ልጆችዎ በቀን ለምን ያህል ሰዓት እንዲተኙ ይመከራል? – Sleeping Hours

                                                          

ከልጆች እንቅልፍ ጋር በተያያዘ ቶሎ ወደ አልጋ አለመሄድ፣ ብቻዬን አልተኛም ብሎ ማስቸገር፣ ወዘተ… ወላጆችን የሚያስቸግሩ ጉዳዮች ናቸው።

እንደ ዩናይትድ ስቴትስ የእንቅልፍ ፋውንዴሽን ሪፖርት ከሆነ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ወላጆች ከህፃናት እንቅልፍ ጋር በተያያዘ ፈተና ይገጥማቸዋል።
ልጆቻችን እንዲራቡ እንደማንፈቅድ ሁሉ በቂ እንቅልፍ የማግኘታቸው ጉዳይ ሊያስጨንቀን ይገባል ባይ ነው ፋውንዴሽኑ።
ባለሙያዎች ለዚህም ህፃናቱ ምን ያህል የእንቅልፍ ጊዜ ያስፈልጓቸዋል የሚለውን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህም መሰረት፦

# አዲስ ለተወለዱ ልጆች (እስከ 2 ወር)፦ በዚህ ዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች ለእንቅልፍ ከ10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ እስከ 18 ሰዓታት በቀን ቢጠቀሙ ጤናማ ይሆናሉ።

# ህጻናት(እስከ 1 ዓመት ገደማ)፦ እነዚህ ህፃናት የአጭር ጊዜ እንቅልፍ እና መደበኛ የመኝታ ክፍለ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ይህም ህጻናቱ የእንቅልፍ ፍላጎት ሲያሳዩ በቀን ከአንድ እስከ አራት ጊዜ አጭር እንቅልፍ (napping) መውሰድ አለባቸው። በመደበኛው የምሽቱ የመኝታ ጊዜ ደግሞ ከዘጠኝ እስከ 12 ሰዓታት የመተኛት ልምድ ሊኖራቸው ይገባል።

# ጨቅላዎች (ከ1 እስከ 3 ዓመት እድሜ)፦ ህፃናት በቀን የሚያገኙት አንድ የእንቅልፍ ጊዜን ጨምሮ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ12 እስከ 14 ሰዓታት መተኛት ይኖርባቸዋል።

# ለመዋዕለ ህፃናት የደረሱ( ከ3 እስከ 5 ዕድሜ)፦ ከ3 እስከ 5 ዕድሜ ክልል ያሉ ለመደበኛ ትምህርት ያልደረሱ ህፃናት በቀን ከ11 እስከ 13 ሰዓታት የሚደርስ በቂ የእንቅልፍ ጊዜ ማግኘት አለባቸው።

# ለመደበኛ ትምህርት የደረሱ (ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 12)፦ ዕድሜያቸው ለመደበኛ ትምህርት የደረሱ ልጆች ከ10 እስከ 11 ሰዓታት በደንብ እንቅልፍ ማግኘት ይኖርባቸዋል ነው የተባለው።

# ታዳጊዎች (እድሜ 13 እና ከዛ በላይ)፦ በዚህ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ታዳጊዎች ከ9 እስከ 9 ሰዓት ከ30 ደቂቃ የእንቅልፍ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል።

በአጠቃላይ እነዚህ ምክሮች ልጅዎ በቂ እረፍት እንዲያገኝ በማድረግ ለጤና ደህንነት አስፈላጊ በመሆናቸው በተባላው መሰረት መተግበር ይመከራል።

ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement