በባልና ሚስት መሃል ጭቅጭቅ ሲነግስ እንዴት ይፈታል?

                                                

ከሊሊ ሞገስ

ትዳር በባህር ወይም ውቅያኖስ ውስጥ ያለችን ትልቅ መርከብ ይመስላል፡፡ መርከቧ ረጅም ርቀት እንደመጓዟ ለተለያዩ አየር ፀባይ ለውጦች መጋለጧ አይቀሬ ነው፡፡ ፀጥታና ሰላም የሰፈነበት ጉዞ እንደምታደርግ ሁሉ አንዳንዴ ማዕበልና ሞገድ ለበዛበት ነፋስ፣ ለተተናኳሽ ሻርኮች፣ ከበረዶ ክምር ጋር ለግጭት፣ ቀደም ብለው ሳይፈተሹ ላለፉት የቴክኒክ ብልሽቶችና በቅርብ ጊዜ ደግሞ ለባህር ላይ ወንበዴዎች ስትጋለጥ እየሰማን ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ከሆነው አደጋ ለመውጣት ወይንም ቀድሞውኑ ላለመጋለጥ ካፒቴኑ፣ ረዳቶቹና ቴክኒሺያኖቹ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የሚጠበቅባቸውን ጥንቃቄ ካላደረጉ ደግሞ ለመዘረፍ፤ እንደ ታይታኒክም ለመስመጥ፣ ከዚያም ባለፈ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡

ትዳርም እንዲሁ ነው፡፡ የዕድሜ ልክ ኃላፊነት የምንወስድበት፣ ከተለመደው የግንኙነት አካሄድ በዘለለ ራሳችንን ለገባንበት ትስስር መስዋዕት የምናደርግበት፣ መልካምና አሳዛኝ የሆኑ ክስተቶችን የምናስተናግድበት ረጅም የህይወት ጎዳና ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ገጠመኞች ለምን ተፈጠሩ? ብለን ብቻ አንቆዝምም፤ ጠዋትና ማታም እያብሰለሰልን ዕድሜያችንን አንገፋም፡፡ ለችግራችን መሰረታዊ የሆነውን መንስኤውን ማወቅ፣ ለገጠመን ጉዳይ እንዴት መመለስ እንደሚገባን ማተኮር ያስፈልገናል፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ሁለቱ ባለትዳሮች የሚወስዷቸው እርምጃዎች ወሳኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጥንዶች ትዳራቸውን ሊያወፍሩት፣ ሊያቀጭጩት፣ መልካምና አስደሳች አሊያም በሰቆቃ የተሞላ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡

የዛሬው እንግዳችን ጌታቸው የሰላሳ ስድስት ዓመት ጎልማሳ ነው፡፡ ቆንጅዬ ሚስትና የአምስት ዓመት ሴት ህፃን ልጅ አለው፡፡ በሃያዎቹ አጋማሽ ዕድሜው አካባቢ በነበረው የቅድመ ጋብቻ የወሲብ ልምምድ ከቀድሞዋ ጓደኛው የአስር ዓመት ወንድ ልጅ አድርሷል፡፡ ልጁ የሚኖረው ከአያቶቹ ማለትም ከእናቱ ወገኖች ጋር ነው፡፡ ‹‹ባለቤቴ ይህን ከመጋባታችን በፊት ታውቃለች፣ እኔም በተወሰነ ጊዜ እየሄኩ እጠይቀዋለሁ›› ይለናል፡፡

‹‹ይሁንና ባለቤቴ ለሴት ልጃችን በቂ ክብካቤ ሳላደርግ ለወንድ ልጄ ብዙ ትኩረት እንደምሰጥና የተለያዩ ነገሮችን እንድምገዛለት ነገረችኝ፡፡ በትንሽ ነገር ከኔ ጋር መጠላት ጀምራለች፤ አለመግባባት ሲፈጠርም የወንድ ልጄን ጉዳይ ሁሌ ታነሳለች፡፡ የርሱን ጉዳይ ትታው የራሳችንን ህይወት እንድንመራ ብነግራትም ትዳራችን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየገባ ነው ያለው፡፡ በጣም ተጨንቄያለሁ፡፡ ከርሷ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ?›› በማለት ጌታቸው ጠይቆናል፡፡

ወጣትነት ብርታትና ጥንካሬ የሞላበት፣ ብዙ ሰዎች ሊመለሱ ቢናፍቁት የማያገኙት፣ ራሳቸውን ለመለወጥ ቢሞክሩ መሆን የማይችሉበት ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት በህይወት ዘመናችን የምናሳልፈው ጊዜ ነው፡፡ ወጣትነት ከነችግሮቹ በዕውነት ደስ የሚል የህይወታችን አንዱ ክፍል ነው፡፡ አንዳንዶች በእርግጥም ይህን ዘመን በትኩስ ሃይላቸው ይጠቀሙበታል፤ ሌሎችንም ያገለግሉበታል፤ ራዕያቸውንም እውን ለማድረግ የወደፊቱን መሰረት በማስያዝ የተቻላቸውን ያደርጉበታል፡፡ ሌላው ደግሞ በተባለው እየተመራ፤ መኖር የተፈቀደው ለዛሬ ብቻ ይመስላል፡፡ ነገን ሳይመለከት እንዲሁ በዋል ፈሰስ ወርቃማ ጊዜውን ያባክነዋል፡፡

እንግዲህ ከወንድማችን ጥያቄ መረዳት እንደምንችለው በአንድ ወቅት በነበረው የቅድመ ጋብቻ የወሲብ ልምምድ ልጅ ወለደ፡፡ መልካም አደረገ ባንለውም በወቅቱ ለፈፀመው ወይም ለገጠመው ነገር ምንም ሊያደርግና ሊመልሰው የማይችለው ነገር እንደሆነ ሁላችንም እንረዳለን፡፡ ያ ያለፈው ታሪኩ ነው፤ አንፍቀውም፡፡ ልንፍቀው እንሞክር ብንልም መላጥ፣ ማድማትና ማቁሰል ነው የሚሆንብን፡፡ ስለዚህ… ከሄድን ሁል ጊዜም ቢሆን ሊፈጠር ወይም ሊከሰት የሚችል ነገር እንዳለ ቀድሞውኑ ማሰብ ነው፡፡ አያችሁ በድርጊታችን ልጅ ሳይፈለግ ወደዚህ ምድር ይመጣል፤ ለኤች.አይ.ቪና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች መዳረግ አለ፤

ከቤተሰብና ጓደኛ መገለል፤ እግዚአብሔርን ማሳዘን ይመጣል፣ ለተለያዩ ማህበራዊና ስነ ልቦና ችግሮች መጋለጥ ይኖራል፡፡ አያችሁ በወጣትነት ዘመን ሁሌ ቸበርቻቻ የለም፤ አንዳንዴ የሚጎረብጡ ሁኔታዎችንም ማሳለፍ አለ፡፡ አካሄዳችንን ካላስተካከልን፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድም ካላደረግን ደግሞ ዘወትር ልንረሳው የማንችለውን ጠባሳ ነው የምንሸከመው፡፡ ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ የምንመክረው ከጋብቻ በፊት ያለ ማንኛውም ግንኙነት ለቀጣይ ህይወታችን መሰረት የምንገነባበት ጊዜና ወሳኝ ቢሆንም የወሲብ ልምምድ ማድረግ ግን አይጠበቅብንም፤ አይጠቅምም፡፡ ብዙዎቻችን አድርገን አልፈን ይሆናል፤ ግን ገንቢ አልነበሩም፡፡ ለጊዜው ተደስተንባቸው ይሆናል፤ መጨረሻቸው ግን አያምርም፡፡ ሐጢያት ከመሆኑም ባሻገር ዘርፈ ብዙ ለሆኑ ችግሮችና ጭንቀቶች ይዳርጉናል፡፡ ልምምዱን ከጋብቻ በኋላ ለጋብቻና ለትዳር ብቻ ማድረግ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ነገር ያልተፈለገ እርግዝና በሁለቱ ሰዎች ላይ ከሚደርሰው የስሜት ችግርና ማህበራዊ ጫና ባሻገር በተወለደው ልጅ ላይ የሚገጥመው ሚዛናዊ ያልሆነ አስተዳደግ በወደፊት ስብዕናው ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉ ነው፡፡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚያስቡት የራሳቸውን ጊዜያዊ ችግር ከመቅረፍ እንጂ ሳይፈልግ ወደዚች ምድር በሚያመጡት ልጅ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር አያስተውሉትም፡፡ ይህን በምን መንገድ እንደፈቱት ሊፈቱት እንደሞከሩ ባናውቅም አንድ እውነታ አለ፡፡ ተለያይተው ነው የሚኖሩት፡፡ አባት ሌላ ትዳር መስርቶ በሌላ ዓለም ውስጥ ሲመላለስ ልጅ ደግሞ ከእናቱና ቤተሰቧ ጋር ሌላ ህይወት ይገፋሉ፡፡ ከዚህ የሚከፋው ደግሞ አሁን ባለ ው አዲስ ህይወት ላይ በፊት የተፈጠረው ችግር ከአሁኑ ላይ ሌ ላ ችግርን እየወለደ ትዳርን መበጥበጡ ነው፡፡ እየተረዳችሁን ነው?

ከላይ ያነሳናቸውን መነሻዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በወንድማችን ትዳር እያንዣበበ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ይበጃሉ የምንላቸው ምክሮች ካነበብናቸውና በህይወታችን ተሞክሮ ካየናቸው ነገሮች በመነሳት የሚከተሉትን አቅርበናል፡፡ (ይሁንና እነዚህ እውነታዎች በሌሎች የባልና ሚስት ጭቅጭቅ ችግሮች ውስጥ መፍትሄ ሊሆኑ እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል)

– የችግሩን መንስኤ ማወቅ

በእርግጥ ላለመግባባታችሁ ምክንያት የሆነው የወንድ ልጅህ ጉዳይ ነው ብለህ ታስባለህን? መሸፈኛ ላለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ ነህ? ተፈጠረ ለምትለውስ ችግርና አለመግባባት ባለቤትህ ሳትሆን አንተ ለችግሩ ያበረከትከውን ነገር እንዳለስ አስበህ ታውቃለህ? አየህ መጀመሪያ እነዚህን መለየትና መሰል ጥያቄዎችን መመለስ የመጀመሪያ ጉዳይህ ሊሆን ነው የሚገባ ህ፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው መጀመሪያ ከራስህ በኩል ያለውን ስታስተካክልና ስታፀዳ ነው፡፡ ሁሉም ቤቱን ቢያፀዳ አካባቢም ንፁህ ይሆናል እንደሚባለው ነው፡፡

የኛ ችግር ምን መሰለህ? ብዙውን ጊዜ ለችግሮቻችን ሌላው ላይ መቀሰርና ሁኔታዎች ላይ ማላከክ እንጂ የለመድነው ወደራሳችን መልሰን መመልከቱን አናስብም፡፡ እንዲህ አደረጉብ ኝ፤ ይህን ሰጡኝ እንጂ ጉዳዩ ለመከሰቱ የኛ እጅ አለበት፤ የስራ ዬን አገኘሁ አንልም፡፡ በእጃችን ያለውን መፍትሄ ሳንጠቀም ሌላ አዲስ ነገር እንፈልጋለን፡፡ ባለን ሳናመሰግን የሌለንን እንናፍ ቃለን፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ምክራችን የሚሆነው ከርሷ ጋር ምን ላድርግ ሳይሆን ከኔ በኩል ምን ላድርግ ብለህ ራስህን እንድትጠይቅና ለችግሩ ትክክለኛውን መንስኤ እንድታውቅ ነው፡፡ መቼም ወደህና ፈቅደህ ያለህበትንና ያሳለፍከውን ሁኔታ ተረድታ ነው ያገባችህ የሚል እምነት አለን፡፡

ቃል ኪዳናችሁን አክብሩ

በየትኛውም ስርዓት ተጋቡ ብቻ በሰርጋችሁ ዕለት አንዳችሁ ለሌላኛው ቃል መግባታችሁ አይቀርም፡፡ በተለይ ደግሞ መንፈሳዊ ጋብቻ ሲሆን በእግዚአብር በጉባኤ መካከል የገባችሁትን ቃል ማስታወስ ነው፡፡ ጋብቻ ውስጥ መጎርበጥ ቢኖርም፣ መውደቅ መነሳት ቢፈጠርም ቃል ኪዳናችሁን ማሰብ ተገቢ ይመስለናል፡፡ ስለዚህ ከመጋባታችሁ በፊት ስለልጁ ጉዳይ ከተነጋገራችሁ እንዴት ልታሳድጉት ነበር ያሰባችሁት? ልትረዱትስ ተነጋግራችኋል? የተባባላችሁትን እናንተው ስለምታውቁ ያንን ኃላፊነት በተሰማው መንገድ መጠበቅ ነው፡፡

