ወንዶችን መሀን የሚያደርጉ አዳዲስ ምክንያቶች ይፋ ተደረጉ!

ሁሉም ሰው ልጅ ማለት ይችላል ራሱን ተክሎ ማለፍ፣ አይኑን በአይኑ ማየት ይፈልጋል፡፡ ጉዳዩ የፆታ ገደብ ባይኖረውም እርግዝናውንም ምጡንም ሴቶች ስለሚከውኑት ጉጉቱ በእነሱ ይበረታል፡፡ ፍሬ ማየት ሲዘገይም ጥያቄው ወደ ሴቲቱ ማመዘኑ በተለይ በኢትዮጵያ የተለመደ ነው፡፡ ይሁንና በህክምናው ሳይንስ የተረጋገጠው ቢያንስ 40 በመቶ የጥንዶች ልጅ ማጣት መንስኤ ወንዱ ጋር ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም የወጡ የተለያዩ ምርምሮች በህክምናው የሚፈቱና የማይፈቱትን ዘርዝረው ቢያሳውቁም ከአኗናር ዘዬ እና ልምዶች ጋር የተያያዙት ላይ ትኩረቱ እጅግም ነበር፡፡በቅርቡ ይፋ ሆኑ የጥናት ውጤቶች በስራ እና ኑሮ ውጥረት ውስጥ የሚዋልሉ ወንዶች፣ እንደ ካናቢስ ያሉ ሱስ አስያዥ መድሀኒቶች መዝናኛ ያደረጉ ዘመናዊ ወጣቶች፣ በከባድ ፀሀይና ሙቀት ለረጅም አመታት ስራ ውስጥ ያሉ ወንዶች ልጅ የማግኘት እግላቸውን በከፈተኛ ሁኔታ ጫና ውስጥ እየከተቱ ነውና ቆም ብለው ራሳቸውን ይመልከቱ እያሉ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፣ ከጥርስ ሳሙናዎ እሰከሚወስዱዋቸው የተለያዩ መድሀኒቶች ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎችም የራስቸው አሉታዊ ተፅእኖን ፈጣሪ ናቸው፡፡ እርስዎ ወይም የቅርብ የሚሉት ሰው ከዚህ ይመደባል?እባክዎ ትኩረት ያድርጉና ዝርዝሩን ይረዱ የዛሬው ትኩረታችን ይኸው ነው፡፡

ውጥረትና የኑሮ ውጣ ውረድ

ሰው ወዶ ባይጨነቅም አንዳንዱን የኑሮ ውጣ ውረድ ግን ቸል ብሎ ጤና ላይ ትኩረት ማድረግ ካልተቻለ በወንዶች የልጅ አባትነት ህልም ላይ እንቅፋት ይሆናል፡፡ የሄን ያስታወቁት በአሜሪካው የኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ ሜይልማን የህዝብ ጤና ትምህርት ቤት ከ38-49 የእድሜ ክልል ባሉ ወንዶች ላይ ጥናትን ያደረጉ ባለሙያወች ናቸው፡፡ ተመራማሪዎቹ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ቢናገሩም በጥናትቸው ግን በእለት ከእለት የኑሮ ውጥረት ውስጥ የሚገኙ ወንዶች ግሉኮኮርቲኮይድ የተሰኘውን ሆርሞን ከልክ በላይ ሰለሚያመርቱ የወንዶችን ዘር በሚያመርቱ ሌሎች ሆርሞኖች ስራ ላይ መስተጓጎል ይፈጠርባቸዋል፡፡ ውጥረትና ጭንቀት ብቻውን የመውለድ ብቃትን ባያስቀርም ከሌሎች ምከንያቶች ጋር በተደራቢነት ሆኖ የልጅ አባትነት ሂደትን ሊፈትን ይችላልና ወንዶች ሆይ ጭንቅላታችሁን ወጥሮ የሚይዛችሁን የህይወት ጉዳይ በሚቻል መጠን በጊዜ መፍትሄ ስጡት ሲሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

‹‹አሪፍ›› ወጣቶች ወደፊት ልጅ መውለድ አትፈልጉም?

ነፍሱን ይማርና ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚያብሄር ስለወጣትነት ሲፅፍ ‹‹ወጣት ስትሆን ሁሉን መሆን ትፈልጋለህ፤ ምንም ነገር አይቸግርህም፤ ሁሉን የመሆንና የማድረግ ስሜትህ ጉደኛ ነው፡፡›› ብሎ ነበር፡፡ ሃሳቡን ቃል በቃል አላስቀመጥኩትም የሆነ ሆኖ ወጣትነት እንደዚህ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ወጣቶች ለብዙ በጎ ወይም ክፉ ተፅእኖዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡ ጥሩ ስሜት ውስጥ ለመግባት፣ ለመዝናናት በሚል ጥቅም ላይ ከሚውሉት ከተለመዱት አልኮል መጠጦች እና ሲጋራ በተጨማሪ አደንዛዥ እፆች ለብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መዝናኛ ናቸው፤ የኑሮ ዘዬ የሆኑበት ሰፈር እና ት/ቤቶችም ጥቂት አይደሉም፡፡

በእንግሊዙ የሼፊልድ ዩኒቨርስቲ የተደረገውና ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነ ጥናት ካናቢስ ተጠቃሚ የሆኑ ወንዶች የዘር ፈሳሽ (ስፐርም) ቅርፅ እና መጠን በእጅጉ ተጎድቶ ታይቷ፡፡ ‹‹ካናቢስ እና መሰል እፆችን መጠቀም በስፐርም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል የሴቷን እንቁላል የመስበር ብቃቱን ያሽመደምደዋል፡፡ ዱልዱም ጥይትን ከጠመንጃ ላይ እንደመተኮስ ልትወስዱት ትችላላችሁ፡፡›› ይላሉ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር አለን ፔሲ በጥናታቸው፡፡

እድሜያቸው ከ20እስከ 30 ባሉ ወጣቶች ላይ የተደረገውን ጥናት የመሩት ባለሙያዎች እንደሚሉት የስፐርም ምርት አጠቃላይ የምርት ሂደት ሦስት ወር የሚፈጅ በመሆኑ ዛሬ እፅ መጠቀምን ማቆም ከወሰኑ በሦስት ወር ውስጥ ሙሉ ጤነኛ ስፐርም ስለሚያገኙ እንቁላሉን መስበር አይቸገሩም ብለዋል፡፡ ወጣቶች ከእለት መዝናናት ባለፈ አስተውሎት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ አመታት ከነጎዱ

የኬሚካሎች ተፅዕኖ

የጀርመንና ዴንማርክ ተመራማሪዎች ጥናት ደግሞ ትናት ያደረጉት በተለያዩ ምርቶች የምንወስዳቸው ኬሚካሎች በወንዶች ስፐርም ብቃት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ላይ ነበር፡፡ ሳይንቲስቶች ምርመራ ካደረጉባቸው 96 ውህዶች ውስጥ የሚበዙት በፀሀይ መከላከያ ቅባቶች፣ የጥርስ ሳሙና፣ ፀረ-ባክቴሪያ ሳሙናዎችና መሰል መጠቀሚያዎች የሚገኙ ኬሚካሎች ሲሆኑ ለነዚህ ኬሚካሎች በብዛት መጋለጥ በስፐርም ውስጥ የካልሲየም ማዕድን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ የስፐርም ህዋሳቱን የመንቀሳቀስና የመዋኘት ብቃት ያዛባውና የሴቷን እንቁላል ሰበሮ ገብቶ የመዋሃድና ጽንስ የመፍጠር አቅሙን ያሳንሰዋል ብለዋል በምርምራቸው፡፡ ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው በላብራቶሪ ውስጥ የወንዶችን ስፐርም በናሙናነት ወስደው የተመለከቱ ሲሆን በቀጣይ በአይጦችና ሌሎች እንስሳት ላይ ኬሚካሎቹ የሚያደርሷቸውን ጉዳቶች በስፋት አጥንተው እንቅጩን ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጉዳዩ በአውሮፓ ከፍተኛ መወያያ የሆነ ሲሆን አገራት የኬሚካሎቹን ተፅእኖ ለመቆጣጠር ደንብ እንዲያወጡም መነሻ ሊሆናቸው እንደሚችል ተዘግቧል፡፡

ለጊዜው የኬሚካሎቹ ተፅእኖ ለእኛ ወንዶች እጅግ የቀረበ ባይሆንም ምርምሮቹን ማንበብና ማስወገድ የምንችለውን በማስወገድ ‹‹ወንድነታችንን›› መንከባከብ ወሳኝ ይሆናል፡፡ ከዚህ ሌላ በተለያየ ስራ ምክያት በከፍተኛ ሙቀት መጠን ባለባቸው የስራ አካባቢዎች የሚኖሩና የሚሰሩት ወንዶችም በመውለድ ብቃታቸው ላይ እክል ሊፈጠር ስለሚችል ራሳቸውን በጊዜ ቢፈትሹ፣ የባለሙያ እገዛንም ቢፈልጉ መልካም ይሆናል፡፡የልጅ አባት የመሆንን ፀጋ ተንከባከቡ ነው የምርምሮቹ መድረሻ፡፡

Advertisement