ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩ ድንቅ አብያተ-ክርስቲያናት – The Incredible Rock-Hewn Churches

                                                                    

በሰሜን ኢትዮጵያ የምትገኘው ላሊበላ ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩት ድንቅ አብያተ-ክርስቲያናት የሚገኙባት ከተማ ናት። ለየት ያሉት እነዚህ አብያተ-ክርስቲያናት አሁን በዩኔስኮ ከተመዘገቡት የዓለማችን ድንቅ ታሪካዊ ስፍራዎች መካከል ይገኛሉ።

ከአንድ ወጥ አለት በርና መስኮት እንዲኖራቸው ተደርገው የተሰሩት እነዚህ አብያተ-ክርስቲያናት አንዳንዶቹ እስከ 50 ሜትር የሚደርስ ጥልቀት አላቸው። የተገነቡትም በ12ኛው እና በ13ኛው ክፍለ ዘመን ነበር።

በርካታ ምሁራንና የታሪክ አጥኚዎች እንደሚሉት ይህ ከአለት አብያተ-ክርስቲያናትን በመፈልፍል የመገንባት ጥበብ ከ500 ዓመታት ቀደም ብሎ የቀረ እንደሆነ ያምናሉ።

ነገር ግን አሁን ባለንበት ዘመንም ከአንድ ወጥ አለት አብያተ-ክርስቲያናትን የመቅረፁ ሥራ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ መሆኑ ታውቋል። የቢቢሲው ዘጋቢ ኢማኑኤል ኢጉንዛ ወደ ስፍራው ተጉዞ ነበር።

“እነዚህን አብያተ-ክርስቲያናትን የመስራቱ ጥሪና አጠቃላይ ቅርፁ ከእግዚአብሄር ዘንድ ተገልፆልኝ ነው” ይላሉ የአርባ ዓመቱ ጎልማሳ አባ ገብረመስቀል ተሰማ ከአለት ፈልፍለው የሰሩትን አዲሱን ቤተክርስቲያ ተዘዋውረው እያሳዩ።

በስፍራው በአጠቃላዩ አራት አብያተ-ክርስቲያናት ሲኖሩ እያንዳንዳቸው እርስበርሳቸው በሚያገናኝ ዋሻዎች ተያይዘዋል። የውስጥ ግድግዳቸውም በጥንቃቄ በተሰሩ ውብ ስዕሎች ተውበዋል።

አባ ገብረመስቀል ተሰማ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ቄስ ሲሆኑ፤ ከሌሎች ሦስት ሰራተኞች ጋር በመሆን በዙሪያቸው ያሉ ምዕመናን የአምልኮት ሥነ-ሥርዓት ለማከናወን ሊጠቀሙበት የሚችሉባቸውን አብያተ-ክርስቲያናት ከአለት ለመፈልፈል ሙሉ ጊዜያቸውን ሰውተዋል።

“አዲሱ ላሊበላ ብዬ ብሰይመው ደስ የሚለኝን ይህን የውቅር የአብያተ-ክርስቲያናት ስብስብን ሰርቶ ለማጠናቀቅ አራት ዓመታትን ፈጅቶብናል” ይላሉ።

በእሳተ-ገሞራ የተፈጠረውን አለት ለመፈልፈልና ቅርፅ ለማበጀት በቅርብ የሚገኙትን መሮ፣ መጥረቢያና አካፋን ተጠቅመዋል። በዚህ ሂደት ከባዱ ሥራ የሚጀምረው ከግዙፍ አለት ጫፍ ላይ በመሆን እየጠረቡ ወደታች በመውረድ ነው። ይህም መስኮቶችን፣ በሮችንና መተላለፊያዎችን መጥረብን ይጨምራል።

                                                                 

አብያተ ክርስቲያናቱ ከተቀረፁበት ቦታ ለመድረስ ቀላል አይደለም። አንደኛው ቤተክርስቲያን እየተቀረፀ ያለበት ስፍራ ለመድረስ ድንጋያማ የሆነ መንገድን ተከትሎ ለአንድ ሰዓት ያህል መጓዝን ይጠይቃል። አንዳንዶቹም በጣም የራቀ ቦታ ላይ ከመገኘታቸው የተነሳ የአካባቢው ባለስልጣናት ሳይቀሩ አብያተ-ክርስቲያናት መሰራታቸውን ሲሰሙ ተደንቀዋል።

አዳዲሶቹ አብያተ-ክርስቲያናት የሚገኙት አስደናቂ ኮረብታዎች ባሉበትና ታዋቂዎቹ ከአለት የተፈለፈሉ የላሊበላ አብኣተክርስቲያናትን ለማየት በሚኣስችለው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ወሎ አካባቢ ነው።

አስራአንዱ ከወጥ አለት የተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ለኢትዮጵያ ክርስትና ዋነኛ ሥፍራ በሆነው ቦታ ላይ በ12ኛው ክፍለዘመን ነበር የተሰሩት።

ተፈልፍለው የተሰሩትም ወደ ኢየሩሳሌም ለመጓዝ ለሚቸገሩ ኢትዮጵያዊያን ምዕመናን ሲል አዲሲቱን ኢየሩሳሌም በቅርብ ለመገንባት በተነሳው በንጉሥ ላሊበላ ዘመን ነው።

