ሩዋንዳን በጨረፍታ – Rwanda at a Glance

                                               

By (Aweke Abreham)

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፍ ቦይንግ አውሮፕላን ወርጄ አነስተኛዋን የኪጋሊ አየር ማረፍያ እግሬ ሲረግጥ ስለ ሩዋንዳ ያለኝ ምስል እንደነበረ ነው። ለአመታት ስለ ሃገሪቱ ከሰማሁት ካነበብኩትና በፊልም ካየሁት ተጠራቅሞ የተሰራው ምስል። እ.አ.አ በ1994 በቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ላይ ከተካሄደው ዘር ማጥፋት ጋር የተያያዘ አሉታዊ የሆነ ምስል ።  ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 84 በመቶውን ከሚይዙት ሁቱ ወገን የነበሩት የሀገሪቱ መሪ ጁቬኒል ሀቢያሪማና እና ሁቱው የቡሩንዲው ፕሬዚዳንት ሳይፕርዬን ንታርያሚራ የሚበሩበት አውሮፕላን ኪጋሊ አቅራቢያ ተመትቶ ከተገደሉ በኋላ ለአመታት በአክራሪ ሁቱዎች ሲጠበቅ የኖረው የሞት ቀጠሮ ደረሰ። የሁቱ ኢንተርሃምዌ ሚሊሻዎች አናሳዎቹ ቱትሲዎች ላይ በከፈቱት የዘር ማጥፋት ዘመቻ እስከ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሩዋንዳዊያን ካለቁ በኋላ የሩዋንዳ መታወቂያ ሆቴል ሩዋንዳ በሚለውፊልምላይ እንዳሉ ዘግናኝ ትዕይንቶች አስፈሪ ነው። ይህን ምስል በአዕምሮዬ እንደታተመ ነው እንግዲህ ኪጋሊ የገባሁት።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ባደረገባቸው ቡታሬ እና ኪጋሊ ከተሞች ላይ በድምሩ አስራ አራት ቀናት ስቆይ እኔም የስራ ባልደረቦቼ የተገረምነው በህዝቡ ስርዓት እና ትህትና ነው። እንዲህ አይነት ትሁት ህዝብ እንዴት በገጀራ ለመተራረድ በቃ? የለሚው መልስ የማይገኝለት ጥያቄ ነው።ትህትናቸው ልዩ ነው።ቅንነታቸው ያስቀናል። ሩዋንዳዊያን ሃያ አመት ስላለፈው እልቂት ሲያስታውሱ ፊታቸው ላይ ሃዘን ይነበባል።በተቀረው ዓለም የሃገራቸው መታወቂያ መሆኑም ያማቸዋል። ትናንት የጨፈጨፉትም የተጨፈጨፉትም ወገኖች ዛሬ ይቅር ተባብለው በፍቅር ይኖራሉ።እንደ ጎሳ ሳይሆን እንደ ሀገር ነው የሚያስቡት።ካለፈው ተምረዋል።

በሩዋንዳ ቆይታዬ ከተዋወቅኳቸው ሩዋንዳዊን አንዱ ንጋቦ ከሁቱ ወይስ ከቱትሲ ወገን ነህ ብዬ ስጠይቀው historically I’m Hutu ብሎ ነበር የመለሰልኝ።በጎሳ መከፋፈል አሁን ቦታ የለውም የሚል አንድምታ ነው ያለው መልሱ። አሁን የጎሳ ግጭት አይኑር እንጂ አብዛኛውን የሃገሪቱን የስልጣንና የሃብት ከፍታ የተቆጣጠሩት የፖል ካጋሜ ወገን የሆኑት አናሳዎቹ ቱትሲዎች ናቸው የሚል ቅሬታ ከሁቱዎች ወገን ይሰማል። የቅኝ ገዢዎች ‘ቱትሲዎች ከኢትዮጵያ ነው የፈለሳችሁት በውበትም በእውቀትም ከሁቱዎች ትበልጣላችሁና ስልጣን የሚገባው ለናንተ ነው’ በሚል የጀመሩት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ውጤት ነው ዘር ማጥፋቱ። የቡታሬ ከተማ ነዋሪ አንድ መቶ ሺህ ይገመታል።ከተማዋ ከኛዎቹ ሃዋሳ አልያም አዳማ ጋር ለንፅፅር አትቀርብም።ትንሽ ናት።በፅዳት ግን ታስከነዳቸዋለች።

