ቲማቲም መመገብ የሆድ ካንሰርን ይከላከላል – Eating Tomatoes Can Prevent Stomach Cancer.

                                       

ቲማቲም መመገብ የካንሰር ህዋሳት እድገትን ለማቆም እንደሚረዳ አንድ ጥናት አመለከተ።

ይህን ተወዳጅ ፍራፍሬ እስከነ ልጣጩ ሙሉውን መመገብ የሆድ ውስጥ ካንሰርን በመከላከሉ ረገድ ሚናው ላቅ ያለ መሆኑ ተሰምቷል።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች በቲማቲም እና ሌሎች ቀይ ቀለም ያላቸው ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች ውስጥ የሚገኘው ላይኮፒን የተሰኘ ኬሚካል ካንሰርን የመዋጋት አቅም እንዳለው ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

አዲሱ በጣሊያን ሜርኮግሊያኖ የካንሰር ጥናት ማዕከል የተደረገው ጥናት ደግሞ የቲማቲም ካንሰርን የመከላከል ብቃት ከላይኮፒን ኬሚካል ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም ብሏል።

የጥናቱ ፀሃፊ ዳንኤል ባሮን እንደሚሉት፥ ቲማቲምን እስከነ ልጣጩ ቀቅለንም ሆነ ጥሬውን መመገብ የካንሰር ህዋሳት እንዳይስፋፉ እና እንዳያድጉ ከማድረጉም በላይ እንደሚገድላቸው በጥናቱ ተረጋግጧል።

በጥናቱ የተሳተፉት ፕሬፌሰር አንቶኒዮ ጂርዳኖ በበኩላቸው፥ የጥናቱ ግኝት ተጨማሪ የሆድ ካንሰር መከላከያ መንገዶችን ለመፈለግ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ጥናቱ ቲማቲም በሽታውን ለመከላከል የሚያበረክተውን ሚና ከመጠቆሙ ባሻገር በቀጣይ አዲስ የበሽታው ማከሚያ ዘዴን ለመፈለግ መንገድ ይጠርጋል ተብሏል።

ይህ ጥናት በሴሉላር ሳይኮሎጂ ጆርናል ላይ ታትሞ ወጥቷል።

የሆድ ካንሰር ወይንም የጨጓራ ካንሰር በአለማችን ብዙም የተለመደ በሽታ አይደለም።

ይሁን እንጂ በብሪታንያ በየአመቱ 7 ሺህ ሰዎች በበሽታው ይጠቃሉ።

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk/

Advertisement