የፀጉር መነቃቀልና መርገፍን ማከሚያ መንገዶች – How to Treat Damaged Hair

የፀጉር መበጣጠስና መሰባበር በአብዛኛው በሴቶች ላይ ይከሰታል።

የፀጉር መሰባበር ደግሞ በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ የሚከሰትና ችግር ነው።

የስነ ውበት ባለሙያዎች ደግሞ በዚህ መልኩ ፀጉር ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የሚረዱ መንገዶችን ይጠቁማሉ።

በተለያየ ምክንያት በፀጉር ላይ የሚከሰቱ የመነቃቀል፣ መሰባበርና መበጣጠስ ችግሮችን ለመከላከልም ቤት ውስ በቀላሉ በሚዘጋጁ ውህዶች መከላከል እንደሚቻል ይገልጻሉ።

የወይራ ዘይት፦ በተለያየ ምክንያት የሚረግፍና የሚሰባበርን ፀጉር ለመጠገን እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህ ዘይት የጭንቅላትዎን ቆዳ በአግባቡ በማዳረስና በመቀባት በንጹህ የፀጉር መጠቅለያ በመጠቅለል ለግማሽ ሰዓት ያክል ባለበት እንዲቆይ ማድረግ አልያም ደግሞ ምሽት ላይ ተቀብተው በአግባቡ ጠቅልልው መተኛት።

ከዚያም ለብ ባለ ውሃ በሻምፖ መለቃለቅና ይህን ጸጉር ማከሚያ መንገድ በሳምንት አንድ ቀን ለውጥ እስከሚያዩ ድረስ መጠቀም።

አቮካዶ፦ በቫይታሚን፣ ፕሮቲንና ለጸጉር እድገትና ጥንካሬ በሚያስፈልጉ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ በመሆኑ ለጸጉር ጥንካሬ አስፈላጊ መሆኑ ይነገራል።

አነስ ያለ አንድ አቮካዶ በማዘጋጀት ከ2 የሻይ ማንኪያ የወይራ ዘይት ጋር ማዋሃድና በደንብ መቀላቀል።

ከዚያም ፀጉርዎንና የራስ ቅልዎ ላይ በአግባቡ በመቀባትና በንጹህ ላስቲክ በመሸፈን ለ1 ሰዓት ያክል ባለበት እንዲቆይ ማድረግና ከተባለው ጊዜ በኋላ ለብ ባለ ውሃ መታጠብና መለቃለቅ።

ከዚህ ባለፈም አንድ መካከለኛ አቮካዶን ከአንድ እንቁላል ጋር በመቀላቀል ጸጉርዎንና የራስ ቅልዎን አዳርሰው በደንብ መቀባትና ከአንድ ሰዓት ባለ ውሃ መለቃለቅም ይችላሉ።

እንቁላል፦ በፕሮቲንና በተለያዩ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ ከመሆኑ አንጻር ለፀጉር ይጠቅማል ከዚህ አንጻርም ቫይታሚን ቢ ስላለው የጸጉር መርገፍን ለመከላከል ይረዳል ከዚህ አንጻርም እንቁላልን መጠቀም የፀጉር ደህንነትን ለመጠበቅ ይረዳል።

አንድ እንቁላል፣ ግማሽ ሎሚ እንዲሁም ሁለት የሾርባ ማንኪያ የወይራ ዘይት፤ ከዚያም ሶስቱን አንድ ላይ በደንብ መቀላቀልና ጸጉርን አዳርሶ መቀባት።

የሶስቱን ውህድ ጸጉርዎ ላይ በመቀባት ለግማሽ ሰዓት ያክል ማቆየትና ለብ ባለ በንጹህ ውሃ መታጠብና መለቃለቅ።

ሙዝ፦ ለጸጉር ጥሩ የቅባት ምንጭ ከመሆኑም በላይ የጸጉር መርገፍና መሳሳትን ይከላከላል።

ለጸጉርዎ ደህንነትም 2 ሙዝ፣ 1 ሾርባ ማንኪያ የወይራ ዘይትና 1 ማንኪያ ማር መቀላቀልና ተቀብተው ለግማሽ ሰዓት ያክል አቆይቶ ለብ ባለ ውሃ መታጠብና መለቃለቅ።