ረጅም ዘመንን ካስቆጠሩት የላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናት መካከል ጣሪያው በመስቀል ቅርፅ የተሰራው ታዋቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ ወይም ቤተ-ጊዮርጊስ እንዲሁም ከአንድ ወጥ አለት በመቀረፅ በዓለም ትልቁ የሆነው የቤተ-ማሪያም አብያተ-ክርስቲያናትን ጨምሮ አንዳንዶቹ ከመሬት በታች እስከ 40 ሜትር ይጠልቃሉ።

አንዳንድ አፈ-ታሪኮች እንደሚሉት አብያተ-ክርስቲያናቱ በሚፈለፈሉበት ጊዜ በንጉሥ ላሊበላ ከውጪ እንዲመጡ የተደረጉ ሰራተኞች ቀን ቀን ሲሰሩ ይውሉና ሌሊት ደግሞ መላዕክት ሥራውን ያከናውኑ እንደነበር ይተርካሉ።

ነገር ግን አባ ገብረመስቀል ይህንን አይቀበሉትም፤ አዲሶቹን ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ለመስራት የተነሳሱትም የላሊበላን አብያተ-ክርስቲያናት በእግዚአብሄር የተመሩ ኢትዮጰያዊያን የሰሩት መሆኑን ለማስመስከር እንደሆነ ይናገራሉ።

                                                                     

“ኢትዮጵያዊያን ይህን መሰለ ተግባርን ለማከናወን የሚያበቃ እውቀትና ክህሎት አልነበራቸውም ብለው የሚያምኑ አንዳንዶች አሉ። ቢሆንም ግን አሁን እኔ በምሰራበት ጊዜ ማንም አንዳች ነገር አላሳየኝም፤ ይህን ድንቅ ሥራ እውን ያደረኩት በመንፈስ-ቅዱስ አማካይነት ነው” ይላሉ።

“በሰሜናዊው ኢትዮጵያ እየተገኙ ላሉት አዳዲስ አብያተ-ክርስቲያናት መንፈሳዊነት ዋነኛው መሰረት ነው” ሲሉ የሚያብራሩት የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ማይክል ገርቨርስ ናቸው።

ፕሮፌሰር ማይክል ከሥነ-ህንፃ እና ከፊልም ባለሙያዎች ጋር በመሆን ይህንን እየጠፋ ያለውን የግንባታ ጥበብ መዝግቦ ለማስቀመጥ አንድ ሥራ ጀምረዋል። በዩናይትድ ኪንግደሙ አርኬዲያ ፈንድ ቢደገፈው እቅዳቸውም ዘመናዊ የመረጃ ቋት በማዘጋጀት ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ነው።

“ከድንጋይ የሚፈለፈሉ አብያተ-ክርስቲያናትን መስራቱ የሚቀጥል ከሆነ ዘመናዊነት እየተስፋፋ በሚመጣበት ጊዜ መፈልፈያ መሳሪያዎችን መጠቀም ስለሚጀመር፤ በእጅ የመስራቱ ጥበብ ሙሉ ለሙሉ ይጠፋል” ይላሉ።

“ስለሆነም ከአንድ የግንባታ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየሄድን የግንባታውን ጥበብ የሚያውቁትን ባለሙያዎችን በማነጋገር ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ያላቸውን የግል ዕውቀት እንመዘግባለን። አላማችንም ያገኘውን መረጃ ለሕዝብ ክፍት ማድረግ ነው።

ቡድኑ እስካሁን 20 አዳዲስ አብያተ-ክርስቲያናትን በተራራማዎቹ በሰሜናዊ የአማራና የትግራይ ክፍሎች ውስጥ አግኝቷል።

“የበለጠ በፈለግን ቁጥር ተጨማሪ እናገኛለን። በርካታ አብያተ-ክርስቲያናት እንዳሉ ስለማምን ሌሎች በርካቶቸን አግኝተን እንደምንመዘግባቸው ተስፋ አደርጋለሁ። ከአለት የተፈለፈሉ አብያተ-ክርስቲያናት አንድ ጊዜ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ብዙም ጥገና የሚፈልጉ አይደሉም። ለሺህ ዓመታት አገልግኦት ሊሰጡ ይችላሉ” ሲሉ ፕሮፌሰር ገርቨርስ ይጨምራሉ።

ለአባ ገብረመስቀል ሥራቸው አብያተ-ክርስቲያናቱን የገነቡበት ጥበብ መኖሩን ከማረጋገጥ በእጅጉ የበለጠ ነው።

“አብያተ-ክርስቲያናቱበይፋ ተከፍተው በአካባቢዬ ያለው ሕብረተሰብ የሐይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶችን ሲያከናውን ለማየት ጓጉቻለሁ። በቅርቡ… በጣም በቅርቡ እነዚህ የእግዚአብሄር ቤቶች በደስተኛ ሰዎች ይሞላሉ” ብለዋል ገፃቸው በፈገግታ በርቶ።

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement