ከአምሳ ሁለት ዓመታት በፊት ኒውዮርክ ባለች በትንሽ ስቱዲዮ ውስጥ የተፈጠረው ኢትዮ-ጃዝ ከአይፎን 8 ማስተዋወቂያነት በጀርመን ውስጥ እስካለ መንደር ስያሜ ሊሆን ችሏል።
የሰሩት ሙዚቃ ለአይፎን 8 ማስተዋወቂያ ከመሆን ጋር ተያይዞም የተወሳሰቡ ጉዳዮች እንዳሉና ከእሳቸው ፈቃድ ውጭ ሙዚቃው እንደተሰጡ የሚናገሩት ሙላቱ ከወኪሎቻቸው ጋር በድርድር ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ ቢሆንም ለአይፎን 8 ማስተዋወቂያነት መብቃቱ ኢትዮ-ጃዝ የፈጠረውን ተፅዕኖ ማሳያ ነው የሚሉት አቶ ሙላቱ “ለሙላቱ ወይም ለኢትዮ-ጃዝ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ትልቅ ነገር ነው” በማለት ይናገራሉ።
በመላው ዓለም ተደማጭነትን ማግኘት የቻለው ኢትዮ-ጃዝ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያደረገው ትግሉ ግን ቀላል አልነበረም ይላሉ አቶ ሙላቱ።
የሙላቱ ስኬቶች
በተለያዩ ትላልቅ መድረኮችም ላይ የመታየት እድልን አግኝቷል። ከነዚህም መካከል የኢትዮ-ጃዝ ውጤት የሆነው የሙዚቃ ሥራ ለኦስካር ሽልማት ታጭቶ ለነበረው “ብሮክን ፍላወርስ” ለተሰኘው ፊልም ማጀቢያነት ውሎ ነበር።
በተጨማሪም በሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ታላቅ ስፍራ ያላቸው አሜሪካዊው ናስና የሬጌ ሙዚቃ ተጫዋቹ ዴሚየን ማርሌይ “የግሌ ትዝታን” ”ዲስታንት ሪላቲቭስ” በሚለው አልበማቸው ውስጥ አካትተውታል።
ሙላቱ አስታጥቄ በሙዚቃ ትምህርት ታላቅ በሚባለው በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትም ያገኙ የመጀመaሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ናቸው።
“በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ለጃዝ ሙዚቃ ታላቅ ዩኒቨርሲቲ ነው። በዚህ ዩኒቨርሲቲም ተቀባይነትንና ዕውቅናን ማግኘት ክብር ነው። በጃዝ ውስጥ ከፍተኛ ስም ካላቸው እንደነ ዱክ ኤሊንግተን፣ ኩዊንሲ ጆንስ፣ አሪታ ፍራንክሊን ያገኙትን አንድ አፍሪካዊ ማግኘት ትልቅ እውቅና ነው” ይላል ሙላቱ።
በቅርቡም ጃፓን ውስጥ በተደረገው የፉጂስ ኮንሰርት ላይ ከ120 ሺህ ሰዎች በላይ በተገኙበት ሥራቸውን ያቀረቡ ሲሆን ስኮትላንድ በሚገኘው ታላቁ ፌስቲቫል ግላስተንቤሪ ከ140 ሺህ ሰዎች በላይ በታደሙበት መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በጀርመን ሀገር በፖፕ ሲቲ በኢትዮ-ጃዝና በሙላቱ አስታጥቄ ስም መንደር ተሰይሟል። ከእሳቸው ሌላም ለሙዚቃ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ለሚባሉት ለእነ ኤልቪስ ፕሪስሊ፣ ማይክል ጃክሰን እንዲሁም ማሪያ ማኬባም ዕድሉ ደርሷቸዋል።
እነዚህ ሁሉ የኢትዮ-ጃዝ ትሩፋት ናቸው የሚሉት ሙላቱ፤ ከዚህም በተጨማሪ የዘመናዊው ጃዝ ፈጣሪ በሆነው ቻርሊ ፓርከር ስም በየዓመቱ ኒውዮርክ ውስጥ በሚካሄድ ፌስቲቫል ላይ መጫወታቸው ለኢትዮ-ጃዝ ያገኘውን ትልቅ ክብር ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ።
“ይሄ ሁሉ ለኢትዮ-ጃዝ ትልቅ ዕውቅና ነው፤ ሁልጊዜም እምፈልገውና የማልመው ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። የትም ቦታ ብሄድ ያለው የህዝቡ ፍላጎትና ፍቅርም ትልቅ ነው” ይላሉ።
ጥናቶችና አዳዲስ ሥራዎች
ሁልጊዜም ቢሆን አዳዲስ ሥራዎችን ከመፍጠር አላቆምም የሚሉት ሙላቱ፤ በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያዊው የዜማ ቀማሪ በቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ላይ የኦፔራ እያዘጋጁ ነው።
ይህ ሥራ ኢትዮጵያ በባህል ዘርፍ ለዓለም ያበረከተችውን አስተዋፅኦ የሚዘክር ነው። በዚህም ጥናት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በምትጠቀመው መቋሚያ ላይም ምርምሮችን አድርገዋል።
ይህንን ምርምራቸውን እያካሄዱ ያሉት በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ስር ነው።
“ሙዚቃን መምራት ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው አስተዋፅኦ ነው” (ኮንደክቲንግ ኢዝ ኢትዮፕያን ኮንትሪቦዩሽን ቱ ዘ ወርልድ) በሚል ርዕስ የጥናት ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ኢትዮጵያ ከሌሎች ቀድማ መቋሚያን በመጠቀም ሙዚቃን መምራት እንዳስተማረች ይዘረዝራል።
መቋሚያን ብቻ ሳይሆን ፀናፅሉን፣ ከበሮውን በአጠቃላይ ንዋየ-ማህሌት ተብሎ የሚጠራውን ሥርዓት እንዳጠኑም ይናገራሉ። “ይህ ክላሲካል ሙዚቃ ተብሎ ለሚጠራው የሙዚቃ ሳይንስ መሰረት ነው፤ ይህም ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችውን ያሳያል እላለሁ” ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የፈጠሩትንና “የሙዚቃ ሳይንቲስቶች” ብለው በሚጠሯቸው እንደነ ደራሼ ባሉት ህዝቦች ሙዚቃም ላይ ምርምር እያደረጉም ነው።
“በታሪክ ስናጠናው እነዚህ ሕዝቦች ለበርካታ የአውሮፓውያን የሙዚቃ መሳሪያዎች መሰረቶች ናቸው። ትራምፔትንና ትሮምቦንን የሚመስሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የቤኒንሻንጉል የሙዚቃ መሳሪያ የሆነው ዙምባራ ነው” ይላሉ።
ሸራተን አዲስ ተደርጎ በነበረው የሙላቱ የሙዚቃ ኮንሰርትም ላይ ሙዚቀኞቹንና እነዚህን የሙዚቃ መሳሪያዎች አካተዋል። በብዙ አጋጣሚዎች ስለደራሼ ህዝብ ሙዚቃ ጥልቀትም ሆነ ጥበብ አውርተው የማይጠግቡት ሙላቱ የደራሼ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ ቅኝት ውጭ የሆነ ሙዚቃ ነው በማለት ይናገራሉ።
ከአውሮፓውያኑ በላይ እንደ ደራሼ ላሉ አገር በቀል ሙዚቃዎች ክብርም ሆነ ዕውቅና መስጠት ይገባል ብለው የሚያምኑት ሙላቱ፤ “ምንም እንኳን ለቀረው ዓለም የጃዝ ሙዚቃ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራዎቻቸው ላይ ጥናትና ምርምር የለም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ሊቀየር ይገባል” ይላሉ።
ኢትዮ-ጃዝ እንዴት ተፈጠረ?
