በሳምንት ለ1 ሰዓት የክብደት ማንሳት ስፖርት መስራት የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች

                                        

ጤንነታችንን ለመጠበቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትረን መስራት እንዳለብን ሁሌም ከሚመከሩ ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው።

ለጤናችን ይጠቅማሉ በሚል የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አይነቶች የሚመከሩ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ለዛሬው የከብደት ማንሳት ስፖርት መስራት የሚያስገኛቸውን ጠቀሜታ እንመልከት።

የኔዘርላንድስ ራድቦውድ ዩኒቨርሲቲ የጤና ማእከል ያወጣው የጥናት ውጤት በሳምንት ውስጥ በትንሹ ለአንድ ሰዓት የክብደት ማንሳት ስፖርት የሚሰሩ ሰዎች የሚያገኟቸውን የጤና ጠቀሜታዎች ያመለክታል።

በጥናቱ መሰረት በሳምንት ለአንድ ሰዓት የአካል ማጠንከሪያ ወይም እንደ ክብደት ማንሳት አይነት ስፖርት መስራት፦

  • ለስኳር በሽታ
  • ለከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም
  • ከመጠን ላለፈ የሰውነት ውፍረት የመጋለጥ እድላችንን በ29 በመቶ እንደሚቀንስ ያመለክታል።

ለእነዚህ የህመም አይነቶች የመጋለጥ እድላችንን ከዚህ በላይ ልንቀንስ እንችላለን በሚል ከአቅም በላይ መስራት ግን ጥቅም እንደሌለው ነው ተመራማሪዎቹ የሚናገሩት።

የሰውነት ማጠንከሪያ እና የኤሮቢክስ ስፖርቶችን አዘውትሮ መስራትም ከላይ ለተዘረዘሩት የህመም አይነቶች የመጋለጥ እድለን ለመቀነስ እንደሚረዳ ነው በጥናቱ የተቀመጠው።

የጥናቱ ውጤት ክብደት የማንሳት ስፖርትን ከአቅም በላይ መስራት ለጤናችን የሚሰጠው ጠቀሜታ አለመኖሩም “እኔ ብዙ አልሰራም” በሚል ራሳቸውን ለሚወቅሱ ሰዎችም የጥናቱ ውጤት መልካም ዜና ነው ተብሏል።

የምናነሳው የክብደት መጠን ምን ያክል መሆን አለበት…?

በካናዳ ኤም.ሲ ማስተር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም ባወጣው ጥናት የሰውነታችን ቅርፅ ያማረ እና ግዙፍ እንዲሆን የግድ ከፍተኛ መጠን ባላቸው ክብደቶች በመጠቀም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት አለብን የሚባለው ሀሳብ ትክክል አይደለም ማለቱ ይታወሳል።

ቀለል ያሉ ክብደቶችን በመጠቀም የሚሰሩ ሰዎችም የሰውነታቸውን ቅርፅ ማሳመር እና ጡንቻዎቻቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማፈርጠም ይችላሉ የሚለውም በጥናቱ ተለይቷል።

ሰውነታችንን መገንባት ከፈለግን ማንሳት በምንችለውን የክብደት መጠን በመጠቀም በድግግሞሽ በመስራት ሰውነታችንን በቀላሉ ማፈርጠም እንችላለን ብለዋል።

ወደ ስፖርት መስሪያ ማእከላት ወይም ጂምናዚየሞች በመሄድ እንዲህ አይነት እና መሰል እንቅስቃሴዎችን ከመስራታችን በፊት ባለሙያ ማማከርም ይመከራል።

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement