በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ልጆች ምቹ የሆኑ ዘጠኝ ሀገራት ይፋ ሆኑ::

                                              

ሰዎች በአዲስ ስራ ፍለጋ ወይም በሌላ የህይወት አጋጣሚ ምክንያት ወደ ሌላ ሀገር ሊጓዙ ይችላሉ፡፡

የተጓዙበት ሀገር ማህበረሰብ፣ የአየር ሁኔታ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችም ምቾት ሊሰጧቸው ወይም “ሀገሬ ማሪኝ” ሊያስብሏቸው ይችላሉ፡፡

በዓለም ደረጃ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 46 በመቶዎቹ ቤተሰብ መስርተው ልጆች የወለዱ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 21 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ልጆቻቸውን እየኖሩበት ባለው ሀገር እያሳደጉ የሚገኙት፡፡

ኢንተር ኔሽንስ የተሰኘ የጥናት ቡድን በውጭ ሀገር በሚኖሩ 3 ሺህ ቤተሰቦች ላይ ቅኝት በማድረግ ቤተሰብ ለመመስረት እና ልጆችን ለማሳደግ ምቹ የሆኑ ሀገራትን ደረጃ ለማውጣት ሞክሯል።

በጥናቱም ስዊዘርላንድ፣ ሩሲያ እና አውስትራሊያ ከውጭ ሀገር ለመጡ ቤተሰቦች ምቹ ባለመሆን የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

በአንጻሩ በውጭ ሀገር ልጆችን ለማሳደግ ምቹ የተባሉ ዘጠኝ ሀገራት ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፡፡

1. ኡጋንዳ

በኡጋንዳ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ያለው የሀገሪቱ ማህበረሰብ ለኑሮ ምቹ ለልጆቻቸውም መልካም አቀራረብ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ ከሚገኙ የውጭ ቤተሰቦች መካከል 68 በመቶዎቹ ልጆቻቸውን በኡጋንዳ በማሳደጋቸው እና ቤተሰብ መስርተው በመኖራቸው ሙሉ በሙሉ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

2. እስራኤል

በጥናቱ መሰረት እስራኤል ልጆች ላሏቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ምቹ በመሆን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ቴል አቪቭ በተለይም ሀገሪቱ ለውጭ ዜጎች እና ለልጆቻቸው ባላት የጤና እና የትምህርት ፖሊሲ ነው ተመራጭ የሆነችው፡፡

3. ታይዋን

ታይዋን ከውጭ ሀገር መጥተው ኑሯቸውን በሀገሪቱ ለመሰረቱ ቤተሰቦች ከእለታዊ ህይወት ጀምሮ እስከ ፋይናንስ ጉዳዮች ድረስ በጥሩ ኑሮ ላይ እንዲገኙ በማድረግ ትጠቀሳለች፡፡

በጥናቱ ከተካተቱ በሀገሪቱ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች መካከል 97 በመቶ ያህሉ መላሾች ታይዋናውያን ለልጆቻቸው ጥሩ አመለካከት እንዳላቸውና የውጭ ሀገር ዜጋ ናቸው በሚል እንደማያገሏቸው ነው የገለፁት፡፡

4. ኮስታሪካ

ይህቺ ሀገር የውጭ ሀገር ዜጎች ለኑሮ ውድነት የማይዳረጉባት እና ሁሉ ነገር ርካሽ የሆነባት መሆኗ ይነገራል።

በኮስታሪካ የሚኖሩ 74 በመቶ የውጭ ሀገር ዜጎች በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ ለልጆች ምቹ የመዝናኛ ስፍራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በጥናቱ ውስጥ 91 በመቶ ያህሉ የውጭ ዜጎች የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆቻቸውን እንደሚያቀርቡ እና እንደዜጋ እንደሚመለከታቸው መስክረዋል፡፡

5. ታይላንድ

እስያዊቷ ሀገር ከሌሎች ሀገራት መጥተው ቤተሰብ ለመሰረቱ ሰዎችና ለልጆቻቸው ጤና ትኩረት በመስጠት የምትታወቅ ሲሆን በሀገሪቱ ከሚኖሩት የውጭ ዜጎች መካከል 76 በመቶዎቹ እርካታ እንደሚሰማቸው መስክረዋል፡፡

6. ግሪክ

ግሪክ ለውጭ ዜጎች ምቹ በመሆን ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ ብትሰለፍም በትምህርት አገልግሎቷ ደካማ ናት ተብሏል።

7. አውስትራሊያ 

በአውስትራሊያ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ለቤተሰባቸው ህይወት እና ለስራ ምቹ መሆኗን ቢጠቅሱም ልጆች የሚዝናኑባቸው ምቹ ቦታዎች ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

8. ሜክሲኮ

ሜክሲኳዊያን ከሌሎች ሀገራት በስራ ወይም በሌሎች የህይወት አጋጣሚ ለሚመጡ ሰዎች አቀባበላቸው መልካም እንደሆነ፣ በኑሮም ተስማሚ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

9. ቱርክ
በቱርክ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች አንካራ ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳድጉ እንደምታበራታታ ገልፀዋል፡፡

ሆኖም በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት የልጆች እና የቤተሰባቸው ደህንነት ስጋት ውስጥ መውደቁን በደካማ ጎኗ አንስተውታል፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement