ከልጆች አጠገብ ሆነው ሊፈፅሟቸው የማይገቡ ተግባራት – Things You Should Never do in Front of Your Child

                                 

ህፃናት ሁልጊዜ ፍቅር እና ትኩረት የሚሹ ንፁህ የነገ ተስፋዎች ናቸው።

ምንም እንኳን ወላጆች በበርካታ ሃላፊነቶች፣ ከሥራ ጋር የተያያዙ ውጥረቶች እና እጅግ በጣም የተንዛዛ መርሃ ግብር ውስጥ ቢሆኑም፥ ልጆቻቸው መሰረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች እንዳሏቸው መርሳት የለባቸውም።

ወላጆች የሚያደርጉት እያንዳንዱ እርምጃ ወይም ግብረ መልስ በልጃቸው ላይ ተፅእኖ እንደሚኖረው መዘንጋታቸው አዎንታዊ እና አሉታዊ ሊኖረው ይችላል።

ነገር ግን በሁሉም ሁኔታዎች በልጁ ፊት ሊደረጉ የማይገቡ የተወሰኑ ነገሮች እንዳሉ ጥናቶች ጠቁመዋል።

ከልጆች አጠገብ ሆነው ሊፈፅሟቸው የማይገቡ ተግባራትም የሚከተሉት ናቸው።

1. ውሸት

Lie.jpg

ወላጆች ልጆቻቸውን ለመርዳት ላለመቻላቸው በርካታ ምክንያቶች ሊኖራቸው ይችላል።

“ይሁን እንጂ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ለልጆቻቸው ውሸት መናገር ተገቢ አይደለም” ሲሉ ባለሙያዎች ገልፀዋል።

ምክንያቱም ህፃናት፥ ልምድ የሌላቸው እና የንፁህ አእምሮ ባለቤት በመሆናቸው ከህፃናት አጠገብ ሆነን ከዋሸን ልጆቻችን የተናገርነው ማጣራት አይችሉም።

በዚህም ልጆች እኛ ያደረግነውን ተመሳሳይ ነገር ለመፈፀም ሊነሱ ማለት ነው።

2. ከትዳር ጓደኛ ጋር መጋጨት

በልጅዎ ፊት ከትዳር ጓደኛዎ ጋር መጣላት፣ ጮክ ብሎ መናገር እና ብጥብጥ ማንሳት ልጅዎ የበለጠ ፍርሃት እንዲሰማው ያደርጋል።

ይህም ልጅዎ ሲያድግ ተመሳሳይ ልምዶች እንዲያዳብር ምክንያት ወይም አነሳሽ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነው የተነገረው።

በተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) መረጃ መሠረት በልጆች ፊት በቤት ውስጥ ብጥብጥ ማንሳት ልጆች ሲያድጉ ተመሳሳይ ችግሮች እንዲፈፅሙ ያደርጋል።

3. ከልጅዎ ፊት መቀለድ/ማሾፍ

ልጅዎን ሲያጫውቱ መቀለድ ወይም ማሾፍ አሁን ላይ ሆነው ሲያዩት ከባድ ነገር ላይመስል ይችላል።

ነገር ግን ልጆች በሚያድግበት ጊዜ አንዳንድ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያመጣ እንደሚችል ተጠቁሟል።

ይህም ለልጁ የስሜት መቃወስን ብቻ ሳይሆን፥ በራስ መተማመንን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል ነው የተባለው።

4. ልጅዎን መቆጣት

ልጅዎ የእርስዎን ፍቅር እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል እንጂ መቆጣጥት ተገቢ እንዳልሆነ የስነልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ልጆች ያልተገቡ ባህርያትን ወይም ስራዎችን ሊያንፀባርቁ ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም ወላጆች በቁጣ እጃቸውን በማንሳት መቅጣትን ወይም በእነሱ ላይ በመጮህ ማስፈራራት ተገቢ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

በየጊዜው ብስጭት እና ቁጣ በሚሰነዘርባቸው ጊዜ ፍርሃት በውስጣቸው እንዲነግስ በማድረግ ወላጆቻቸውን ለማነጋገር ፈቃደኛ አይሆኑም፤ ሃሳብ ማጋራት ያቋርጣሉ።

5. ተገቢ ያልሆኑ ምግቦችን መመገብ

ፈጣን ምግቦች ለልጆችዎ ምቹ አማራጮች ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ለልጅዎ አስፈላጊ የሆነውን መሠረታዊ የሆነው ንጥረ ነገር ላይኖረው ይችላል።

ከዚህም በላይ ሱስ የሚያስይዙ ሊሆኑ ስለሚችሉ ልጆቻችሁ ለእነሱ ያላቸውን ምኞት እንዲያሳድጉ ያደርጋቸዋል።

ስለዚህ “በልጆቻችሁ ፊት ተገቢ ያልሆኑ ወይም በጊዜ ሂደት ጉዳት የሚያመጡ ምግቦችን ከመመገብ ይቆጠቡ” ሲሉ ነው ባለሙያዎቹ ምክራቸውን የለገሱት።

6. ብዙ ጊዜ የሞባይል ስልክ መጠቀም

ሁልጊዜ ሞባይል ስልክዎን በመነካካት ማሳለፍ እና ልጅዎ በተለየ ሁኔታ የሚጠብቀውን የጨዋታ ጊዜ ችላ ማለት ተገቢ አይደለም።

በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸውን ከአጠገባቸው ለማራቅ ሲሉ ታብሌት ኮምፒተር ወይም ሞባይል ስልኮችን መስጠትም በሁሉም ሁኔታዎች መወገድ ያለበት ተግባር ነው ተብሏል።

ምክንያቱም እነዚህ ባህሪያት ህፃናትን በስልኮቻቸው እና በታብሌቶቻቸው ስክሪን ላይ ብዙ ሰዓታት ማሳለፍ፥ ጥሩ እንደሆነ ስለሚያመለክቱ ወላጆች እነዚህ እና መሰል ተግባራት ከመፈፀም መቆጠብ እንዳላቸው ተጠቁሟል።

ልጆች በስክሪን ላይ አፍጥጠው ብዙ ጊዜ ማሳለፋቸው ስነልቦናዊና አካላዊ የጤና ቀውሶችን እንደሚፈጥርም መገንዘብ ያስፈልጋል ነው የተባለው።

በመሆኑም ወላጆች ራሳቸው ሞባይል ስልክና መሰል የኤሌክትሮኒክ እቃዎችን አዘውትሮ ከልጅች ፊት ባለመጠቀም አርዓያ እንዲሆኑ በባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።

ምንጭ፦Mahdere Tena

Advertisement