ይቅርታ በማድረግ የሚያገኟቸው ጠቀሜታዎች

               

ይቅርታ ማድረግና ይቅር ባይነት በህይዎት ዘመን ሲኖሩ እጅጉን ከሚያስፈልጉ ሰዋዊ ባህሪያት አንዱ ነው።ይቅር ባይነት ለአዕምሮ እርካታን በመፍጠር የደስተኝነት ስሜትን ያጎናጽፋል የራስ መተማመን እንዲኖርም ይረዳል።ይቅር ማለት ትልቅነት ከዚህ ባለፈም ፍቅርና ርህራሄን ማሳያም ተደርጎ ይወሰዳል።

የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይቅርታ አድራጊው ለመጥፎ ባህሪዎች ሳይሆን ለነበሩ መጥፎ አጋጣሚዎች ይቅርታ በማድረግ ከዚህ በኋላ መልካም ግንኙነትና መልካም ወዳጅነትን ለመመስረት በማለም የሚደረግ የመልካምነት መገለጫ መሆኑን ይናገራሉ።ይቅርታ ማድረግ በራሱ ለነገሮች ፍትህ የመስጠት ያክልም ውጤት አለውና ይቅር ማለት እጅጉን አስፈላጊ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።
ከዚህ አንጻርም ይቅር ለማለት የሚያበቁና ይህን በማድረግዎ የሚያገኟቸውን ጠቀሜታዎች ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ፤

የአዕምሮ ነጻነት ለማግኘት፦ ይቅርታ ሲያደርጉ መጀመሪያ የሚያገኙት ትልቁ ነገር የአዕምሮ እርካታና ነጻነት ነው።ከዚህ አንጻርም ይቅር ሲሉ አላስፈላጊ የሆኑ ቁጣና ግልፍተኝነት በመቀነስ የተሻለ ድባብ መፍጠር ይችላሉ።

ግንኙነትን ለማደስ፦ ይቅር ሲሉ ከዚያ ሰው ጋር የነበረዎትን ኩርፊያም ሆነ ቁርሾ አስወግደው መልካም ወዳጅነት ይመሰርታሉ።ይህ ደግሞ ምናልባትም ሰው ለሰው ያለውን ዋጋም ከፍ ያደርግልዎታል።

የተሻለ ስብዕናን እንዲላበሱ ያደርጋል፦ ይቅር ባይነት ስብዕናዎን ከፍ በማድረግ በአስተሳሰብም ሆነ በአመለካከት የተሻሉ እንዲሆኑ ያደርግዎታል።የእነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ የተሻለ ማንነትን ለመላበስ እጅጉን ያግዝዎታል።

ትብብርን ያጠናክራል፦ ይቅርታ ሲያደርጉ ምናልባትም በተፈጠረው ነገር አላግባብ ተበድያለሁ ነገሮችም በዚህ መልኩ በመሆናቸው ተጎድቻለሁ ለሚል ሰው አለኝታነትን ማሳያ መንገድም ይሆናል።ከዚህ አንጻርም ጠንካራ ትብብሮሽ ያለበት ወዳጅነትን ለማጠናከርና ወዳጅነትን ለማዝለቅም እጅጉን ይረዳል።

ሰላም፦ ይቅርታ ማድረግ ሲችሉ ይቅር ባይነት የሰላም መንገድ መሆኑን ለሌሎች ማሳያም አጋጣሚ ነው።በዚህ ደግሞ ሌሎችን ከኩርፊያና ከመነጣጠል ይልቅ የተሻለ የሰላም መንገድ እንዳለ በማሳየት እገዛ ያደርጉላቸዋል።የእርስዎም ሆነ የአካባቢዎ ሰላም ያለውን ዋጋ ደግሞ ዘለቄታዊና አስፈላጊ መሆኑን ማሳያም ይሆንልዎታል።

የተሻለ ከባቢን ለመፍጠር፦ ይቅርታ ሲያደርጉ ቁጣ የተሞላበት ስሜታዊነት ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት የራስዎን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ይረዳዎታል።ይህን ማድረግዎም የተሻለ ከባቢን ለመፍጠር ይረዳወታል።

መልካምነትን ለማጎልበት፦. የእርስዎ ይቅር ማለት በሌሎች ዘንድ ምንም አይነት ስያሜ ቢሰጠውም መልካምነትን ለማጎልበትና ለማሳደግ ይርዳዎታልና ይጠቀሙበት።

የራስን የህይዎት ዘይቤ ለማዳበር፦ ይቅር ባይነት በራስዎ የህይዎት ፍልስፍና እንዲጓዙና መልካም የሆኑ ባህርያትን እንዲያጎለብቱም ይረዳዎታል።እናም ለእርስዎ መልካም ባይሆኑም እንኳን ሰዎችን ይቅር ማለት ጥቅሙ ከፍ ያለ ነውና ያንን ማድረጉን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ከምንም በላይ ያለፈን መጥፎ ነገር እያሰቡ መኖር ወደ ኋላ ከመጎተትና ከማስቀረት የዘለለ ጠቀሜታም ሆነ አስተዋጽኦ የለውም።ይቅር ለማለት የሚያገኙ ድፍረት ደግሞ የህይዎትዎ የጥንካሬ ምንጭ ይሆናልና፥ ባለችዎት አጭር የህይዎት ዘመን ይቅር ባይ ቢሆኑ ያተርፋሉ።

ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement