረ የመጣው የአለም ህዝብ ቁጥር በምድራችን የተፈጥሮ ሃብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳረፈ ነው።

እንደ ሪፖርቶቹ ትንበያ የሰው ልጅ የምግብ ፍላጎቱን ለማርካት እየሄደበት ባለው ሁኔታ አሁን ከሚያመርተው 70 በመቶ ተጨማሪ ምግብ ማምረት ካልቻለ፤ እ.አ.አ. በ2050 ዓለማችን ምግብ አልባ ትሆናለች።

በ2013 የተባበሩት መንግስታት የምግብና ግብርና ድርጅት ባወጣው ጥናት መሰረት አካባቢን ከሚበክሉ ግሪንሃውስ ጋሶች 14.5 በመቶ የሚሆኑት የሚመነጩት የቀንድ ከብቶች ከሚለቁት ሚቴን ከተባለ ጋስ ነው።

ይህ ደግሞ እያንዳንዱ መኪና፣ ባቡር፣ አውሮፕላንና መርከቦች ወደ ምድር ከሚለቁት ጋስ ጋር እኩል ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የስጋ ምርት ብዙ የተፈጥሮ ሃብት ያባክናል። ለምሳሌ 450 ግራም የሚመዝን ቆስጣ ለማደግ 104 ሊትር ውሃ የሚጠቀም ሲሆን፤ ተመሳሳይ ክብደት ያለው ስጋ ግን 23 ሺ ሊትር ውሃ ይፈጃል።

የተባበሩት መንግስታ የዓለም ህዝብ ቁጥር 7 ቢሊየን እንደሆነ የሚገምት ሲሆን፤ በ2050 ደግሞ 9.2 ቢሊየን እንደሚደርስ ግምቱን አስቀምጧል።

ምንም እንኳን የተረጋገጠ ቁጥር ማግኘት ባይቻልም የአለም አቀፉ የእንስሳት ተዋጽኦ የማይጠቀሙ ሰዎች ማህበር እንደሚለው ቁጥራቸው ከ550 እስከ 950 ሚሊየን ሊደርስ ይችላል።

የእንስሳት መብት ተሟጋቾች በፊሊፒንስImage copyrightGETTY IMAGES

4. አዋጪ የስራ ዘርፍ

ቪጋኒዝም ወይም የእንስሳት ተዋጽኦ ያለመጠቀም ባህል አሜሪካ ውስጥ ብቻ 600 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ እንግሊዝ ውስጥ ደግሞ 400 በመቶ እድገት አሳይቷል።

ይህ ዓለም በአዲስ መልክ እየተከተለችው ያለው የአመጋገብ ስርአት ብዙዎችን እየሳበ ነው። ከስጋ ነጻ የሆኑ ምግቦችን የሚያዘወትሩ ሰዎች ቁጥር በ2017 ብቻ በ1000 ፐርሰንት ያደገ ሲሆን፤ በ2018 ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

በተለይ ደግሞ ታዋቂ ሰዎችና ስፖርተኞች የሚከተሉትን ጤናማ የአመጋገብ ስርአት በተመለከተ ኢንስታግራም በተባለው የማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰፍሯቸው መልእክቶች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እየሳቡ ነው።

እንደ ‘ኔስሌ’ ያሉ የዓለማችን ትልልቅ የምግብ አምራች ኩባንያዎችም ፊታቸውን ወደ እነዚህ ሰዎች እያዞሩ ነው። ‘ጀስት ኢት’ የተባለው የተለያዩ ምግቦችን ሰዎች ባሉበት ድረስ የሚያቀርብ ድርጅት በአንደኛ ደረጃ በደንበኞች የሚታዘዙት ምግቦች ከእንስሳት ተዋጽኦ ነጻ የሆኑት እንደሆኑ ገልጿል።

ራዕይ አላቸው ተብለው የሚታሰቡ የስራ ፈጠራ ባለሙያዎችም እውቀታቸውንና ገንዘባቸውን በዚህ ዘርፍ ላይ እያዋሉ ነው። በመጪዎቹ ሁለት ዓመታትም ዘርፉ እስከ 4 ቢሊየን ዶላር ድረስ ሊያንቀሳቅስ እንደሚችል ተገምቷል።

5. ልክ ያለፈ አክራሪነት

‘የቪገኒዝም’ እንቅስቃሴ ገና ከጅምሩ እንስሳት ፍቅርና ክብር ይገባቸዋል በሚል የተጠነሰሰ ቢሆንም፤ አሁን አሁን የሚታዩ ተግባራት ግን ወደ ማክረሩ የተጠጉና ሌሎችን እስከመከልከል ይደርሳሉ።

ብዙ የቀንድ ከብት የሚያረቡ ገበሬዎች በአክራሪዎች ፍርድ ቤት ተከሰዋል፣ ስጋ መሸጫዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ እንዲሁም ሰዎች ለምን ስጋ ትመገባላችሁ ተብለው እስከ መገለል ደርሰዋል።

”ገዳይ ወይም ነፍስ አጥፊ ተብለህ ስትጠራ በጣም ያሳዝናል፤ ያስደነግጣል” ትላለች እንግሊዝ ውስጥ በግብርና ስራ የምትተዳደረው አሊሰን ዋግ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.