ኪጋሊ ከአፍሪካ ፅዱ ከተሞች አንዷ ናት።በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2008 ላይ ፌስታልና መሰል የማይበሰብሱና አካባቢን የሚበክሉ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም በመላ ሃገሪቱ በአዋጅ ከተከለከለ በኋላ የኪጋሊ ውበት እና ፅዳት ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ ነዋሪዎች ነግረውኛል። ከአህጉሪቱ ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞች ዝርዝርም ላይም ከመጀመሪያው ረድፍ የምትቀመጥ ናት ኪጋሊ።ከተማ ለማማር የግድ ከላይ እስከታች በመስታወት በተጀቦኑ ህንፃዎች መታጀብ እንደሌለበት ጥሩ ማሳያ መሆን ትችላለች። በሰፋፊና አረንጓዴ መናፈሻዎች የተሞላች እና በየቦታው ዛፎች የሚታዩባት ውብ ከተማ ናት። ኪጋሊም ሆነ ቡታሬ ላይ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እኛጋ በተለምዶ ላዳ እያልን የምንጠራቸው አይነት የኮንትራት ታክሲዎችና የከተማ አውቶቡሶች ቢኖሩም አብዛኛው ሰው አንድ ሰው የሚያፈናጥጡ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሞተር ብስክሌቶችን ይጠቀማል። አሽከርካሪዎቹ ከላይ የደንብ ልብሳቸውን ደርበው አናታቸው ላይ ከአደጋ መከላከያ ቆብ ማድረግና ለተሳፋሪዎችም ቆብ ማዘጋጀት ግዴታቸው ነው።

ስለ ሩዋንዳ ውበት አንስቶ ስለ ሃገሬው ቆነጃጅት ሳይጠቅሱ ማለፍ አይገባምና በየቦታው አዲስ አበባ ያሉ እስኪመስል ኢትዮጵያዊያን ውብ ሴቶችን የመሰሉ ማየት መጀመሪያ ያልጠበቅነው ኋላ ላይ የለመድነው ሆነ። ኪጋሊ ወደሚገኘው ላሊበላ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ስንገባ ኢትዮጵያዊ መስላን በአማርኛ ያናገርናት አስተናጋጅ ሩዋንዳዊት ኖራ በሃገሬው ቋንቋ ኪኛሩዋንዳ መልሳ አስደንግጣናለች። ለኢትዮዽያዊያን ያላቸው ፍቅር ልዩ ነው።ሃገራችሁ የሃገራችን ወዳጅ የክፉ ቀን ደራሽ ናት ይላሉ።ደማችን አንድ ነው የውብ ሴቶች መገኛ መሆናችንም ያመሳስለናል የሚለው ከብዙ ሩዋንዳዊያን አንደበት የሚደመጥ ነው። ቢሾፍቱ ከተማ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ብዙ ሲቪል እና ወታደር የሆኑ ሩዋንዳዊያንን አግኝቼ በሚሰባበር አማርኛ አዋርተውኛል። ስለ ኢትዮጵያ ምን እንደሚያውቁ ሲጠየቁ ቴዲ አፍሮን የሚጠሩ ጥቂት አይደሉም።ላንባዲና የሚለው ዘፈኑን ከልጅ እስከ አዋቂ ተወዳጅ ነው።

ሩዋንዳ አሁንም ጦርነት ያለ ይመስል በቀልድ መልክ ‘ስትመጣ ሁለት ክላሽንኮቭ ይዘህልኝ ና’ የሚል ወዳጅ ጥይት እንደ ቲማቲም በየቦታው የሚሸጥ የሚመስለው አይጠፋም። ሃገሬዎቹ ሲናገሩ እንኳን በጎሳ ተቧድኖ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ፀብ የተለመደ አይደለም።ፀብ፣ግጭትን መሸሽን ከጠባሳቸው ተምረዋል።አዲስ አበባ ላይ ቦክስ የሚያሰነዝር ነገር ኪጋሊ ላይ በዝምታ ይታለፋል።

ወደ ኪጋሊ የሚወስደኝ አውሮፕላን ውስጥ ሆኜ ስለ ሩዋንዳ ሳስብ ጭንቅላቴ ውስጥ የነበሩት ምስሎች ቤተኛ ከመሆኑ የተነሳ ቡና ፈልቶአል ተብሎ ቢጠራ እንኳን አዲስ አበባ የሚመጣ የሚመስለኝ የሃገራቸው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ያሉ ዘግናኝ ትዕይንቶ ብቻ ነበሩ። ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ኪጋሊን ስለቅ ግን የሩዋንዳ ምስል በሌላ ተተክቶአል። በትላንት ፀባቸው መቃብር ላይ የዛሬ ፍቅርና መቻቻልን ያነፁ መልካም ሰዎች ባሉባት ሩዋንዳ!!

ምዊሪዌ~መልካም ውሎ የዛሬ ሁለት ዓመት በዚሁ ቀን የተለጠፈ

ምንጭ:-  ሸ.ነ.ግ – Sheneg

Advertisement