ከዚህ ባለፈም 2 ሙዝ በመላጥ ጸጉርን መቀባትና በላስቲክ ሸፍኖ ለግማሽ ሰዓት ያክል በማቆየት በሻምፖና ኮንዲሽነር ታጥቦ መለቃለቅም ጸጉርዎን ከመሰባበርና ከመርገፍ ለመከላከል ይረዳዎታል።

የኮኮናት ዘይት፦ ለጸጉር እድገት፣ ጥንካሬና ደህንነት የሚረዱ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ የያዘ በመሆኑ ለጸጉር እጅግ አስፈላጊ ነው።

የኮኮናት ዘይት ጸጉርዎን እንዳይነቃቀልና እንዳይረግፍ በማድረግ የተፈጥሮ ወዙን እንደጠበቀ ጠንካራ ጸጉር እንዲኖርዎት ይረዳዎታል።

የፀጉር መርገፍና መሳሳት በጣም የሚያስቸግርዎት ከሆነ የኮኮናት ዘይቱን በየቀኑ ለአምስት ደቂቃ ያክል ጸጉርዎን እያዳረሱ መቀባት።

አልያም ደግሞ በሳምንት ሶስት ቀን ማታ ወደ መኝታ ከማምራትዎ በፊት መቀባትና ሌሊቱን ሙሉ ባለበት እንዲቆይ ማድረግ ይመከራል።

ሬት፦ ሬት በተለያየ ምክንያት የተጎዳን ፀጉር መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ በእጅጉ እንደሚረዳ የስነ ውበትና የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለፀጉርዎ ደህንነትና ጥንካሬ እጅግ የሚረዱ እንደ ቫይታሚን ሲ እና ኢ እንዲሁም አሚኖ አሲድን በውስጡ ይዟል።

የተጎዳን ፀጉር ለማከምም የሬቱን ፈሳሽ በጥንቃቄ ጸጉርዎ ላይ መቀባትና ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ተቀብተው ማቆየትና ከተባለው ጊዜ በኋላ ለብ ባለ ውሃ መለቃለቅ ይመከራል።

ከዚህ ባለፈም 4 የሾርባ ማንኪያ የሬት ፈሳሽ፣ 2 የሾርባ ማንኪያ ኮኮናት ዘይት እና 3 የሾርባ ማንኪያ እርጎ ከተገኘ አንድ ላይ መቀላቀልና ማዋሃድ።

ከዚያም ፀጉርዎን በአግባቡ መቀባትና ለግማሽ ሰዓት ያክል ባለበት ማቆየትና በሻምፖ መለቃለቅ።

በዚህ መልኩ ፀጉርዎን በሳምንት አንድ ቀን በመቀባት ለውጥ እስከሚያዩ ድረስ መደጋገም።

ማር፦ ማር በተፈጥሮው የተጎዳና የደረቀን ፀጉር ለማከምና ለማለስለስ ይረዳል።

ሩብ ሲኒ ንጹህ ማር በንጹህ ውሃ በማቅጠን ፀጉርን መቀባትና ለ30 ደቂቃ ያክል ማቆየት።

ከዚያም ለብ ባለ ውሃ መታጠብና መለቃለቅ ይህን ማከሚያ መንገድ በሳምንት ሁለት ቀናት እየደጋገሙ መሞከር።

እንደ አማራጭም 2 የሾርባ ማንኪያ ማርና 1 የሾርባ ማንኪያ እርጎ እንዲሁም ከ1 የሾርባ ማንኪያ የወይራ አልያም የኮኮናት ዘይት ጋር መቀላቀልና ማዋሃድ።

በዚህ መልኩ ያዘጋጁትን ውህድ ፀጉርዎን መቀባትና ለ20 ደቂቃ አቆይቶ ለብ ባለ ውሃ መታጠብ፤ ይህንን በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ያድርጉት።

በተደጋጋሚ መልኩ ፀጉርዎን በማር ለማከም መሞከሩ ፀጉርዎን ስለሚያሳሳው ከተጠቀሰው ጊዜ በላይ መጠቀሙ አይመከርም።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement