የልብ ድካም በሽታ – Heart Diseases

                                                   

ልብ ድካም ማለት የልብ አካል ላይ በደረሰ ጉዳት ወይም የአሰራር ለዉጥ ምክንያት ለተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች የሚሰራጨዉ ደም በቂ ሳይሆን ሲቀር የሚከሰት የጤና መታወክ ነዉ፡፡ የልብ አካል ጉዳት ሲባል የልብ ቫልቮች መጥበብ ወይም መስፋት የልብ ደም ስሮች መጥበብ የልብ ጡንቻና ማቀፊያ መጎዳት ሊሆን ይችላል፡፡

የልብ ድካም መንስኤዎች
የልብ ድካም መንስኤዉ ተፈጥሮአዊ የልብ በሽታ ወይንም ከጊዜ በኋላ በሚመጣ የልብ በሽታ ሊሆን ይችላል፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃና በተጨናነቀ አካባቢ የሚኖሩ ህፃና በተደጋጋሚ በቶንሲል ህመም ይበቃሉ፡፡ ለዚህ ቶንሲል በሽታ የተመረቱ አንቲቦዲ የተባሉ በሽታ ተከላካዮች የልብ ቫልቮች መጥበብና መስፋት ጋር ተያይዞ ለልብ ድካም ይዳርጋሉ፡፡

ከልብ ደም ቧንቧ መጥበብ ጋር ተያይዞ የሚመጣዉ የልብ ድካም በአብዛኛዉ በዕድሜ በገፉና በወንዶች ላይ ይከሰታል፡፡ በተጨማሪ በቤተሰብ ታሪክ ተመሳሳይ በሽታ መኖር፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከፍተኛ ደም ግፊት፣ ዉፍረት፣ ስኳር በሽታ፣ ኮሊስትሮል መብዛትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ለዚህ በሽታ የመጋለጥ ዕዱልን ይጨምራል፡፡

ለረዥም ጊዜ ሳይታከም የቆየ ከፍተኛ የደም ግፊት የልብ ደም ቧንቧዎችን በማጥበብና የልብ ጡንቻዎችን በማወፈር ለልብ ድካም ይዳርጋል፡፡
ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት ከእንሰሳት ተዋጽኦ የሚገኙ ስብና ቅባቶችን አብዝቶ መመገብ ደም ዉስጥ የኮሌስትሮል መጠንን ከፍ በማድረግ ለደም ቧንቧዎች ጥበት ይዳርጋል፡፡

የልብ ድካም ምልክቶች
በቀላሉ መድከምና አቅም ማጣት፣ ያለምንም እንቅስቃሴ ወይም መጠነኛ የአካል እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ሰዓት ትንፋሽ ማጠር ፣ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ አስፈሪ እና ከፍተኛ የሆነ ትንፋሽ ማጠር፣ ሌሊት ላይ የሚበረታ ሳል፣ እግር ማበጥ ወይም ከእግር የመጀምር የሰዉነት ማበጥ የልብ መምታትና የትርታ መጨመር ፌንት ማድረግ ደረት ህመም እንዲሁም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ማቅለሽለሽ፣ የሆዱ መንፋትና ሆድ ህመም ዋና ዋናዎቹ የልብ ድካም ምልክቶች ናቸዉ፡፡

ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement