ከራስ ጋር ማውራት የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች…

                                                         

አንዳንድ ጊዜ ድምጻችንን አሰምተንም ይሁን ያለ ድምጽ ከራሳችን ጋር የማውራት ባህሪዎች ይስተዋሉብናል።
ከእነዚህም ውስጥ ስልኬን አሊያም ቁልፌን የት አደረኩት ከሚሉት ጥያቄዎች ጀምሮ በውድቅ ሌሊት ላይ አጠገባችን ሰው ሳይኖር በማውራት ለራሳችን መልስ መስጠት ይገኝበታል።
ታዲያ ከራስ ጋር የሚደረግ ንግግር ጤናማ ነው የተባለ ሲሆን፤ አእምሯችን ጤናማ እና ብቁ እንዲሆን ያለው አስተዋጽኦም ከፍተኛ መሆኑ ነው የሚነገርለት።
ከራስ ጋር ማውራት ንግግራችንን ለመቆጣጠር እና ለማስተካከል፣ ለምንሰራቸው ስራዎች እቅድ ለማውጣት፣ የማስታወስ አቅማችንን ለመጨመር እና ስሜታችንን ለመቆጣጠር ይረዳናል፤ ይህ ማለትም በአጠቃላይ ራሳችንን ለመቆጣጣር ይጠቅማል ማለት ነው።
ከራሳችን ጋር ማውራት በሁለት የሚከፈል ሲሆን፥ አንደኛው ድምጽ ሳናሰማ በውስጣችን የምናደርገው ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ ድምጽ አሰምተን ከራሳችን ጋር የምናወራው ነው ተብሏል።
ከእነዚህ ውስጥ ድምጽን ከፍ አድርጎ ማውራት ድምጽ ሳናሰማ በውስጣችን የምናደርገው ውይይት መስፋፋት ነው፤ ይህ ደግሞ ሳይታወቀን የሚከሰት መሆኑም ይነገራል።
ሆኖም ግን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ከራሳችን ጋር መነጋገርን አንዳንዶች ከአእምሮ ችግር ጋር ሲያያይዙት በብዛት ይስተዋላል።
እነሱ እንደዛ ያስቡ እንጂ እውነታው ግን ይህ አይደለም፤ ከራስ ጋር ማውራት አእምሯችን በሳል እንዲሆን እና የምናደርጋቸው ነገሮች ላይ ከራሳችን ጋር በመመካካር ውጤታማ እንድንሆን ያደርጋል ነው የተባለው።
ስለዚህም ሰዎች ከራሳቸው ጋር በሚያወሩበት ጊዜ የአእምሯቸው አቅም እንዲጨምር እድል ስለሚከፍቱ፤ እንዲህ አይነት ልማድ ካላቸው መልካም ልምድ መሆኑ ነው የሚነገረው።
ከዚህ በተጨማሪም ከራስ ጋር ማውራት ሀሳብ የሆኑብንን ነገሮች ለማቅለል እና መፍትሄ ለመስጠት የሚረዳን ሲሆን፥ እንደ ጭንቀት እና ድብርት ያሉ ችግሮችንም ለመፍታት ጠቀሜታው የጎላ ነው ተብሏል።
ምንጭ፦ http://edition.cnn.com

Advertisement