የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር – Starting a Relationship

ከሰዎች ጋር መተዋወቅና ጓደኝነት መመስረት አስደሳች ስሜትን መፍጠሩ አይቀርም፤ ጉዳዩ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ሲሆን ደግሞ ትንሸ ለየት ይላል።

ያንን ጓደኝነት እና ትውውቅ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረሱ ደግሞ ለበርካቶች አስደሳች እና የተለየ ስሜትን የሚፈጥር ጉዳይ ነው።
የስነ ልቦና ባለሙያዎች ትውውቁን ወደ ፍቅር ጓደኝነት ለማምራት እነዚህን መንገዶች ይከተሉ ይላሉ።
ፍላጎትን መለየትና ማሳወቅ፦ በየትኛውም የህይዎት ምህዋር ውስጥ የመጀመሪያው እና ቀዳሚው ነገር ፍላጎትን መለየትና መረዳት ነው፤ በፍቅርም እንደዛው።
ከዚህ አንጻርም ከበርካታ ሴቶች/ወንዶች ጋር ትውውቅ እና ግንኙነት ቢኖርም፥ ለእኔ የቱ ይበጀኛል የሚለውን መለየትና መወሰን አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከተዋወቁት ጋር በፍቅር መውደቅ እና አብሮ መሆን ምኞትን ለጊዜው ጋብ አድርጎ የሚሆነውን መለየት፤ ያን ጊዜ ፍቅር መጀመሩም ሆነ አብሮ መዝለቁ ቀላል ነው ይላሉ።
በፍቅር ግንኙነት ዙሪያ የስነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሄለን ፊሸር፥ አዕምሮ ጉጉት እና ፍላጎት ያለበት፣ አስደሳች ግን ዘላቂነት የሌለው ፍቅር እንዲሁም ዘላቂ የሆነ የፍቅር ግንኙነትን በተመሳሳይ ጊዜ ማስተናገድ እንደሚችል ይናገራሉ።
ከዚህ አንጻርም ማንም ሰው በዚህ መልኩ ከሶስት የተለያዩ ሰዎች ጋር በእንዲህ መልኩ ፍቅር እና ፍቅር መሳይ ግንኙነቶችን መጀመር እንደሚችልም ይገልጻሉ።
ወሳኙ ጉዳይ ግን ሶስት የተለያዩ ፍላጎቶችን በድብቅ ማስኬዱ ሳይሆን ትክክለኛው የእኔ ምርጫ የትኛው ነው የሚለውን መለየት ይሆናል።
ከቀረቧቸው ሰዎች መካከልም እርስዎ የሚፈልጉት እና የፍቅር አጋርዎ ቢኖረው/ቢኖራት ምርጫየ ነው የሚሉትን ከአካላዊ ቁመና ጀምሮ፥ ስብዕና እና ባህሪን መሰረት ባደረገ መልኩ ፍላጎትን ማወቅ እና መወሰን አስፈላጊው እንደሆነም ያስረዳሉ።
ፍላጎትን ለአጋርዎ ማጋራት፦ ፍቅር ለመጀመር አስበው ለተዋወቁት ሰው ሃሳብን እና ፍላጎትን ማጋራት የእርስዎን ፍላጎትና ምኞት ለመግለጽ ይረዳዎታል።
ይህም የግንኙነታችሁን ዘለቄታዊነት የተመለከተ ውይይት ለማድረግ ይረዳል፤ አብሮነታችሁ እርስዎ ሃገር ለቀው ከወጡ በኋላ ስለ መቀጠል አለመቀጠሉ እና በማንኛውም ሁኔታ ዘለቄታዊ ስለመሆኑ ለመነጋገርም እንዲሁ።


