በአነስተኛ ዋጋ የምትሸጠው የቆዳ ካንሰር መመርመሪያ መሳሪያ ዓለም አቀፋዊ ሽልማት አሸነፈች – Skin Cancer Diagnostic Tool Won The Global Award

                                                         

ስካን( sKan) የተሰኘችው የቆዳ ካንሰር መለያ ትንሽ መሳሪያ የ2017 ዓለም አቀፋዊ የጄምስ ደይሰን ሽልማትን አሸነፈች።

መሳሪያዋ በቆዳ ላይ የሙቀት ካርታ በመስራት ከመጀመሪያ ደረጃ የካንሰር ህመም ጋር የተያያዙ ምልክቶች መኖር አለመኖራቸውን ትለያለች።

በተለይም ሜላኖማ የተባለው በገዳይነቱ የሚታወቀው የካንሰር ምልክትን መለየት ዋናው ስራዋ ነው ተብሏል።

በዓለም ደረጃ የቆዳ ካንሰር ከካንሰር ህመሞች በጣም የተለመደው እና በገዳይነቱ የታወቀ ነው።

ይህ የካንሰር ህመም ምንም እንኳ በቆዳ ላይ በቀላሉ መታየት የሚችል ቢሆንም፥ አሁንም ድረስ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።

ይህም የሆነው ሃኪሞች በእይታ ብቻ የተመሰረተ የቆዳ ካንሰር ህክምና የምርመራ ውጤት በማድረግ የበሽታውን ምልክት የማይገልጽ ውጤት ላይ ስለሚደርሱ በሽታው በሰውነት ህዋሶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የመፍጠር እድል ስለሚኖረው ነው።

የካናዳው ማክማስተር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የሰሯት ስካን የተሰኘችው መሳሪያም፥ ከዚህ ቀደም ከነበረው እጅግ የተሻለ የምርመራ ውጤት ማስገኘቷ ተጠቁሟል፤ ዋጋዋም በጣም አነስተኛ ሲሆን ፈጣን የምርመራ ውጤት ታስገኛለች። 

የካንሰር ህመም ህዋሶች በሰውነት ውስጥ ካሉ ከጤናማ ህዋሶች የበለጠ ሙቀት ይለቃሉ።

የመጀመሪያ ደረጃ የሜላኖማ በሽታ ምልክት መኖሩን የሚያረጋግጥ ምርመራ ለማድረግ፥ በቅድሚያ የሰውነት ቆዳ በበረዶ እንዲቀዘቅዝ ይደረግና መሳሪያዋ በተፈለገው የቆዳ ክፍል ላይ ትቀመጣለች።

መሳሪያዋ የሙቀት ማንበቢያ ስልትን( thermistors) በመጠቀም ቆዳን ከቅዝቃዜ ወደ ሙቀት መመለሱን ትለካለች።

በዚህም መመሰረት የሜላኖማ ምልክቶች ካሉ መሳሪያዋ ያረፈችበት ቆዳ ከሌላው አካል በተለየ ሙቀቱ ይጨምራል።

አዲሷ መሳሪያ በሙቀት ማስፈሪያ ካርታዋ አማካኝነት የሙቀት ልዩነቱን በጊዜ ልዩነት በመተንተን በኮምፒውተር ፕሮግራም አማካይነት ይፋ ታደርጋለች።

አሰራሩ ውስብስብ ያልሆነ ፈጣን እና ውጤታማ ሲሆን፥ የመሳሪዋ ዋጋም ከ770 የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ነው።

ስካን የቆዳ ካንሰር መመርመሪያ መሳሪያ በአንፃራዊነት በቅናሽ ዋጋ ለገበያ መቅረቧ፥ በዓለም ላይ በሜላኖማ ከፍተኛ የቆዳ ካንሰር ህመም የሚሞቱ ሰዎችን ለመታደግ መልካም ዜና ነው ተብሏል።

መሳሪያዋን የሰሯት ተመራማሪዎች 40 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተሸልመዋል።

ተመራማሪዎቹ የዓለም አቀፉ የጄምስ ዳይሰን ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው፥ በቀጣይ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ መሳሪያዎችን ለማምረት ተግተን እንድንሰራ ያበረታታናል ብለዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement