SPORT: ኔይማር / የአለም ውዱ ተጫዋች የዝውውር ሂደት ዝርዝር ጉዳይና ባርሴሎና በማን ሊተካው ይችላል?

                                                 

ኔይማር ትናንትና ጠዋት በባርሴሎና የልምምድ ማዕከል ተገኝቶ መደበኛ ልምምዱን እንደሚቀጥል ሲጠበቅ ወኪሉ ሆነው በሚያገለግሉትና ውለታ በማያውቁት አባቱ ቀንደኛ ገፋፊነት መሰረት የካታላኑን ክለብ ልቀቁኝ ብሎ ጠይቋል።

የስፔኑ ታላቅ ክለብም ልቡ የሸፈተውን ተጫዋች በግድ ማቆየት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ብራዚላዊው የ 25 ተጫዋች ክለቡን ለቆ እንዲሄድ ፍቃድ መስጠቱን በመግለፅ በይፋ ማረጋገጫ ለመስጠት ተገዷል።

በብራዚላዊው ተጫዋች ሰሞነኛ ተግባር ብዙዎቹ የባርሴሎና ቡድን አጋሮቹ ቢበሳጩም ወደ ባርሴሎና የመመለሱን ነገር ሰምተው በልምምድ ላይ ስለመጪው ጊዜው እንዲነግራቸው ሰብሰብ ብለው በጉጉት ሲጠይቁትም ምንም ሳይሸማቀቅ ስንብቱን አርድታቸዋል። 

ከካታላኑ ክለብ ያፈተለከው ይፋዊ መግለጫ “ኔይማር ጁኒየር ከአባቱና ከወኪሉ ጋር በመሆን ጠዋት ላይ በክለባችን ፅህፈት ቤት ተገኝቶ ባደረግነው ስብሰባ ላይ የመልቀቅ ውሳኔውን አሳውቆናል።

“ከዚህ የተጫዋቹ አቋም ጋር በተያያዘም ክለባችን ለተጫዋቹ ውል ማፍረሻ አሁን ባለው ውሉ ላይ የተቀመጠውን 221 ሚሊዮን ዩሮ (196 ሚሊዮን ፓውንድ) ገቢ የሚያረግ ከተገኘ ፍቃደኞ መሆናችንን አሳወቅናቸዋል።” ሲል ተነቧል።

ከባርሴሎና መግለጫ በኋላም የዚህን የያዝነውን የክረምት በትልቁ አጨናንቆ የሰነበተው የዝውውር ጭምጭምታም በዚህ ሳምንት መጨረሻ በ 196 ሚሊዮን ፓውንድ የአለም ሪከርድ ዋጋ መቋጫ እንደሚያገኝ በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበት ተጫዋቹ ለህክምና ምርመራ ማምራቱ ተነግሯል። 

ከሰሞኑ የኔይማርን ቀጣይ እጣ ፈንታ ለማወቅ የኒው ካምፕ ስብስብ አባላት ጆሯቸውን አቁመው የሰነበቱ ሲሆን የመሀል ሜዳው የቡድኑ ሞተር አንድሬስ ኢኔስታ ከዚህ ቀደም በሰጠው አስተያየት ክለቡ ተጫዋቹን ሸጦ ከሚያገኘው 200 ሚሊዮን ፓውንድ ይልቅ የቀደሞው የሳንቶስ አጥቂ በክለቡ ቢቆይ ያለውን ጥቅም ማስረዳቱ ይታወሳል። 

በሌላ በኩል ጄራርድ ፒኬ “እሱ ይቆያል” ከሚል ማጀቢያ ፅሁፍ ጋር ከኔይማር ጋር የተነሳውን ምስል በትዊተር ገፁ ለቆ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ሁነቱ እውነታው የሚገልፅ ሳይሆን የራሱ ፍላጎት እንደሆነ ለማብራራት ተገዷል።

ለዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ውሀ የማያነሳ ምክንያት ቢሆንም ብዙዎች ብራዚላዊው ኮከብ ከሜሲ ጥላ ስር ለመውጣት በሚል የካታላኑን ክለብ እንደሚለቅ ምለው ሲከራከሩ የሰነበቱ ሲሆን በዚህም ተባለ በዚያ ግን ኔይማር በአምስት አመታት ቆይታው በ 54 ሚሊዮን ፓውንድ አመታዊ ክፍያ የ 270 ሚሊዮን ፓውንድ ውል በፖሪሱ ክለብ ቀርቦለታል። 

ይህ በነዳጅ ዘይት ገንዘብ በከበረው የኳታር ስፖርት ኢንቨስትመንት በተሰኘው ተቋም የሚሾፈረው ፒኤስጂ የዝውውሩን ሙሉ ወጪ የሚችል ሲሆን ኔይማር በፈረንሳዩ ክለብ የሁሉ ነገር መነሻ ዋና ምልክት (central figure) እንደሚሆን ሀሳብ የሰነቀ ሲሆን አንድ ጊዜ ብቻ ከፈረንሳይ ሊግ የባለንዶር ሽልማት ከተነሳበት የአውሮፓ አምስተኛውና ደካማው ሊግ ላይ ተቀምጦ የአለም ኮከብነት ምርጫን እንደሚያገኝ እያለመ ይገኛል።

በዚህ ብዙዎችን ጥርስ ባናከሰው ዝውውር የላሊጋው አስተዳዳሪ አካል ጭምር የፈረንሳዩ ክለብ ተጫዋቹን ትልቅ ገንዘብ አውጥቶ የመውሰድ ምንም አይነት ህጋዊ ምክንያት እንደሌለው በመግለፅ ከስልጣኑ ውጪ ተጫዋቹን በስፔን ለማቆየት ሲውተረተር ታይቷል። 

ወጣም ወረደም በቀጣይነት በባርሴሎና ቤት ህይወት ከኔይማር ውጪ ሽክርክሪቷን ትቀጥላለች። ለብራዚላዊው ተጫዋች ምትክነትም አንቶኒ ግሪዝማን፣ ፊሊፔ ኩቲንሆ እና ሙሳ ዴምቤሌ አይነት ኮከቦች በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ስማቸው እየተጣለ እየተነሳ ይገኛል። 

እዚህ ላይ የግሪዝማንን በተተኪነት መካተት በተጫዋቹና በአትሌቲኮ ማድሪድ ቤት ካሉ ወቅታዊ ምክንያቶች አንፃር እንደማያስኬድ አስበን ወደ ሌሎቹ ስናነጣጥር ከዚህ ቀደም በቀላሉ የቀረበለትን የዝውውር ሂሳብ የሚቀበለው ሊቨርፑል በኩቲንሆን ዙሪያ ጥያቄን እንደማያስተናግድ በሩን መዝጋቱ የተጫዋቹን የኔይማር ተተኪነት እድል ማጥበቡን ያስመለከተናል። 

በክሎፕ በጥብቅ የሚፈለገውንና ከባርሴሎና ይልቅ ፒኤስጂን መርጦ  እንዲቀላቀል በሀገሩ ልጅና በልብ ጓደኛው ኔይማር በዋትሳፕ መልዕክት ሳይቀር የተነገረው ኩቲንሆን ለማግኘት በዚህ ክረምት ለባርሴሎና ትልቅ ፈተና እንደሚሆነው ይታሰባል።

በቀጣይ ከኔይማር ያልተጠበቀ ዝውውር በፊት ጀምሮ የባርሴሎና የዝውውር ኢላማ የሆነውን የቦርሲያ ዶርትሙንዱን የ 20 አመት ታዳጊ ኦስማን ዴምቤሌን እንደ ሶስተኛ አማራጭነት ቀርቦ ስሙ በተደጋጋሚ ሲገልፅ የሚሰማ ከሆነ ዋል አደር ብሏል። 

ነገርግን ደምቤሌ ካለው የእግር ኳስ ብስለት ደረጃና እድሜ አንፃር በኔይማር መልቀቅ የሚፈጠረውን ክፍተት ለባርሴሎና በበቂ ሁኔታ እንደማይሸፍንለት ግልፅ ሲሆን የቡንደስሊጋው ክለብም ተጫዋቹን በቀላሉ የሚለቅ አይነት አይደለም። 

እዚህ ላይ ኔይማርን በሚገባ መተካት የሚችል፣ በሚገባ የተፈተነ እና ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰውን የጁቬንቱሱን የፊት መስመር ኮከብ ፓውሎ ዳይባላ ላይ ትኩረት ማድረግ ለካታላኑ ክለብ በኔይማር መልቀቅ የሚፈጠርበትን ወቅታዊና የማያዳግም ክፍተት ለመቅረፍ ተገቢ ምላሽ ይመስላል። 

በእርግጥ አርጀንቲናዊው አጥቂ ሜሲን በዋነኛ ፊት አውራሪነት በሚጠቀመውና ኳስን ቶሎ ቶሎ ወደካታላኑ ክለብ 10 ቁጥር ወደሚያደርሰው የባርሴሎና ስብስብ መቀላቀልን ላይፈልግ ቢችልም የዝውውር ጥያቄ ከቀረበለት ከአለም ምርጡ የሀገሩ ተጫዋች ጋር በአንድ ቡድን ለመጫወት የሚመርጥ ይመስላል። 

በሌላ በኩል ተጫዋቹ በአዲስ ሊግ ለመፈተንና የእግር ኳስ ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ከሚኖረው ፍላጎት አንፃር እንዲሁም ደግሞ ዳይባላ ለካታላኑ ክለብ አይነት ኳስ ይዞና በትልቁ መስርቶ ለሚጫወት ቡድን ትክክለኛው የማጥቃት ሀይል የመሆኑ ነገር ባርሴሎና ከኔይማር ዝውውር የሚያገኘውን ገንዘብ ግማሽ ያህሉን ለአሮጊቶቹ አጥቂ ቢመድብ ተገቢ መሆኑን እንድንቀበል ያደርገናል።

በእርግጥ ጁቬንቱሶች ግሽበት በመታው እንዲሁም ደግሞ የከዚህ ቀደም የአለም ሪከርድን ሶስት እጥፍ የሚሆን ገንዘብ ለኔይማር መከፈሉን ሲያውቁ በዳይባላ ላይ የለጠፉትን የከዚህ ቀደም ዋጋ እንደሚያንሩት የሚጠበቅ ቢሆንም የካታላኑ ክለብ ስኬታማ ድርድር ማድረግ ከቻለ 150 ሚሊዮን ፓውንድ ባልፈጀ ዋጋ ተጫዋቹን በእጁ ማስገባት ይችላል። 

                የአለም ውድ የዝውውር ዋጋዎች 

1,000 ፓውንድ አልፍ ኮመን (1905) / እንግሊዛዊው አጥቂ ከዛሬ 112 አመት በፊት ከሚድልስብራ ሰንደርላንድን በጊዜው ሪከርድ አራት አሀዞች ዋጋ ተቀላቀለ። 

10,890 ፓውንድ ዴቪድ ጃክ (1928) / ቦልተኑ ለእንግሊዛዊው የፊት መስመር ኮከብ ዝውውር 13,000 ፓውንድ ቢጠይቅም የጊዜው ውድ አጥቂ ከወንድረድስ ፍላጎት ባነሰ ዋጋ አርሰናልን ተቀላቀለ። 

23,000 ፓውንድ : ቤርናቤ ፌሬራ (1932) / አርጀንቲናዊው ተጫዋች ቲግሬን በመልቀቅ ሪቨርፕሌትን የተቀላቀለና የመጀመሪያው እንግሊዛዊ ዜግነት የሌለው የአለም የዝውውር ሪከርድን የሰበረ ተጫዋች ሆነ።

152,000 ፓውንድ : ሊውስ ሱሀሬዝ ሚራሞንተስ (1961) / ስፔናዊው አማካኝ በጊዜው ትልቅ ግርምትን በፈጠረ ዋጋ ከኢንተር ሚላን ባርሴሎናን ተቀላቀለ።

1.2 ሚሊዮን ፓውንድ : ጁሴፔ ሳቮልዲ (1975) / በወቅቱ ለሀገሩ ጣሊያን ገና አራት ጨዋታ ብቻ ያደረገውና ናፖሊን በመልቀቅ ቦሎኛን የተቀላቀለው ሳቮልዲ የመጀመሪያው በሚሊዮኖች ዋጋ የተዘዋወረ ተጫዋች ሆነ።

3 ሚሊዮን ፓውንድ : ዲያጎ ማራዶና (1982) / ማራዶና ከቦካ ወደ ጁቬንቱስ ሲያመራ የሰበረውን የአለም የዝውውር ሪከርድ ዋጋ በ 1984 ወደ ናፖሊ ሲያመራ በድጋሚ በአምስት ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ እንደሰበረው አይረሳም።

15 ሚሊዮን ፓውንድ : አለን ሺረር (1996) / የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ 1996 አውሮፓ ዋንጫ ኮከብ የነበረውን አጥቂ በሪከርድ ዋጋ ከኒውካስትል ወደ ብላክበርን በማዘዋወር የገንዘብ ጡንቻው እየፈረጠመ እንደሚሄድ ለአለም አሳየ።

21.5 ሚሊዮን ፓውንድ : ዴኒልሰን (1998) / ብራዚላዊው ከሳኦ ፖሎ ወደ ሪያል ቤትስ ያደረገው ዝውውር አይን ገላጭ የነበረ ቢሆንም ዴኒልሰን የነበረውን የወጣትነት እምቅ ችሎት በስፔኑ ክለብ በሚገባ ማሳደግ ሳይችል ቀርቷል።

37 ሚሊዮን ፓውንድ : ሊውስ ፊጎ (2000) / የፖርቹጋላዊው ጨዋታ አቀጣጣይ ከባርሴሎና ወደ ማድሪድ ያደረገው ሪከርድ ሰባሪ ዝውውር የሁሉ ነገር መነሻ የጋላክቲኮስ ዘመን መባቻ ሆኖ ተመዝግቧል።

89 ሚሊዮን ፓውንድ : ፖል ፖግባ (2016) / ፈረንሳዊው ተጫዋች ጁቬንቱስን ለቆ የቀድሞ ክለቡን ማንችስተር ዩናይትድን ተቀላቀለ።

198 ሚሊዮን ፓውንድ : ኔይማር (2017) / ብራዚላዊው ኮከብ የአለምን የከዚህ ቀደም የዝውውር ሂሳቦች የሚያኮስስ እጅግ ትልቅ ከመጠን በላይ ገንዘብ ሊወጣበት ከባርሴሎና መውጫ በር ላይ ቆሟል። 

ምንጭ:- ኢትዮአዲስ ስፖርት

Advertisement