ልጅህን በፊት አልረዳውም፤ ምንም አላደርግለትም ብለህ ነግረኻት ከሆነና አያቶቹና እናቱ ይበቁታል ብለህ ወደ ትዳር ከገባህ ያንን ማክበር ነው፡፡ እርሷም ምንም ችግር የለም፤ ዋናው ፍቅሩ ነው በውጪ ሆኖ ልትረዳው ትችላለህ ብላህ ከነበረ ቃሏን መጠበቅ ይኖርባታል፡፡ ጠቅልለህ ቤትህ ካስገባሃት ወይም ጠቅላላ ቤት ከገባች በኋላ ባህሪያችሁንና የገባችሁትን ቃል አጥፋችሁ ከሆነ አግባብ ይመሰለንም፡፡

ደግማችሁ በግልፅ ተነጋገሩ

ከላይ የጠቀስነው ነገር ሊሰራ መስሎ ካልታያችሁና፣ ቃላችሁን ማጠፍ ከጀመራችሁ ማድረግ የሚገባችሁ ነገር በጉዳዩ ላይ መነጋገር ነው፡፡ በስሜት ተገፋፍታችሁና የነበራችሁበት ወቅታዊ ፍቅር አርቃችሁ እንዳትመለከቱ ካደረጋችሁ ደግማችሁ በጉዳዩ ላይ በግልፅ መወያየት ነው፡፡ መቼም እንደ ባለአዕምሮ ሰው አትርዳው አትልህም፤ አንተም እርሷ እንዳለችው ከሴት  ልጅህ በማስበለጥ እየረዳኸው ካለ አግባብ ነው ለማለት አንደፍርም፡፡ ሁለቱም ልጆችህ ቢሆኑም በአንድ አይነት ማየት አለብኝ ብለህ መሰብ ግን የዋህነት ነው የሚመስለን፡፡ ለዚህም የአብርሃምን ታሪክ ማስታወሱ የምንልህ የበለጠ ይገባሃል የሚል እምነት አለን፡፡

አብርሃም ሚስቱ ሳራ መውለድ ባልቻለችበት ወቅት አገልጋይ ከሆነቻት አጋር ጋር እንዲተኛ ፈቀደችለት፡፡ ኢስማኤል የተባለ ልጅም አገኘ፡፡ ሳራም በእግዚአብሔር ዘንድ መጎብኘትዋ በደረሰ ጊዜ ፀነሰች፣ ይስሃቅንም ወለደች፡፡ ይሁንና ኢስማኤል ከይስሃቅ ጋር እኩል በአባቱ ቤት ያድግ ዘንድና ያለውንም ይካፈል ዘንድ ሳራ ደስተኛ አለነበረችም፡፡ አጋርን ከነልጁ ያሰናብታቸው ዘንድ ጠየቀችው፡፡ አብርሃምም የተባለውን አደረገ፡፡ አብርሃም ልጁን ኢስማኤልን ጠልቶት ይመስልሃል ከአጋር ጋር እንዲሄድ ያደረገው? ከቃልኪዳን ሚስቱ ከሳራ ሀሳብ ጋር በመተባበር አይመስልህምን? የተስፋውን ልጅ ይስሃቅን የመረጠው ዝም ብሎ ይመስልሃልን? አየህ በቃል ኪዳን የተገኘ ለጅና በመወስለት የመጣ አንድ አይደለም፡፡ ከዚህ የምንማረው ነገር ያለ ይመስለናል፡፡

ባለቤትህን አማክር

ሌላው ስለትዳር ሲታሰብ ሁሌ መዘንጋት የሌለብህ ነገር ከጋብቻ በኋላ የኔ የሚባል ነገር የለም፡፡ የእኛ የሚባል አጀንዳ ነው የሚመጣው፡፡ ያንተ ጉዳይ የርሷ ነው፤ የርሷም ደግሞ የአንተ ነው፡፡ ለልጅህ የምታወጣውን ጊዜና ገንዘብ ከባለቤትህ ጋር በመመካከር ሊሆን ይገባል፡፡ አንድ ነገር ማሰብ ያለብህ ልጅህን መርዳትህ ወንጀል ባይሆንም፤ ሄደህ መጎብኘትህንም ማንም ባይጠላውም መርሳት የሌለብህ ነገር ልህንን ልታይ ስትሄድ የቀድሞ ጓደኛህንም የማግኘቱ አጋጣሚ የሰፋ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከባለቤትህ ፈቃድና እውቅና ውጪ ሲዘወተር ሌላ ነገር እንድትጠረጥር ያደርጋታል፡፡ ሰው ነችና ደግሞ ቢሰማት ሊገርምህ አይገባም፡፡ በትዳራችሁ ላይ የወንድ ልጃችሁ ጉዳይ እስከገባ ድረስ የርሱን ነገር ተይው ልትላት አይገባም፡፡ ልጁ እኮ እያነጋገራችሁ ነው? ልጁ እኮ ላለመግባባታችሁ መንስኤ እየሆነ ነው፡፡ የራሳችሁን ኑሮ ለመኖር ከፈለጋችሁ በጋራ ጉዳያችሁ ብቻ ነው ልታተኩሩ የሚገባው፡፡ ግን እውነታውን እንይ ካልን አይደለም ከአብራካችን ስለወጡት ልጆች ከሌላውም ጋር ቢሆን መገናኘታችን፣ መነካካታችን የግድ ይላል፡፡ ደሴት ሆነን ልንኖር አልተጠራንም፡፡ ስለዚህ የርሱን ነገር ትተሽ የራሳችንን ኑሮ ብቻ እንኑር አትበላት፡፡ አማክራት፡፡ ነገሩን በመሸሽ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ልናመጣ አንችልም፡፡ ነገሩን አዳፍነነው በአፈር ሸፋፍነነው ላሁኑ በዚሁ ብናልፍ ዝናብ ሲዘንብበትና ነፋስ ሲመጣበት አግጦ መውጣቱ አይቀርም፡፡ S

– የእግዚአብሔርን ቃል አጥኑ

ከላይ ያነሳናቸው ጠቃሚ ምክሮች ቢረዷችሁም በትዳራችሁ ዘላቂ የሆነ ውጤት እንድታመጡ ግን ከናፈቃችሁ ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ማሰብ ነው፡፡ ክርስቲያን እንደመሆናችሁ ለማሰብ ከዛም ባለፈ የሚታየ ለውጥ በህይወታችሁ ለማምጣት ቃሉን ማጥናት መልካም ነው እንላለን፡፡ ቃሉ ህይወት አለው፤ መዳን በርሱ በኩል ብቻ እንደሆነ ነው የሚናገረው፡፡ አየህ ቃሉ ውስጥህ ሲገባ ተመሳሳይ ስሜት አይኖርህም፡፡ ስታጠፋ ይወቅስሃል፤ ስታዝን ያፅናናሃል፤ ስትደክም ያበረታሃል፤ ከመንገድ ወጣ ትስትልም ወደ ቀናው ጎዳና ይመልስሃል፡፡

ስለዚህ ይህን ማድረግ በህይወታችሁ ስትለማመዱ እናንተ ስላላችሁ ወይም ልጆቻችሁን ስለተንከባከባችሁ ብቻ በስርዓት ያድጋሉ ማለት እንዳልሆነ ትረዳላችሁ፡፡ አብርሃም ልጁን ከአጋር ጋር ሲሰድ እግዚአብሔር ዝም አላላቸውም፡፡ በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ይረዳቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ቃሉ ሲገባችሁ ልጅህ የመከራከሪያ አጀንዳ፤ ላለመግባባታችሁ መንስኤ አይሆንም፡፡ ያላችሁን ነገር ለአምላካችሁ አሳልፋችሁ መስጠት ትጀምራላችሁ፡፡ የሰጣችሁትንም ይጠብቅና ያሳድግ ዘንድ እርሱ ታማኝ ስለሆነ ቃሉን ዕለት ዕለት ለማጥናት ሞክሩ፡፡

እንግዲህ ይበጃችኋል ብለን ያሰብነውን በተለያየ አቅጣጫ ለመጠቆም ሞከርን፡፡ ለውጥና ፍተሻ ከራስ ነውና የሚጀምረው ስራህን በራስህ እንድትጀምር፤ እንድትመካከሩ፤ በግልፅ እንድትወያዩ ቃል ኪዳናችሁንም በማክበር የአምላካችሁን ቃል ተግባራዊ እንድታደርጉ አውግተናል፡፡ እኛ እንግዲህ መጠቆምና አቅጣጫ ማሳየት እንጂ ተሳታፊዎቹ እናንተው የችግሩ ባለቤቶች ስለሆናችሁ ከዚህ በላይ ልንሄድ አንችልም፡፡ ሁሉን የሚችለው አንድዬ እርሱው ይርዳችሁ፡፡ ለዛሬ አበቃን፡፡ 

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement