ባህልን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቀመመው ሮፍናን

እናቱ እንዝርት እያሾሩ ጥጥ ሲፈትሉ በተመስጦ የሚያስተውለው ታዳጊ ስለ ፈትል ክምሩ ይጠይቃል።

“እማ እሱን ምን ልታደርጊው ነው?”

“ዶርዜው ይመጣል፤ እሱ ሲመጣ ምን እንደሚደረግ ታያለህ” ከእናቱ የሚያገኘው ምላሽ ነው።

ዶርዜው ሰአቱን ጠብቆ ይደርስና ፈትሉን ይረከባል።

እጀኛው ሸማኔ ከቀናት በኃላ ከፈትሉ ውብ ጥብበ ልብስ አምርቶ ያስረክባል። ቀሚስ፣ ነጠላ ወይም ጋቢ በማራኪ ጥለት አሰውቦ።

ታዳጊው የፈትሉን ታሪክ በወጣትነቱም አልዘነጋውም። የሸማኔውን ታሪክ በዜማ አቀናብሮ ለአድማጭ እነሆ ብሏል።

“ዶርዜ ዶርዜ ዶርዜ

ያብዛው ሰላሙን ለአገሬ ሰው

ፈትሉን ከቀለም ለሚያረቀው

የእናቴን ቀስም በአሞቂያው ከቶ

እናና አማረባት ዶርዜው ሸምኖት”

ሮፍናን ኑሪ ይባላል። ሙዚቃ አቀናባሪ፣ ዲጄ፣ ድምጻዊም ነው። ዲጄ ሮፊ በሚለው የመድረክ ስሙ ይታወቃል።

ከሳምንታት በፊት “ነጸብራቅ” የተሰኘ አልበም አውጥቷል።

በአልበሙ ስምንተኛ ሙዚቃ “ጋሞ ዳሬ” የልጅነት ትውስታውን በግጥምና ዜማ ከሽኗል።

እናቱ እጅግ ለሚወዱት ሰው ስጦታቸው ጥበብ ነጠላ፣ ጋቢ ወይም ቀሚስ ነው። ሮፍናን የልጅነት ትውስታውን አንግቦ ወደ ደቡብ ክልል አቀናና ከጥበቡ ባለቤቶች ጋር ተገናኘ።

ከሸማ አሻግሮ ስለ ሙዚቃቸውም አጠና። “የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው። ከነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እድለኛነት ነው” ሲል ወቅቱን ያስታውሳል።

• ”አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው”

• የሙዚቃ ሕክምና በኢትዮጵያ

ከደቡብ በተጨማሪ በተቀሩትም የኢትዩጵያ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ሀገርኛ ሙዚቃን ካሰሰ በኃላ ከባህር ማዶው ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ጋር ቀይጦ አልበሙን ጠነሰሰ።

ከስድስት ዓመት ስራ በኃላ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አልበሙ ገበያ ላይ ውሏል። መጠሪያው “ነጸብራቅ” የተባለው ያለምክንያት ሳይሆን ሙዚቃዎቹ የህይወት ተሞክሮው ድምር ውጤት መሆናቸውን ለማሳየት እንደሆነ ይናገራል።

በሙዚቃዎቹ ቱባ ባህልና የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ምት ተሳስረዋል። “ጋሞ ዳሬ” ብቻ ሳይሆን በአልበሙ የተካተቱ ሌሎች 15 ሙዚቃዎችም የሀገርኛ ዜማና ምቱ የፈጠነው የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ውህድ ናቸው።

“የአስተዳደጌ የትውልዴና የማህበረሰቤ ነጸብራቅ ነው”

ሮፍናን በአስራዎቹ እድሜ ክልል ሳለ መማሪያ ጠረጴዛ እንደ ከበሮ እየመታ ሙዚቃ ለመፍጠር ይሞክር ነበር።

ወደ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪነት ሲሸጋገር ኮምፒውተሩ ላይ መተግበሪያዎች በመጫን ተሰጥኦውን ማሳደግ ያዘ። አስከትሎም በአዲስ አበባ የምሽት መዝናኛዎች ዲጄ ወደማድረግ ዘለቀ።

ዲጄነትን ሙዚቃ ከማቀናበር ጋር አያይዞ መቀጠሉን “ራሴን ያሳደኩበት ወቅት” ሲል ይገልጸዋል።

ሮፍናን ሙዚቃውን የሚገልጸው “የአስተዳደጌ፣ የትውልዴና የማህበረሰቤ ነጸብራቅ” ሲል ነው። የሙዚቃው መሰረት የሚያስተውላቸው የአካባቢው እውነታዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ቅኝቶች ትዝታ፣ ባቲ፣ አንቺ ሆዬ፣ አምባሰል የማህበረሰቡ መገለጫ ናቸው። ያለንበት ዘመን ደግሞ የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን አቅርቦለታል።

ከሙዚቃዎቹ መካከል የተለያዩ ማህበረሰቦች መገለጫዎች የታከሉባቸው ይጠቀሳሉ። ጉራግኛ ምት ያለው “ጌት ቱ ወርክ” ከማህበረሰቡ የሥራ ባህል የተቀዳ፣ ኦሮምኛው “ቀነኒሴ” በፈረስ ኮቴ ድምጽ የታጀበ ነው።

ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን የኔ ዘመን ሙዚቃ ይለዋልImage copyrightROPHNAN
አጭር የምስል መግለጫኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን የኔ ዘመን ሙዚቃ ይለዋል

በሙዚቃዎቹ በሀገርኛና በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ መካከል ድልድይ ፈጥሮ እኛ የውጪውን የተቀረው ዓለም ደግሞ የኛን ሙዚቃ እንዲገነዘብ እንደሚያደርግ ያምናል።

“የኛ ሙዚቃ በተቀረው ዓለም ቅኝት ጭምርም ሲቀርብ ይደመጣል” ይላል።

በዚህ ዘመን ተወዳጅነትና ተቀባይነት ካገኙ የሙዚቃ ስልቶች አንዱ የሆነውን ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን የመረጠው እሱ የሚካተትበት ትውልድ የሚገለጽበት ዘዬ በመሆኑ ነው። “የሙዚቃዬ ነጸብራቅነት ለትውልዱም ነው” የሚለውም ለዚሁ ነው።

ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ለሀገሬው ጆሮ እንግዳ?

በትዊተር፣ ፌስቡክና ሌሎችም ማህበራዊ ሚዲያዎች የሮፍናንን ሙዚቃዎችና የአልበሙን የሽፋን ምስልም ብዙዎች ሲጋሩት ተስተውሏል። እሱም በጎ ምላሽ እያገኘ መሆኑን ይናገራል።

የዛሬው ‘የመረጃ ዘመን ልጆች’ ስለተለያዩ ሀገራት ለማወቅ መጓጓታቸው የሮፍናን አይነት ሙዚቀኞችን እሰየው አስብሏል።

ሮፍናን “የኔ ዘመን ሙዚቃ” ይለዋል ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን። በየዘመኑ ገናና የሆኑ የሙዚቃ ስልቶች አሉ። ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ቀለም ነው። ስልቱ በተይም በምዕራቡ ዓለም ታዋቂ ነው። ኢትዮጵያዊ መልክ መስጠት ግን ጅማሮ ላይ ይገኛል።

በእርግጥ ሙዚቃ ተወራራሽ ነው። ድንበር አይወስነውም። ቢሆንም የከሚሴን እንጉርጉሮ ከፈጣኑ (ሀይ ቴምፖ) ሙዚቃ ማዳቀል ልዩ ስልት ያሻዋል።

ኃይሉ መርጊያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃ ይጫወት በነበረበት ወቅት የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። አሁን በአሜሪካ እየኖረም ቢሆን ግን ሙዚቃ ማቀናበሩን አልተውም።

ሙዚቀኛው “የዶርዜ አካባቢ የህብረት ዜማ፣ የሸዋ ፎሌ፣ የሰላሌ ረገዳን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ማቅለም ሙዚቃዊ ምርምር ነው” ይላል።

በአንድ የኢትዮጵያ ገጠር ኮረብታ ላይ ዋሽንት ሲነፋና በቅንጡ ምዕራባዊ ስቱዲዮ ሙዚቃ ሲቀመር ያለው ውህድ የዩሀንስ አፈወርቅን ዋሽንት ከስኪሪሊክስ ቅንብር ጋር ማገናኘት እንደማለት ነው።

ሁለቱን የሙዚቃ ስልቶች የሚገናኙበት ነጥብ እንዳለ የሚናገረው ሙዚቀኛው “ስሌቱን ማግኘት ሙዚቃው በአድማጭ እንዲወደድ ያስችላል” ይላል።

