The Leader of Change PM Abiy in World Media Coverage | የለውጥ መሪው ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ-በዓለም አቀፉ ዘ ኢኮኖሚስት መፅሄት እይታ

በቢኒያም መስፍን

የለውጥ መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በዓለም አቀፉ ዘ ኢኮኖሚስት መፅሄት እይታ የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ በተሰኘው አምዱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን በተመለከተ እና በአጭር ጊዜያት ውስጥ ስላከናወኗቸው ተግባራት ሰፋ ያለ ትንታኔ ይዞ ወጥቷል፡፡

እንደ መጽሄቱ ትንታኔ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከወራት በፊት ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መጥተዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት እና ህዝባዊ ተቃውሞች እንዲሁም ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሰፈነበት ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ በመያዛቸው በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ እንዳልታመነ ዘ ኢኮኖሚኒስት አትቷል፡፡

ሆኖም በሹመት በአላቸው ለሀገራዊ አንድነት ጥሪ ማቅረባቸው እና በተቃውሞ ሰልፍ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችን አስመልክቶ ይቅርታ መጠየቃቸው ግርምትና አድናቆትን አጭሯል፡፡
በቀጣይም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ብዙ ህዝብ በተገኘባቸው መድረኮች የትውውቅ ንግግሮችን እና ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡ ከህዝቡ ጋር በአንድነት ለመስራት እንደሚፈልጉም ገልፀው ነበር ይላል የዘኢኮኖሚስት ትንታኔ፡፡
በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከሀገር የተባረሩ ተቃዋሚዎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ እና በውጪ ሀገራት የሚገኙ እና በተቃዋሚነት የተፈረጁ መገናኛ ብዙኃን በአዲስ አበባ ማዕከላቸውን እንዲከፍቱ ጥሪ ቀርቧል፡፡

አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሌሎች አያሌ የፖለቲካ እስረኞች ክሳቸው ተቋርጦ በነፃ ተለቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገ-መንግስቱን በማሻሻል የስልጣን ዘመንን ገደብ ለማበጀት ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ካቢኔያቸው በወሰነው መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ተነስቷል፡፡ በድንበር ውዝግብ ከኤርትራ ጋር ተፈጥሮ የቆየውን ውጥረት ለመፍታት እና ኢትዮጵያን የወደብ ተጠቃሚ ለማድረግ የአልጀርሱን ስምምነት እንደሚቀበል ካቢኔያቸው ይፋ ማድረጉን ዘኢኮኖሚስት አስፍሯል፡፡

የአልጀርሱ ውሳኔ በብዙ ዜጎች ዘንድ ጥርጣሬ እና ተቃውሞ ማስነሳቱንም ጠቅሷል፡፡ በስራ ተወጥረው የቆዩት ዶ/ር አብይ ችግር ላይ ለወደቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብዙም ትኩረት የሰጡት አይመስልም ነበር ይላል ዘገባው፡፡
ሆኖም በመንግስት ሙሉ ቁጥጥር ስር የቆዩ ቁልፍ የመሰረተ ልማት ፣ ባንክ፣ ባቡር፣ ቴሌኮም፣ እና የበረራ ዘርፎችን ለግሉ ዘርፍ በሙሉ እና በከፊል በማዘዋወር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያጠናክሩ መናገራቸው ለኢኮኖሚው ዘርፍ ትኩረት መስጠታቸውን ያሳያል፡፡

ከጥቂት ወራ በፊት ሚኒስትሩ ከባለ ሀብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ዘርፎች ከመንግስት እጅ እንደማይወጡ በመግለጻቸዉ የአሁኑ ውሳኔ ግርምትን ፈጥሯል ብሎም ኢኮኖሚክ ሊብራል ወይም የነፃ ኢኮኖሚ ርዬተ-ዓለም ተከታይ ናቸው የሚል እምነትን አሳድሯል ይላል የዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ፡፡
ዘኢኮኖሚስት በትንታኔው እንዳሰፈረዉ መንግስት አነዚህን ውሳኔዎች ያሳለፈው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አንጻራዊ በሆነ መልኩ መዳከም በማሳየቱ ነው፡፡ ባለፉት አስር አመታት የሀገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ እድገት በአማካኝ 10 በመቶ የነበረ ሲሆን በያዝነው አመት ከ2 በመቶ በላይ ቅናሽ እንደሚኖረው የዓለም የገንዘብ ድርጅትን (IMF) ዋቢ አድርጎ ትንታኔውን አስቀምጧል፡፡

የውጪ ምንዛሬ እጥረት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ መጉዳቱን እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሶ በዚህ ሳቢያ የዋጋ ውድነቱ በ 15 በመቶ ማሻቀቡን ጠቁሟል፡፡

መንግስት ያሳለፋቸዉ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ለኢኮኖሚያዊ ለውጥ ትኩረት መስጠቱን አመላካች ቢሆኑም ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በጥልቅ ካልተሰራ የባለቤትነት ለውጥ ብቻ እንደሚሆን እና ለሙስና የተጋለጠ አሰራርን ሊፈጥር እንደሚችል የኢኮኖሚ ምሁራንን ጠቅሶ ዘኢኮኖሚስት አስፍሯል፡፡

ይሁንና ጠ/ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸዉ ከወራት በፊት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በአልጀርሱ ስምምነት እና በተወሰኑት ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ዙሪያ ዉይይት ሲያካሂድ መቆየቱን ብሎም ዉሳኔዉ ቀደም ብሎ የታሰበ እንደነበር አንድ ኢትዮጵያዊ ተንታኝ መግለጹን አስፍሮ ትንታኔዉን ደምድሟል፡፡

ምንጭ:  Amhara Mass Media Agency

 

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.