አንድ ሰው ትንፋሹ በድንገት ቢቋረጥ ምን እናደርጋለን?

የ ትንፋሽ መቋረጥ በብዙ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፤ ለምሳሌ በአንገት ወይም በፊት ላይ በሚደርስ ግጭት፣ በውኃ ውስጥ በመስጠም፣ በኤሌክትሪክ መያዝ፣ በመታፈን፣ የአየር ትቦ በባዕድ ነገር መዘጋት፣ በኦክስጅን እጥረት፣ በደረት ላይ በሚደርስ የአየር የግፊት ጫና ለውጥ(በፍንዳታ አካባቢ በመገኘት ሊሆን ይችላል)፣ የአየር ማስተላለፊያ ትቦ በጋዝ ወይም በጭስ ምክንያት ተጎድቶ ሲቆጣና ሲያብጥ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ሊጨመሩ ይችላሉ፡፡

የተለያዩ ምክንያቶች
ወደ አፋችን ያስገባነው ምግብም ሆነ ሌላ ነገር፣ አየር ከጉሮሮ ወደ ሳንባ የሚተላለፍበትን ትቦ ሲዘጋ፣
ጭንቅላታችን ወይም አንገታችን ከተመታ፣ 
አፋችን ወይም ጉሮሯችን በተለያዩ ምክንያቶች ማበጥ፣ በጭስ መታፈን፣ ትንታ፣ የጋዞች ወይም የኬሚካሎች አለርጂ፣ 
በአደጋ ምክንያት የጉሮሮ ትቧችን በመታጠፍ የአየር ፍሰትን መዝጋት፣
በአስም እና ሳይነስ በሽታዎች ምክንያት፣
ምላስን በመዋጥ የሚፈጠር(አየር ወደ ሳንባችን እንዳይደርስ በማድረግ እራሳችንን እንድንስት ያደርገናል፤ አልፎ ተርፎም ለሞት ይዳርጋል) ይህ ሁኔታ የሚከሰተው አንገታችን ወደ ፊት በጣም በሚታጠፍበት ጊዜ፣ የታችኛው መንጋጭላችን እና ምላሳችን ጡንቻዎች እንዲለጠጡ ሲያደርግ፣ ምላስ ወደ ኋላ ማለትም ወደ ጉሮሮ በመሸሽ፣ የአየር ቧንቧ እንዲዘጋ ስለሚያደርግ ነው፡፡

ትንፋሹ የተቋረጠን ሰው መታደግ
አንድ ሰው የመተንፈሻ አካሉ በባዕድ ነገር ተዘግቶ መተንፈስ ካቃተው በፍጥነት ከጀርባው ሆነን ወገቡ ላይ እጃችንን ከጎድኑ በታች በመጠምጠም ዐራት ጊዜ በኃይል ወደ ላይ በመጭመቅ የዘጋው ባዕድ ነገር ተፈናጥሮ እንዲወጣ ማድረግ አለብን፤ ይህ ዘዴ ካልሰራልን ደግሞ ከማጅራቱ በታች ጀርባው ላይ ዐራት ጊዜ በኃይል በመምታትና በድጋሚ ከጀርባው ሆነን ከወገቡ በመጭመቅ ባዕድ ነገሩ እንዲወጣ ማድረግ አለብን፡፡

የአፍ ለአፍ ትንፋሽ የመጀመሪያ እርዳታ/“Kiss of life”/
የአፍ ለአፍ የአየር እርዳታ፣ ራሱን ለሳተ ሰው፣ በዛው አሸልቦ እንዳይቀር በጣም ፈጣንና ፍቱን ዘዴ እንደሆነ ይታመናል፤ ይህንን እርዳታ የአየር መተላለፊያ ትቦ መስመር ክፍት እንደሆነ መለገስ መጀመር እንችላለን፤ ዘዴውን በትክክል ከተገበርነው ከካርቦን ሞኖክሳይድ መመረዝ፣ ከኤሌክትሪክ አደጋ እና በመድኃኒት መመረዝ ውጪ ላሉ አደጋዎች ተጎጂው ለማገገም ብዙም ጊዜ አይወስድበትም፡፡ ለምሳሌ በካርቦን ሞኖክሳይድ መመረዝ ወቅት ጡንቻዎች እና የነርቭ ስርዓት መዋቅሮች ተልፈስፍሰው ሽባ ስለሚሆኑ ወይም ደግሞ ከደም ውስጥ ካርቦን ሞኖክሳይድ ኦክስጅንን ስፍራ ስለሚያሳጣው ጉዳቱ የከፋ ይሆናል፤ ለማገገምም ረዥም ጊዜ ስለሚያስፈልግ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በፊት ላይ ከባድ ጉዳት ሲደርስ፣ በመርዝ በመመረዝና በኬሚካል ንጥረነገሮች መቃጠል ምክንያት የአፍ ለአፍ የአየር እርዳታ መስጠት በማይቻልበት ጊዜ ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀም አለብን፡፡ የአፍ ለአፍ የትንፋሽ እርዳታ ለመስጠት ጉዳተኛው በመጀመሪያ በጀርባው በማስተኛት መዘጋጀት አለበት፤ በመቀጠልም በአንድ እጃችን አፍንጫውን በመዝጋት በሌላኛው ደግሞ አፉን ከፈት አድርገን በመያዝ እርዳታውን መጀመር አለብን፡፡

አንድን ሰው አየር(Oxygen) እንዲያገኝ መርዳት
ተግባር 1፡- አደጋው የገጠመው ግለሰብ አየር ማግኘት ያልቻለው ሙሉ በሙሉ ከሆነ ወይም ራሱን የሳተ ከሆነ፣ የመጀመሪያ ደረጃ የአፍ-ለ-አፍ አየር እርዳታ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ማሳልና መናገር የሚችል ሆኖ አየር በበቂ ሁኔታ ማግኘት የማይችል ከሆነ ደግሞ የበለጠ አየር እንዲያገኝ በማራገብ እገዛ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የአፍ-ለ-አፍ አየር እርዳታ በምንሰጥበት ወቅት ምንም አየር አልተላለፍ ብሎን የመዘጋት ምልክቶች ካየን፣ ሆዱን በመጫን የተዘጋው ነገር እስኪከፈት ሙከራችንን መቀጠል አለብን፡፡ 
ተግባር 2፡- የመተንፈሻ አካሉ በበአድ ነገር ተደፍኖ ከሆነ ማጅራቱን በመምታት እንዲወጣ ማድረግ፤ ባእድ ነገሩ የሚታየን እና የምንደርስበት ከሆነ ደግሞ ጣታችንን በማስገባት በፍጥነት ማውጣት አለብን፡፡ 
ተግባር 3፡- የታችኛውን አገጭ ከስሩ በመጫን ወይም በመግፋት፣ በሁለቱም በኩል የተዘጉ ትቦዎች ወይም የተቀረቀሩ ባእድ ነገሮች ካሉ በመክፈት መፍትሔ መስጠት እንችላለን፡፡
ተግባር 4፡- ባእድ ነገሩን አውጥተን፣ የአየር ማስተላለፊያ ትቦው ከተከፈተ በኋላ፣ አፍንጫውን በጣታችን አፍነን በአፍ-ለ-አፍ የትንፋሽ እርዳታ አየር ወደ ሳንባው እንዲደርስ ማድረግ አለብን፤ በመቀጠልም ከሁለት ተከታታይ የአፍ-ለ-አፍ ትንፋሽ እርዳታ በኋላ ውጤቱ እንዳለ የሚከተሉትን ምልክቶች ማስተዋል አለብን፡፡
ከደረቱ ከፍ እና ዝቅ ማለት መጀመሩን 
በአፍንጫውም ሆነ በአፉ አየር እየገባ እና እየወጣ መሆኑን ማየት 
ተግባር 5፡- ምንም አይነት ውጤት ካልተገኘ የአፍ-ለ-አፍ የትንፋሽ እርዳታውን መቀጠል፡፡
ጥንቃቄ! አልፎ አልፎ በአፍ-ለ-አፍ የትንፋሽ እርዳታ ወቅት ሊያስመልሰው ስለሚችል ሁኔታውን በንቃት መከታተል አለብን፡፡

ምንጭ:- ጤናችን