ግን ደግሞ ሃሳብን ማጋራት ማለት ያ ሰው ከእኔ ጋር ይዘልቃል/ ትዘልቃለች ማለት ሳይሆን፥ የሚሄዱበትን መንገድ ማሳያ ብቻ መሆኑን መረዳትም ተገቢ ይሆናል።
ከዚህ አንጻር መዳረሻችሁ የሚወሰነው በመሰል ጅማሮዎች ነውና ይህን መሰሉን አካሄድ ያጎልብቱ።
ራስን መሆን፦ ራስን መሆን ሲባል ከፀባይ ጀምሮ አለማስመሰል፣ የሌለን ነገር አለኝ ማለትን ጨምሮ እቅድን፣ የወደፊትን ሃሳብዎን፣ እምነት ላይም ሆነ ነገሮች ላይ ያለን አመለካከትን በተመለከተ የሚያምኑበትንና የሆነውን ከመናገር ይጀምራል።
ከዚህ በተቃራኒው ሆነው ጊዜያዊ ለሆነ ነገር ሰው ማግኘትን ባይለምዱት ይላሉ ባለሙያዎቹ።
ዘወትር በየትኛውም ቦታ ራስዎን ሆነው መቅረብን ልማድዎ ያድርጉ።
የእኔነት ስሜት ወይም መረዳት፦ አጋርህን መረዳትና በስሜት እንደተግባባችሁ ማሳየትም ያሰባችሁትን የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር እና ለማዝለቅ መልካም ነው።
“አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች” የሚል መጽሃፍ የጻፉት ዶክተር ጋሪ ቻፕማን፥ ከአጋራችሁ ጋር እነርሱ በሚረዱት መንገድ ስሜታችሁን ለመጋራት ሞክሩ ይላሉ።
እንደ እርሳቸው፥ አካላዊ ንክኪ፣ እርግጠኛነት (እሺታም ሊሆን ይችላል)፣ እሺታ የታከለበት የአገልጋይነት መንፈስ፣ ጥሩ ጊዜን አብሮ ማሳለፍ እና ስጦታዎች አምስቱ የፍቅር ቋንቋዎች ናቸው።


እናም እርስዎ አጋርዎ ሊረዳዎት በሚችለው አንደኛው መንገድ ስሜትዎን መግለጽን ይልመዱ ሲሉም ያስረዳሉ።
ምናልባት አጋርዎን እወድሻለሁ ወይም በጣም ቆንጆ ሴት ነሽ ብለዋት ምላሽ ባያገኙ እንዳይከፉ።
ከዚያ ይልቅ የእርሷ የፍቅር ቋንቋ አካላዊ ንከኪ አልያም ሌላኛው ሊሆን ይችላልና ስሜትዎን ሲገልጹ አጋርዎ የሚቀበልበትን መንገድ ማጤንን ይመክራሉ።
ቴሌቪዥን እየተመለከቱ በድንገት ማቀፍ፣ መሳም እና መሰል ድርጊቶችም ይበልጥ ስሜትን ለመግለጽ እና ለመግባባት አማራጮች እንደሆኑም ነው የሚናገሩት።
ምንም ቢሆን ግን የእርስዎን የፍቅር ቋንቋ ለአጋርዎ ማሳወቅን አይዘንጉም ይላሉ ዶክተር ቻፕማን።
በፍቅር ትልቁ ስኬት ለፍቅር አጋር የእኔነት ስሜት ማሳየቱና መረዳት ነውና ያንኑ ይተግብሩ ሲሉም ያክላሉ።
በጫካ የሚበቅሉ አበባዎች እንደምትወድ እያወቁ ሮዝ አበባ ከመስጠት ይቆጠቡ፤ ለእግር ጉዞ ሽርሽር አብሮ መውጣት፣ በእራት ሰዓት ቴሌቪዥን ማጥፋትና እየተመገቡ መጨዋወትንም ያጎልብቱ።
በፍቅር አለም ውስጥ አልተወደድኩም የሚል እና ያለመፈለግ ስሜት አደገኛ ስለመሆነም ስሜቱ እንዳይፈጠር ያስቡበት።
ከዚህ ባለፈ ግን ባለዎት ልክ ሰው መቅረብ እና በዚያው ልክ መግባባትንም በፍቅር ህይዎት ጅማሮ ላይ ያክሉበት።

ምንጭ፦ howstuffworks.com

Advertisement