ኢትዮጵያ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ህዋ ታመጥቃለች

ኢትዮጵያ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ጥቅምት ወር አጋማሽ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ህዋ የምታመጥቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ኢንስቲትዩቱ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ የሚያስችለውን ዓለም አቀፋዊ ፈቃድ ማግኘቱንም  ገልጿል።

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት ሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም በተካሄደው 1ኛው የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት ጉባኤ፥ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በኋላ ሳተላይት ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ መገለጹ ይታወሳል።

ይሄን ተከትሎም ሳተላይት የማምጠቁ ሂደት የት ደረሰ?በሚል ለኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ዶክተር ሰለሞን በምላሻቸውም፥የኢትዮጵያና ቻይና መሐንዲሶች በጋራ በመሆን ወደ ህዋ የምትመጥቀውን ሳተላይት የመገንባቱን ተግባር እያገባደዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሳተላይት ማምጠቅ የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ ፈቃድና የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ምዝገባ መጠናቀቁን የገለጹት ዶክተር ሰለሞን፥ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ጥቅምት 15 ቀን 2019 ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ ተናግረዋል።

ሰባ ኪሎ ግራም ክብደት ያላት ሳተላይቷ፥ ዋና አገልግሎቷ ለግብርና፣ ለውኃ ፣ለማዕድን፣ ለከተማ ልማት እንዲሁም ለአየር ንብረት ቁጥጥርና ክትትል የሚሆኑ መረጃዎችን ማቀበል እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ሳተላይቷ በሃምሳ አራት ቀናት ዓለምን፤ በአራት ቀናት ደግሞ ኢትዮጵያን በመዞር ተልዕኮዋን እንደምታከናውንም አብራርተዋል።

ምንጭ ፦ ኢዜአ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.