ለምን ራስዎን ከሌሎች ጋር ማነጻጸር ያቆማሉ?

                        

 ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደርና ማነጻጸር የተለመደና በስፋት የሚስተዋል ጉዳይ ነው።

ይሁን እንጅ ይህን መሰሉ ነገር የበዙ አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ራስን ከጓደኛ፣ ከስራ ባልደረባ፣ ከታዋቂ ሰዎችና ሃብታሞች ጋር ማወዳደር የተለመደ ሲሆን ይስተዋል።

ይህ ራስን ከሌሎች ጋር የማነጻጸርና የማወዳደር አባዜ ምናልባት ጥቂት ከፍ ወዳለ ነገር ለመድረስ ከማሰብ ከሚመጣ የስሜት ርሃብ ሊመነጭ ይችላል።

በጣም በበዛ መልኩ ግን ንጻሬው ከማሰብ የዘለለ ውጤታማ ሲሆን እንደማይስተዋል ነው የስነ ልቦና ባለሙያዎች የሚናገሩት።

ምክንያቱም ሌሎች የደረሱበት ለመድረስ ራስን ማነጻጸርና መመኘት ሳይሆን፥ የራስን ጥረት ማድረግና መሞከር ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ።

ከንጻሬ ይልቅ ራስን ከራስና ከጊዜ ጋር እያወዳደሩ አሁን የቆሙበትን ከትናንቱ ጋር ማመሳከርና ለውጡን መገምገም የተሻለም ይሆናል።

ከዚህ አንጻርም ራስን ከሌሎች ጋር ማነጻጸርና ማወዳደር ማስወገድ ይገባል ይላሉ፤ ምክንያቱም፥ 

ተስፋ አስቆራጭ ስለሚሆን፦ በኑሮ ስኬታማና ባለፀጋ የሆነን ሰው ህይዎት ማየትና የእርሱን ስኬት መመኘት ከህልም የዘለለ አንድምታ የለውም።

በሰሩት ስራ ውጤታማ በመሆን አንቱታን ያተረፉ ሰዎችን ሊመለከቱም ይችላሉ፥ የዚህ ስኬት ባለቤትና ተቋዳሽ ግን ባለቤቱ እንጅ ስኬቱን የሚመኘው ተመልካች አይሆንም።

የሰዎች ስኬታማ የአኗኗር ሁኔታና ዘይቤም ለተመልካች እንጅ ለባለቤቱ ምንም ነው፤ ምክንያቱም እርስዎ የሚመለከቱት የዛሬውን ስኬታቸውን እንጅ የመጡበትን መንገድ አይደለምና።

ገጻቸው ላይ የሚመለከቱት የደስታ ስሜትና የሚታይባቸው ሳቅ ከረጅም ጊዜ ልፋትና ስቃይ በኋላ የተገኘ እንደሆነም አያስቡም።

በዚህ ሳቢያም “የእነርሱ ስኬት እኮ የህልም አለም እንጅ የሚደረስበት አይደለም” የሚል እሳቤን በመያዝ ወደ ስኬት የሚያመሩበትን መንገድ ይዘጋሉ።

ከዚህ ባለፈም ተስፋ አስቆራጭ እና የማይደረስበት ግን ደግሞ የሚመኙትን አይነት ህይዎት ለመምራትና ለማግኘት የሚጀምሩትን ጉዞ ባጭሩ ይቋጩታል።

ይህ አይነቱ ንጻሬም ራስን ለውድቀት ይዳርጋልና፥ ራስን በማነጻጸር በከንቱ ከማለም የቻሉትን ያክል የራስዎን ነገር መሞከርን ይልመዱ።

ለሰዎች የተሰጠው የተለያየ በመሆኑ፦ አንዳንድ ጊዜ ህይዎት በራሷ ፍትሃዊ የማትመስልባቸው ጊዜያት አሉ።

አንዳንዱ የገንዘብ አቅም ካላቸውና ከባለፀጋ ቤተሰቦች ሲፈጠር አንዳንዱ ደግሞ ከዚያ ፍጹም ተቃራኒ ከሆኑ ቤተሰቦች ይፈጠራል።

ከዚህ አንጻር ባለፀጋዎቹ ቤተሰቦች በጣም አዋጭና አትራፊ የንግድ ስራዎችን፥ ያላቸውን ሃብትና ስም በመጠቀም በቀላሉ ሊያገኙት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ ከስራቸው አንጻር ካላቸው ማህበራዊ ትስስሮሽና ተቀባይነት አንጻር የሚመጣ ነው፤ ይህም ስኬታቸውን የተሻለ ያደርገዋል።

በአንጻሩ በሌላኛው አቅጣጫ ያለ ሰው ከዚህ ተቃራኒው ያጋጥመዋል።

እናም ይህን መሰሉን ስኬት እየተመኙ ሳለ የእርስዎን የኑሮ ሁኔታ እያስተዋሉ፥ “ከእነዚህ ጋር እንዴት መፎካከርና ስኬታቸውንስ እንዴት ማጣጣም ይቻላል” በሚል እሳቤ ራስዎን ያሰንፋሉ።

አለፍ ሲልም የመወዳደሪያ መድረኩ ያልተመጣጠነና ለአንዱ ብቻ የተሰጠ መሆኑን ማሰብና ማመንም ይጀምራሉ።

ያን ጊዜ ለመቀበል የሚከበድ አይነት እውነት ያደርጉትና ከመሞከር ይልቅ ቁጭ ብለው በተመኙት ልክ ሁኔታዎችን ይዳኛሉ።

በዚያው መጠንም ከመንገድዎ ይወጣሉ፤ ይህን መሰሉ ራስን የማነጻጸር አባዜም በዚህ መልኩ እርስዎን ከመሞከር ያግድዎታልና ቢቻል ባያስቡት መልካም ነው።

ከማነጻጸር ይልቅ ውጣ ውረዱ ቢበዛም የራስን መሞከርና መጣር የተሻለም ይሆናል።

ወዳጅነትን ወደ ባላንጣነት ስለሚቀይር፦ በሚኖሩበት አለም ምንም ቢሆን በሌሎች ስኬትና ውጤታማነት ሊደሰቱ ይገባል።

ይህን ሲያደርጉ ቢያንስ ከሰዎች መልካም ነገርን በመቅሰም የእርስዎን ጥሩ ነገር የሚያጎሉበትን እድል ያገኛሉ።

ከዚህ በተቃራኒው ሞክረው አልሳካ ሲልዎት “የእነርሱ ስኬት ለእኔ የውድቀት ምንጭ ነው” የሚል መጥፎ እሳቤ ውስጥ ከገቡና በዚያው መንገድ ከተጓዙ ግን ውጤቱ ተቃራኒ ይሆናል።

ዘወትር “በእነርሱ ምክንያት እንዲህ ሆኛለሁ” የሚቀድም ከሆነም በክፋት ታውረው የእርስዎን መልካም ነገርም አያስተውሉትም።

እናም የሰዎችን የስኬት መጠን በማየት ራስዎን በዚያ ደረጃ ማነጻጸር ሳይሆን ከስኬታቸው መልካም ነገር መውሰድና በራስዎ ላይ ብቻ ማተኮር መልካም መሆኑን ይመክራሉ።

ከዚህ ባለፈ ግን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ዘወትር ሳይሆን ከጊዜ ጋር የሚደረግ ንጻሬ ሁለት ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይገልጻሉ።

ከዚህ አንጻር በዚያ መልኩ የሚደረግ ንጻሬ የተስተካከለ እቅድ እንዲይዙ በማድረግ ከመነሻ እስከ መድረሻዎ ያለውን መንገድ ቅርፅ ይሰጡታል።

ስለሚፈልጉት ነገር ጥርት ያለ ሃሳብ እንዲኖር በማድረግ ለተጨባጭ ውጤቶች የተስተካከለ ሃሳብ እንዲኖር ያግዛሉ።

በተጨማሪም ችግሮችን መለያ እና መመልከቻ መንገዶች በመሆንም ያገለግላሉ።

ምናልባት ቀደም ባለው ጊዜ በብቃት የተወጡትን ስራ ወይም ተግባር አሁን ላይ መፈጸም አቅቶዎት ከሆነ፥ መሰል አጋጣሚዎች ችግሩን መለያ መንገድ ይሆናሉ።

ከዚህ አንጻርም ለሚመጣው ፈተና ጥሩ መዘጋጃም ሊሆኑም ይችላሉ።

ሁልጊዜም ቢሆን ግን የለውጥ ሂደቶችን እያስተዋሉ ይሂዱ፥ በቻሉት መጠን የራስዎን ለውጥ እንጅ እርስዎን ከሌሎች ጋር አያነጻጽሩ።

ምክንያቱም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በእጅዎ ያለውንና የእርስዎን መልካም አጋጣሚ የሚዘነጉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላልና።

ምንጭ፦ psychologytoday.

Advertisement