ሙዚቃን በበርክሌይ ያጠኑት ሙላቱ “ወደራስ መመልከት ወይም ማየት” ለሚለው መነሻቸውም የሆነው በዚሁ ትምህርት ቤት የሙዚቃ መምህር በነበረ ሰው አማካኝነት እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህ መምህር “ራሳችሁን ሁኑ” የሚል ምክርም በተደጋጋሚ ለግሷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ከትምህርት ቤት ወጥተውም ኒውዮርክ በሚኖሩበት ወቅት ስለኢትዮጵያ መመራመራቸውን ቀጠሉ።
“እነዚህ ቅኝቶች ላይ ተመስርቼ ቀለምና መልካቸውን ሳይቀይር ከአውሮፓውያኑ አስራ ሁለት ድምፆች ጋር እንዴት አዋህጄ አዲስ ድምፅ መፍጠር እንደምችል እየተመራመርኩ ነበር” ይላሉ ሙላቱ።
ከብዙ ጥናትና ምርምር በኋላም የሁለቱ ጥምረት ኢትዮ-ጃዝን መፍጠር ቻለ። ይህንንም ጥምረት ሙላቱ ”የቅኝቶች ፍንዳታ” (ኢምፕሮቫይዜሽንን) ይሉታል።
ወደ ኢትዮጵያም ሲመለሱ ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ አልነበረም።
ከሚያስታውሱትም አንዱ የፀጋየ ገብረ-መድህን ቲያትር ድርሰት ለሆነው ‘ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት’ ሙዚቃ በገናን፣ ፒያኖን፣ጊታርና ሌሎች ሙዚቃ መሳሪያዎችን በመጠቀም ቅንብሩን ሰሩ።
በዚያን ወቅት የጥላሁን ገሰሰ “ኩሉን ማን ኳለሽ” በጣም ታዋቂ ዘፈን የነበረ ሲሆን ይህንን ሙዚቃ እንዲጠቀሙ ብዙዎች ቢፈልጉም የራሴን ቅንብር ነው የምጫወተው በማለት ሙላቱ በሀሳባቸው እንደፀኑ ይናገራሉ።
በአምባሳደር ቲያትር ቤት ዝግጅታቸውን አቀረቡ። “መቼም ቢሆን አልረሳውም፤ ሙዚቃውም ከበገና ወደሌሎች ሙዚቃ መሳሪያዎች ሲሄድ ብዙዎች ውረድ አሉኝ። ውረድ የሚለው ድምፅ ቢበረታም ሳልጨርስ አልወረድኩም” የሚሉት ሙላቱ “ሁልጊዜም ቢሆን የምናገረው ያን ጊዜ ተስፋ ቆርጨ ሙዚቃ ማቆም እችል ነበር፤ መታገልን የመሰለ ነገር የለም። እንዲያውም እሱ የበለጠ ብርታትና እልህ ሰጥቶኛል። ‘ተስፋ አትቁረጡ ሁልጊዜም ታገሉ፤ አዲስ ነገር ፍጠሩ’ በማለት እመክራለሁ” ይላሉ።
ከዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮ-ጃዝ ታዋቂነትን እያገኘና ተከታዮችን እያፈራ ቢመጣም አሁንም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያለው በአውሮፓና በሌሎች ሀገራት እንደሆነ ሙላቱ ይናገራሉ።
ስለአዝማሪዎች
ኢትዮ-ጃዝ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደሆነ የሚናገሩት ሙላቱ በዓመታት ውስጥ ብዙ የምርምር ሥራዎች እንደተጨመረበት ይናገራሉ።
“አሁን ደግሞ ዋናው የኢትዮ-ጃዝ አላማ የሙዚቃ ሳይንቲስቶቻችንና ፈጣሪዎቻችን ላይ ተመስርተን፤ ያሉን መሳሪያዎች መልካቸውና ዲዛይናቸው ሳይቀይር እንዴት አድርጎ የሌላውን ዓለም ሙዚቃ መጫወት ይችላል የሚል ነው” ይላሉ።
”አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው” የሚሉት ሙላቱ፤ ያሉትን የኢትዮጵያ ሙዚቃ መሳሪያዎችንና ሙዚቃን ፈጥረው እዚህ ካደረሱ ቀጣዩ ትውልድ ደግሞ ሊያሻሽለው እንደሚገባ ይናገራሉ።
ሥራዎቻቸው መካከልም አዝማሪን ወደ 21ኛው ክፍለ-ዘመን ማምጣት በሚል በክራር ላይ የሰሩት ይገኝበታል። “እነዚህ ሥራዎች ቀላል አይደሉም። ማድመጥና መውደድን የሚፈልጉ ሰዎችን ይጠይቃል። በግለሰብ ደረጃ ብቻ የሚሰራ አይደለም” ይላሉ ሙላቱ።
ከምርምርና ከሙዚቃ ሥራው በተጨማሪ አፍሪካን ጃዝ ቪሌጅ (የአፍሪካ ጃዝ መንደር) የሚባል የሙዚቃ ትምህርት ቤት፣ የሬድዮ ፕሮግራም የነበራቸው ሲሆኑ ለሀርቫርድ ጥናት በሄዱበት ወቅት ተቋረጦ የነበረ ቢሆንም የሬድዮ ፕሮግራሙ አሁን ወደ አየር ተመልሷል።
ምንጭ:- ቢቢሲ