ሙዚቃው ለሀገሬውም ለውጪውም አድማጭ ጆሮ ባዳ እንዳይሆን የማድረግ ሂደት መሆኑንም ያክላል።

ሀገር ውስጥ የተካሄዱ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ስልቱን በማስተዋወቅ ረገድ ይጠቀሳሉ። አዲስ አበባ የተካሄደው “ቢራቢሮ” ኮንሰርት እንዲሁም አርባ ምንጭ የተካሄደውም ይገኙበታል።

“ሙዚቃውን ለማስለመድ ግዜ ቢወስድም ከምናውቀው ባህል ጋር መደባለቁ እንዲወደድ ያግዛል” ሲል ያስረዳል።

ሙዚቃው በከተሜው ዘንድ ብቻ የሚደመጥ ወይስ መነሻው ያደረገውንም ማህበረሰብ ያማከለ ብለን ስንጠይቀውም “የሙዚቃውን መሰረታዊ ይዘት ስላልቀየርኩት የሰራሁት ሙዚቃው ለወጣበት ማህበረሰብም ጭምር ነው” ይላል።

ሙዚቃው የተጠነሰሰባቸው አካባቢዎች አልበሙ ባለመድረሱ ምላሹን ለመለካት ገና ቢሆንም ተደማጭነት እንደሚያገኝ ተስፋ ያደርጋል።

ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ እንደሱ በሃያዎቹ እድሜ ገደማ ያሉ ወጣቶች ሙዚቃ ቢሆንም በየትኛውም እድሜ ያለ እንዲያደምጠው በማሰብ አልበሙን ማዘጋጀቱን ያስረዳል።

እሱ እንደሚለው “ስልቱ ‘የወጣቱ’ ቢባልም ሙዚቃው በሁሉም እድሜ ክልል እንዲደመጥ ባህላዊ መሰረቱ ያግዘዋል። እንዲያውም የእድሜ ክፍተቱን ያጠባል።”

ሮፍናን ከሌሎች ስልቶች በላቀ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ለምርምር ይመቸዋልImage copyrightROPHNAN
አጭር የምስል መግለጫሮፍናን ከሌሎች ስልቶች በላቀ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ለምርምር ይመቸዋል

ሙዚቃውን ወደ ለም መድረክ

ሮፍናን ከሌሎች ስልቶች በላቀ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ለምርምር ይመቸዋል። አንዱን ሙዚቃ ከሌላው ይቀይጥበታል። ኢትዮጵያ ባህል የተቸረች መሆኗ ለሙዚቀኞችም የተመቸ ነው።

ሆኖም አብዛኛው ባህላዊ ሙዚቃ በአግባቡ እንዳልተጠናና ገኖ እንዳልወጣም ሙዚቃኞች ይስማሙበታል።

በእሱ እይታ የባህል ሙዚቃን ፈትሾ ማውጣት “ሙዚቃችን እኛን ወክሎ እንዲሰማ ማድረግ” ነው። ሙዚቃውን ለተቀረው ዓለም ማስተዋወቅም ይሻል።

ኢትዮ-ጃዝን በምሳሌትነት በማንሳት ኢትዮ-ኤሌክትሮኒክ የተሰኘ ስልት ይፈጠር ይሆን? ብሎ መጠየቅ አይቀርም።

ሮፍናን ከተሳተፈባቸው ተጠቃሽ ዓለም አቀፍ መድረኮች መካከል ‘አክስ ኢቢዛ’ ይገኝበታል። ከአህጉረ አፍሪካ ከተውጣጡ የኤሌክትሮኒክ ሙዚቀኞች አንዱ ሆኖ ሥራዎቹን አቅርቧል። “ጨረቃን” የተሰኘው ሙዚቃው የአፍሪካ ሕብረት የወጣቶች ክንፍ ብሔራዊ መዝሙር ሆኗል።

ሉላዊነት የሙዚቃውን ስርጭት የበለጠ እንደሚያሰፋውም ተስፋ ያደርጋል።

“ዓለም ላይ አዲሱ ሙዚቀኛ ዲጄ ነው” የሚለው ሮፍናን ዘመኑ እንደሱ ሙዚቃ ማቀናበርና ዲጄ ማድረግን ላጣመሩ እንደሚሆን ያስረዳል።

ሁሌም ሙዚቀኛ ሲባል ቦታ የሚሰጠውም ለድምጻዊ ብቻ መሆኑን የሚተቸው ሮፍናን፤ ሙዚቃ ማቀናበር፣ ዲጄነትና ማቀንቀንን በማጣመሩ መጪውን ዘመን ተስፋ ጥሎበታል። አልበሙ ለዚህ ማሳያ እንደሚሆንም ይናገራል።

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.