የበታችነት ስሜት ምንድነው?

የበታችነት ስሜት ማለት ስለራስ ማንነት፣ ብቃት፣ ችሎታ ወይም በሌሎች የህይወት ገጽታዎች ከሌሎች ሰዎች በታች እንደሆኑ ማሰብና ስሜቱንም መለማመድ ነው፡፡
ይህ ከሌሎች በታች እንደሆኑ ማሰብ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በተለያዩ አሉታዊ ጫናዎች የተፈጠረ አስተሳሰብና ስሜት ነው፡፡ የበታችነት ስሜት ለራስ ዋጋ አለመስጠት፣ ስለራስ ብቃትና ችሎታ መጠራጠር እንዲሁም በማንኛውም መለኪያ ከሌሎች ሰዎች ጋር እኩል እንዳልሆኑ ተቀብሎ መኖር ነው፡፡
የበታችነት ስሜት ሰዎች ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ በመሆኑ ውጫዊ ነገሮችን በመቀያየር የሚለወጥ ነገር አይደለም፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር እኩል ለመሆን በስራ እጅግ ስኬታማ መሆን፣ ገንዘብ ሊገዛ የሚችለውን ነገር ሁሉ መግዛት፣ መዝናናት፣ የበታችነት ስሜትን አያጠፋም፡፡ መንስኤው የሰዎች አስተሳሰብ በመሆኑ፣ ራሳቸውን የሚያዩበት መስፈርት መለወጥ አለበት፡፡
ራሳችንን የምናይበት ሁኔታ በአካባቢያችን ያለውን ዓለም የምናይበትን መነጽር ይሰጠናል፡፡ ራሳችንን የምንመለከትበት መነጽር ትክክለኛ ካልሆነ፣ ዓለምንም የምናይበት መነጽር የተሳሳተ ነው፡፡
የበታችነት ስሜት ሌሎች ሰዎች በእኛ ላይ የሚጭኑት አስተሳሰብ ሳይሆን እኛው ራሳችን የምናሳድገው አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰዎች ለአስተሳሰቡ መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን እኛ እሺ ብለን ካልተቀበልን በስተቀር ሌሎች ምንም ያህል ስለእኛ መጥፎ ነገር ቢናገሩ በእኛ ላይ ኃይል እንዳይኖረው ማድረግ እንችላለን፡፡ ከበታችነት ስሜት ለመውጣትም ከፍተኛው ድርሻ የእኛው ይሆናል፡፡
የበታችነት ስሜት እንደ በሽታ ነው፡፡ አንድ በሽታ የራሱ የሆነ ምልክት እንዳለው ሁሉ፣ የበታችነት ስሜትም እንደ ስነ-ልቦና ችግር የራሱ ምልክቶች አሉት፡፡
የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች በህይወታቸው የሚያሳዩትን ምልክቶች:-
-በህይወታቸው ውስጥ መልካም ነገር እንዳለ አያምኑም
-ሰዎችን ለማስደሰት መኖር
-በራስ የመተማመን መንፈስ ማጣት
-ከፉክክርና ውድድር መሸሽ
-ነገሮችን በወቅቱ አለመሥራት
-ስህተት ፈላጊዎች ናቸው፡

የበታችነት ስሜት መንስኤዎች፡-
-ክፉ የአስተዳደግ ሁኔታ
-የስነ–ልቦና ጥቃት ሰለባ መሆን
-በተደጋጋሚ ችላ መባል
-ያለመሳካት መደጋገም

ምንጭ: ዶክተር አለ

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.